ለሴቶች መብትና እኩልነት የሚሟገተው መጽሄት
ዓርብ፣ ግንቦት 27 2013« Addis Powerhouse» በየወሩ በበይነመረብ አማካኝነት ለአንባቢያን የሚቀርብ መጽሔት ነው። በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው ይኼው መጽሔት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎን፣ ሴትነት እና ኃይማኖትን፤ ጽንፅ ማጨናገፍን እና የሴተኛ አዳሪነት ሙያን የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል። የዚህ መጽሔት መስራቾች እና አዘጋቾች ህሊና ኃይሉ እና ሃና ለማ ይባላሉ። ሁለቱም የ 24 ዓመት ወጣቶች ናቸዉ። « Addis Powerhouse» የሚል መጠሪያ ለመጽሔታቸው የሰጡት ራሳቸው ናቸው። «አዲስ የሚለው ቃል አዲስ አበባን እና የዲጂታል መፅሔት አዲስ እንደመሆኑ መጠን ያንን ለማመላከት ሲሆን ፓወር ኃውስ የሚለው ደግሞ የኃይል አቅራቢ እንደሆነ እና ነገሮችን ለመለወጥ አቅም እንዳለው ለማሳየት ነው።» ትላለች ሃና።
የህሊና እና ሃና ትውውቅ የሚጀምረው ITEC የሚባል ድርጅት ውስጥ ባልደረባ ሳሉ ነው። ህሊና እንደገለፀችልን ከአንድ ዓመት ከሦስት ወር ገደማ በፊት ነው ይህንን መፅሔት ለማዘጋጀት የወሰኑት። ይህንን እውን ለማድረግ ሌሎች አራት ወጣት ሴቶች አብረዋቸው ይሰራሉ። « በፁሁፍ ላይ የምንሳተፈው እኔ እና ሃና ነን።» ሌሎቹ ደግሞ በተለይ ለድረ ገፁ በሚያስፈልጉ ስራዎች ላይ የሚሳተፉ ናቸው።
ይህ ስራ ግን ለ « Addis Powerhouse» መስራቾቹም ይሁን አብረዋቸው ለሚሰሩት ሌሎቹ ሴት ወጣቶች ቋሚ ስራቸው አይደለም። ህሊና የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ባለሙያ ስትሆን ሃና ደግሞ ያጠናችው ዲቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ነው። ሁሉም በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው ይሰራሉ። « ነፃ ሰዓት ባገኘን ቁጥር እንሰራለን። መፅሔቱ በየወሩ ነው ድረ ገፃችን ላይ የሚወጣው። ሶሻል ሚዲያ ላይ የሚወጡት የጊዜ ገደብ የላቸውም። ማንኛውም ሰው በፆታዊ ጉዳይ ላይ መፃፍ በፈለገ ቁጥር ሰዎች በኢሜል ይልኩልናል። » እነሱም ይዘቱን አይተው ገፃቸው ላይ ይለጥፋሉ። የ « Addis Powerhouse» መጽሔት እስካሁን 12 ጊዜ ይፋ ሆኗል። ሲጀምሩ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ ነበር። አሁን ላይ ደግሞ በአማርኛ መፃፍ ጀምረዋል። ሃና እንደምትለው ወደፊት ሌሎች ቋንቋዎችንም የማካተት እቅድ አለ። በአሁኑ ሰዓት «ቢያንስ አንድ ዘገባ በአማርኛ የሚፃፍበትን ሁኔታ ነው ያለው»። ለፆታ እኩልነት እና ለሴቶች መብት መሟገት ያስደስተኛል የምትለው ሃና «ያደኩበት ማህበረሰብ ለዚህ የገፋፋኝ ይመስለኛል። ለዚህም ነው ይህንን መፅሔት ለመመስረት የወሰንኩት» ትላለች።
የወጣቶቹ ዓላማ የማህበረሰባቸውን እና የሴቶችን ግንዛቤ ማሳደግ ሲሆን ሌላው ደግሞ ለሴት የመብት ተሟጋጆች ሀሳባቸውን የሚያጋሩበት መድረክ መፍጠር ነው። እነሱም ሴቶች በፖለቲካ ያላቸውን ተሳትፎ የሚመለከት አንድ መጠይቅ አዘጋጅተው ነበር። ህሊና « ዋና አላማችን ሰዎች በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩ እንጂ ሰው ይህንን ነው የሚያስበው የሚለውን ውጤት ይፋ ማድረግ አይደለም» ትላለች። እንደዛም ሆኖ በዚህ መጠይቅ ወቅት የተሳተፉ ሰዎች «ስለምርጫው በቂ መረጃ የለኝም» የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ህሊና ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች።
ወጣቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ወቅታዊ በሆነው ምርጫ ላይ ሴቶች የሚኖራቸውን ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ርዕስ ያደረጉት በትግራይ ክልል ስለተፈፀሙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችም ነው። #endweaponizedrape ወይም አስገድዶ መድፈርን እንደ ጠመንጃ መጠቀም ይቁም የሚል ትርጓሜ ያለው ሀሽታግ የመጽሔቱ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ይነበባል። ለሴቶች መብት የሚያደርጉት ሙግት ወደዱም ጠሉም ሃና እንደምትለው « ከፖለቲካ ጋር » ይነካካል። እንደዛም ሆኖ ከሴቶች ጋር ጉዳዩ እስከተያያዘ ድረስ ለጉዳዩ ሽፋን ይሰጣሉ።
ሌላው የሃና እና ህሊና መጽሔት ያለፈው መጋቢት ወር ርዕስ ያደረገው ሴትነትን እና ኃይማኖትን የሚቃኝ ነው። « ብዙ ጊዜ ስለ ፆታ እኩልነት ሲወራ ውይይቱ ኃይማኖትን ያካተተ አይደለም» የምትለው ሃና ይህንን ወደ ጎን የማድረግ አመለካከት ለመቀየር ብለው በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ እንደፈለጉ ትናገራለች። በዚህም ዳሰሳቸው “Women in Islam” የሚባል መጽሔት አዘጋጆች ያላቸውን ተሞክሮ ጠይቀዋል። « ስላላቸው አመለካከት፣ እንዴት እንደተነሳሱ ፣ ስለ ሐይማኖት ሲያወሩ ምን አይነት ተሞክሮ እንደነበራቸው በተለይ ደግሞ ከእስልምና ጋር በተያያዘ ጠይቀናቸዋል። » ሃና እና ህሊና ሙስሊምም ይሁኑ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ከሚከተሉት ዕምነት ጋር በተያያዘ ስለገጠማቸው ፈተናም ይሁን ተሞክሮ ዝርዝር ውስጥ ስላልገቡ ይህን ይመስላል የሚል ተጨባጭ ድምዳሜ ላይ አልደረሱም።
ሴቶች በፖለቲካም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ የአመራር ቦታዎችን የሚያገኙበት አጋጣሚዎች እየተሻሻሉ መጥተዋል። ይሁንና ለተመሳሳይ ስራ እዚህ ጀርመን ሀገር ላይም በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ሴቶች ከወንዶች እኩል እየተከፈላቸው አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥስ ሴቶች ከወንዶች እኩል እንዲከፈላቸው የሚሟገቱበት ሁኔታ አለ? ህሊና « በዚህ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠር አልተደረገም። ገና እኛጋር ብዙ የሚያስጨንቁ ነገሮች ስላሉ ትኩረታችንን ወደእዛ አላዞርንም።» ትላለች። ይሁንና በተለይ የቀን እና የጉልበት ስራ የሚሰሩ ሴቶች ላይ ይህ አይነት ልዩነት እንደሚስተዋል ታዝበዋል።
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ