1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐንጋሪ በስተመጨረሻ የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን ገንዘብ እንዲሰጥ ፈቀደች

ሐሙስ፣ ጥር 23 2016

የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን ርዳታ እንዲሰጥ ሐንጋሪ ተስማማች። ኅብረቱ ለዩክሬን ሊሰጥ ያቀደውን ርዳታ ሐንጋሪ ባለመፍቀዷ ለሳምንታት አራዝሞት ነበር ። ዛሬ ግን 27 ቱም የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ብራሰልስ ውስጥ ባካሄዱት ጉባኤ ለዩክሬን ተጨማሪ የ50 ቢሊዮን ዩሮ እርዳታ ለመስጠት ተስማምተዋል።

https://p.dw.com/p/4bw2V
Belgien, Brüssel | Treffen von Staatschefs am Rande eines Treffens des Europäischen Rats
ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images

ሐንጋሪ የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን ርዳታ እንዲሰጥ ተስማማች

የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ዛሬ ብራሰልስ ውስጥ ባካሄዱት ጉባኤ ለዩክሬን ተጨማሪ የ50 ቢሊዮን ዩሮ እርዳታ ለመስጠት ተስማሙ። የኅብረቱ የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርል ሚሼል በትዊተር እንዳስታወቁት ሀያ ሰባቱም የኅብረቱ አባል ሀገራት በሙሉ ከኅብረቱ በጀት ለዩክሬን ተጨማሪ 50 ቢሊዮን ዩሮ የእርዳታ ማዕቀፍ ለመስጠት ተስማምተዋል።

ሚሼል ስምምነቱ ለዩክሬን በፍጥነት የተሰጠ ዘላቂ ድጋፍ መሆኑን ገልጸው የአውሮጳ ኅብረትም በዩክሬን ጉዳይ የመሪነቱን ቦታና ሃላፊነቱንም እየወሰደ ነው ሲሉ ገልጸዋል። 

የዩክሬን ፕሬዝዳን ት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ስምምነቱን በደስታ ተቀብለዋል። ዜልንስኪ እርዳታው የሀገራቸውን የምጣኔ ሀብትና ፋይናንስ  መረጋጋት በዘላቂነት ያጠናክራል ብለዋል።ለዩክሬን ሊሰጥ በቃቀደው በዚህ እርዳታ ላይ ባለፈው ታህሳስ የአባል ሀገራት መሪዎች ሲነጋገሩ እቅዱን የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን ውድቅ አድርገውት ነበር።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና የሀንጋሪ ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን ሲጨባበጡ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና የሀንጋሪ ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን ሲጨባበጡ ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images

የኅብረቱ አባል ሀገራት ለሳምንታት ከኦርባን ጋር ሲወዛገቡ ከቆዩ በኋላ  ነበር ዛሬ የተስማሙት። ጉባኤው ከመጀመሩ አስቀድሞ የኅብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ኦርባን ጫናውን በማንሳት ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ግፊት ካደረጉባቸው በኋላ  ለዩክሬን ርዳታ እንዲሰጥ ሐንጋሪ ተስማምታለች። የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባን የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን ሊሰጥ ያቀደውን የ50 ቢሊዮን ዩር የገንዘብ ድጋፍ ሀገራቸው ስታከላክል የቆየችው ስለገንዘቡ ዋስትና ባለማግኘቷ መሆኑን ተናግረዋል ። ሐንጋሪ የተጨነቀችውም ለሐንጋሪ የሚገባው ገንዘብ  ወደ ዩክሬን ይሄዳል ብላ ነበር ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሯ ። በእርግጥ በአውሮጳ ኅብረት እና የኅብረቱ አባል በሆነችው ሐንጋሪ መካከል ዩክሬንን በተመለከተ የውዝግቡ ምክንያት ምንድን ነበር? 

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ