ለጀርመን ጦር 100 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚመደብ መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ይፋ አደረጉ።
እሑድ፣ የካቲት 20 2014የጀርመን መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ለአገራቸው ጦር 100 ቢሊዮን ዩሮ (112.7 ቢሊዮን ዶላር) ልዩ በጀት እንደሚመድቡ ይፋ አደረጉ። የጀርመን ፌዴራል የትራንስፖርት እና ዲጂታል መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የሩሲያ አውሮፕላኖች በአገሪቱ የአየር ክልል እንዳይበሩ አድግዷል።
ቡንደስታግ ተብሎ የሚጠራው የአገሪቱ ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው ልዩ ስብሰባ ንግግር ያደረጉት መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ "በዚህ አንገብጋቢ ሰዓት ዩክሬንን ማገዝ አለብን" ሲሉ ተደምጠዋል።
"ይኸን ጦርነት የመረጡት ፑቲን ናቸው እንጂ የሩሲያ ሕዝብ አይደለም" ያሉት መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ "ስለዚህ የፑቲን ጦርነት እንደሆነ ማየት አለብን" በማለት ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
በጀርመን የተመረቱ ጦር መሣሪያዎች ለዩክሬን እንዲሰጡ መንግሥታቸው ያሳለፈው ውሳኔ "የፑቲንን ጥቃት ለመመከት ብቸኛው ምላሽ" እንደሆነም አስረድተዋል። የጀርመን መንግሥት ትላንት ቅዳሜ 1,000 ጸረ-ታንክ የጦር መሣሪያዎች እና 500 ከምድር ወደ ሰማይ የሚምዘገዘጉ ሚሳይሎች ከጀርመን ጦር ክምችት ለዩክሬን እንዲሰጥ ወስኗል። ከዚህ በተጨማሪ ኢስቶኒያ እና ኔዘርላድስ ጀርመን ሰራሽ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ለዩክሬን ለመለገስ ፈቃድ አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት እርምጃ ተከልክሎ ነበር።
ጀርመን ለዩክሬን በጦር መሣሪያ ከምታደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ኦላፍ ሾልስ በ2022 በጀት ዓመት 100 ቢሊዮን ዩሮ (112.7 ቢሊዮን ዶላር) ለአገራቸው ጦር ሠራዊት ለመመደብ ቃል ገብተዋል። ጀርመን ከአሁን በኋላ በየአመቱ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 2 በመቶውን ለመከላከያ እንደምትመድብ ሾልስ በምክር ቤቱ ንግግራቸው ገልጸዋል።
"ዩክሬንን በማጥቃት ፑቲን የፈለጉት አንድን አገር ከዓለም ካርታ ለመፋቅ ብቻ አይደለም። ከሔልሲንኪ ጀምሮ የነበረ የአውሮፓ የጸጥታ መዋቅርን ጭምር እያጠፉ ነው" ብለዋል።
ከዛሬ እሁድ ጀምሮ የሩሲያ አውሮፕላኖች በጀርመን ሰማይ እንዳይበሩ የአገሪቱ ፌዴራል የትራንስፖርት እና ዲጂታል መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አግዷል። የጀርመን ጎረቤት ቤልጅየምም ተመሣሣይ እርምጃ መውሰዷን ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ደ ክሮ ይፋ አድርገዋል።
የግል ጀቶችን ጨምሮ ንብረትነታቸው የሩሲያ የሆኑ አውሮፕላኖች በፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቡልጋሪያ፣ ሮማኒያ እና ስሎቬኒያ ሰማይ መብረር ተከልክለዋል። ብሪታኒያ እርምጃውን በመውሰድ ቀዳሚ ስትሆን ጣልያንም የአየር ክልሏን ለሩሲያ አውሮፕላኖች እንደምትዘጋ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ከሩሲያ 800 ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራው ፊንላንድ ተመሣሣይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ላይ እንደምትገኝ የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትር ቲሞ ሐራካ ይፋ አድርገዋል። የአውሮፓ አገራት የሚወስዱት እርምጃ ከዴንማርክ፣ አየርላድ እና ኦስትሪያ ድጋፍ አግኝቷል።