መርካቶን በስልካችን
ዓርብ፣ ጥር 19 2015ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር የተወሳሰበና ኋላቀር የአገራችን የግብይት ሥርዓትን በዲጂታል ስርዓት ለመቀየር ``መርካቶን በስልካችን`` በሚል መርህ የሚንቀሳቀስ አሸዋ የበይነ መረብ ግብይት መስራችና ስራ አስኪያጅ ጋር ቆይታ እናደርጋለን። የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ አስተያየትም አካትተናል።
በአገሪቱ የምርትና አገልግሎቶች ግብይት እጅግ ኋላቀርና ውስብስብ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ላይ ግብይቱ ሻጭና ገዢ የሚያገናኙ በየእርከኑ ያሉ ደላሎች ሻጭም የለፋበትን ገዢም በውድድር ላይ የተመሰረተና ለምርቱ ወይም አገልግሎቱ የሚመጥን ዋጋ ከፍሎ እንዳይጠቀም እንቅፋት እንደሆነ የመስኩ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
ለዚህ የተወሳሰበ ችግር እንደ አንድ መፍትሔ የሚወሰደው በበይነመረብ የሚደረግ ግብይት ነው። ``አሸዋ የቴክኖሎጂ ሶልሽንስ`` በሚል የሚጠራው ድርጅት የተለያዩ መተግበሪያዎችን በማበልጸግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከነዚሁም አንዱ የበይነ መረብ ግብይትት ስርዓት ነው። ወጣት ዳንኤል በቀለ የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው።
`` ትልቅ ክፍተት ነው ያለው። ይህ ማለት ዲጂታል ተጠቃሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ30 ሚልዮን በላይ አለ። ግን አብዛኛው መረጃ ብቻ ነው እያገኘ ያለው እንጂ ሕይወቱን እየቀየረ አይደለም፤ የሥራ ዕድሉ እየተጠቀመበት አይደለም ከጥቂቶች ውጭ።``
ድርጅቱ በበይነመረብ አማካኝነት የግብይት ሥርአቱን ለማዘመንና የተጠቃሚውን ጉልበትና ጊዜን በመቆጠብ እስካሁን እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ወጣት ዳንኤል እንዲህ አጫውቶናል።
`` ሁሉንም በአንድ ቦታ የምንገዛበት የገበያ ቦታ ነው። መርካቶን በስልካችን ነው እያልን ያለንው። በዓለም ላይ የግብይት ሥርአቱ ተቀይሮ በኦንላይን ወይም ደግሞ በስል ነው እየተከናወነ የሚገነው። በአገራችንም ይሄ ሂደት እያደገ ነው። በተለይ ከኮረና ወዲህ በሚገርም ሁኔታ እየተቀየረ ነው ያለው። አሁን ባለኝ ዳታ እስከ 6 ሚልዮን የሚሆን ሰው መግዛትም መሸጥም እያደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።``የበይነ መረብ ግብይቱ ጋር ተያይዞ ያቋቋሙት ምርትና አገልግሎት ወደተጠቃሚ የማድረስ ሥራም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሆነ ወጣት ዳንኤል ይገልጻል።
በበይነመረብ የሚደረጉ ግብይቶች በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ ሐገራት የንግድ ሥርዓቱን በማዘመንንና ገዢና ሻጭ ያለ ብዙ ድካም በቀጥታ በማገናኘት ኢኮኖሚው ለሚያመነጨው ሐብት የበኩሉን የማይተካ ሚና እንዳለው የነገሩን ደግሞ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያና በርካታ መተግበሪያዎችን በማበልጸግ የሚታወቁት አቶ ሐብታሙ ታደሰ ናቸው። አቶ ሀብታሙ በአሁኑ ሰዓት የዛይራይድ መስራችና ዋና ሥራ ስኪያጅ ናቸው።
የበይነ መረብ ግብይቶች ምርት ወደ ተጠቃሚ ለማድረስ በርካታ የሰው ሃይል ስለሚፈልጉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ባለሙያው አቶ ሐብታሙ ታደሰ ገልጸዋል።
የበይነመረብ ግብይቱ ገና ከጅምሩ በበርካታ ችግሮች እየተፈተነ ነው። ከኢንተርኔት መቆራረጡ በላይ እንደዋና ችግር የሚታየው ግን የፖሊሲ ችግር እንደሆነ ያብራራሉ አቶ ዳንኤል።`` የኦንላይን ግብይቶች ጥቅሞች ሰፋ ያሉ ናቸው። በተለይ እንደኢትዮጵያ ባለ ድሃ አገር ምርቶችህን ይዘህ ወደ ገበያ ለመውጣት ብትፈልግ አንዱ የሚያስፈልግህ የኦፊስ ስፔስ ነው። ይህ በጣም ውድ የሆነበት ሁኔታ አለ። ብዙ እቃ የምትይዝ ከሆነም ሰፋ ያለ ስቶር ያስፈልገሃል። እሚገዛህ ደግሞ አንተ ያለህበት ቦታ የሚመጣ ብቻ ነው። የኦንላይን ግብይት ግን ቢሮም ሳያስፈልግህ እቤትህ ሆነህም ልትሰራው የምትችል ነው። የምታገኘው የገበያ መጠንም በጣም ትልቅ ነው።``
የበይነ መረብ ግብይቶች በእጁ ጥሬ ገንዘብ የዞ የማይንቀሳቀስ ማሕበረሰብ በመፍጠር በኩልም ትልቅ ሚና እንዳላቸው አቶ ሐብታሙ አክሏል። የአሸዋ ዶት ኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል በቀለ ሕብረተሰቡ ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እንዲገባ በርካታና ተከታታይ የማንቃት ስራዎች እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ባለሐብቶችም የዚሁ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን ተናግሯል። ከተለያዩ ድርጅቶች በጋራ እየሰሩ እንደሆነ በማከል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ታምራት ዲንሳ