1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ለኢትዮ አሜሪካውያን መራጮች የቀረበው ጥሪ

ታሪኩ ኃይሉ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 7 2017

የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ ከተቋቋመበት ዓላማዎች አንዱ፣ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር እንዲሁም የኢትዮጵያን ጥቅም ከሚያስጠብቁ የአሜሪካ ተመራጮች ጋር መስራት ነው።

https://p.dw.com/p/4luQv
የአሜሪካ ኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (AEPAC) እንደሚለዉ ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ፖለቲከኛ መምረጥ አለባቸዉ
የአሜሪካ ኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (AEPAC) ባዘጋጀዉ ስብሰባ ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን ከአሜሪካ ዕጩ ፖለቲከኞች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋልምስል AEPAC via Tariku Hailu/DW

ለኢትዮ አሜሪካውያን መራጮች የቀረበው ጥሪ

በአሜሪካ በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን በንቃት በመሳተፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ዕጩዎችን እንዲመርጡ የአሜሪካ ኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ ኤፓክ) ጠየቀ።ኤፓክ፣ሰሞኑን ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ተወካዮች እና ከሌሎች የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋር ሥለምርጫዉ ሒደት ተነጋግሯል።ታሪኩ ኃይሉ አሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ውስጥ የተደረገዉን ውይይት የሚመለከት ዘገባ ልኮልናል።

የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን ህዝብጉዳዮች ኮሚቴ ከተቋቋመበት ዓላማዎች አንዱ፣ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር እንዲሁም የኢትዮጵያን ጥቅም ከሚያስጠብቁ የአሜሪካ ተመራጮች ጋር መስራት ነው።የኮሚቴው የቦርድ አባልና ፀሐፊ አቶ ዮም ፍስሐ፣ ሰሞኑን የተካሄደውን ውይይት በተመለከተ፣ ከዶይቸ ቨለ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሚከተለው ምላሽ ሰጥተዋል።

"ለኢትዮጰያውያን እነዚህ ተወዳዳሪዎች ምን ያህል ኢትዮጵያን እንደሚረዱ፣ ምን ያህል ኢትዮጵያን እንደሚወዱ፣ ከተመረጡም ለኢትዮጵያ ሰላምና ለሰብዓዊ መብት፣ለሁለቱ አገሮች ወዳጅነት እንደሚሰሩ የገለጹበት ታሪካዊ ጉባኤ ነው።"

የትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተሣትፎ

ወይዘሪት እየሩሳሌም ክብረት፣በኤፓክ ወጣቶች ኮሚቴ ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ ታገለግላለች።ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ወጣቶች  በአሜሪካ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ትናገራለች።

"ለሃገራችን፣ እዚህ ላለነውም ተጽዕኖ መፍጠር እንድንችል ሁለቱም የሚያያዝ ነገር ነውና፤በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሠሩ እናበረታታቸዋለን።በየስቴቶቻቸው  ያሉ የኮንግረስ ተመራጮች፣ የሴኔት ተወካዮችን፣ሃገረ ገዥዎችን አግኝተው፣ ከእነሱ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ጥሩ የሆነ  ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በማድረግ ደረጃ ከኤፓክ ጋር ወጣቱ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ያለነው።

 

የአሜሪካ ኢትዬጵያ ሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ኢትዮጵያ አሜሪካዊያን በአሜሪካ የምርጫ ሂደት በመራጭም ሆነ በተመራጭነት በንቃት እንዲሳተፉ ይንቀሳቀሳል።ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማትን በሚደግፉ የአሜሪካ ፖሊሲዎች ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርጉ እድል እንደሚሰጣቸው ኤፓክ ይገልጻል።አቶ ዮም፣መሆኑን ኢትዮ አሜሪካዊያን ጥቂት ቀናት በቀሩት የአሜሪካ  አጠቃላይ ምርጫ እንዲመርጡና የዜግነት ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በቅርቡ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በሚደረገዉ ምርጫ ኢትዮጵያዉያን አሜሪካዉያን በንቃት እንዲሳተፉ AEPAC ጠይቋል
የአሜሪካ ኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ AEPAC) መሪዎች ከዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች ጋርምስል AEPAC

"የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በአሜሪካ ሃገር መምረጥ የሚችለው፣ ዜግነት ያለው መብት ያለው፣ቁጥሩ በጣም ብዙ ነው፤ የሚመርጠው ግን ቁጥሩ አነስ ያለ ነው።ስለዚህ እኛ ትልቁ ስራችን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው እንዲመርጡ፣ ሲመርጡ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ጥቅም የሚያስጠብቁ እዚህ የምንኖረውን ኢትዮጵያን ዲያስፖራ ጥቅም የሚያስጠብቁትን በኢምግሬሽን፣ ስለ ኢኮኖሚ ጉዳይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሉበት አካባቢ ሁሉ፣ ለኢትዮጵያውያኖች ዕውቅና የሚሰጡትን ሰዎች እንዲመርጡ ነው የምንፈልገው።"

 

"ስዊንግ ግዛቶች"

 በምርጫው ከፍተኛ ፉክክር በሚጠበቅባቸው እና በተለምዶ "ስዊንግ ግዛቶች"በሚባሉት፣ጆርጂያ፣ፔንሲልቫንያ፣ዊንኮንሲን፣ኒውሃምሻየር ፣ሚኒሶታና ሜይንን ጨምሮ ባሉ ግዛቶች፣የኢትዮጵያ አሜሪካውያኑ ድምጽ ወሳኝ ድርሻ አለው።ወይዘሪት እየሩሳሌም፣በምርጫው ወቅት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድምጽ ሲሰጡ ልብ ሊሏቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ ተከታዮን አስተያየት ለዶይቸ ቨለ ሰጥተዋል።

" አንዳንድ ጊዜ በመጨረሻ ሰዓት ላይ ነው፣እዛው ምርጫ ላይ ይኼ ይኼ ተብሎ በፓርቲ የምንመርጠው፣ያ መቅረት አለበት። በተለይ ለአፍሪቃ ዲያስፖራ ቀድመን የትኛው ይጠቅመናል የትኛው ዕጩ ሊሰማን ይችላል የሚለውን ነገር ቀድሞ ማጣራቱ በጣም ትልቅ ተጽእኖ አለው።እና እንደ ወጣት ያንን ነው የምናበረታታው፣ በተጨማሪም ደግሞ ለምርጫ መመዝገብ ቁጥራችን ኢትዮጵያ ዲያስፖራ እዚህ ያለው በጣም ብዙ ነው። ግን ከብዙ ደግሞ የተመዘገው ቁጥር በጣም የቀነሰ ነው።መመዝገብ ትልቅ ነገር ነው፣ ምክንያቱም የፖለቲካ ሰዎቹ ያውቁታል ቁጥራችንን።ስለዚህ ሁሉም ዲያስፖራ ወጥቶ እንዲመዘግብ፣ ድምጽ እንዲሰጥ ምክንያቱም ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚያደርገን ተመዝግበን ድምጽ መስጠታችን ነው።"ብላለች።

ታሪኩ ኃይሉ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ