«15ኛው የጀርመን አፍሪቃ የኢንርጂ ጉባኤ»
ቅዳሜ፣ ግንቦት 27 2014«15ኛው የጀርመን አፍሪቃ የኢንርጂ ጉባኤ» ጀርመን፤ ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ ረቡዕ ግንቦት 24 እና ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ተከናውኗል። ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የተካፈሉበት ይህ ጉባኤ በአፍሪቃም ኾነ በጀርመን የሚገኙ የኃይል አቅራቢዎች ተቀራርበው እንዲወያዩ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር ተብሏል። በጉባኤው አፍሪቃም ኾነች ጀርመን በጋራ ተጠቃሚ ሊኾኑ ስለሚችሉባቸው ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል።
የጀርመን ኩባንያዎች የሃይድሮጂን ኃይል አምርተው ለአውሮጳ ገበያ ለማቅረብ ፍላጎት ያሳዩ የአፍሪቃ አምራቾችን በገንዘብ እንደሚደግፉም ተገልጧል። በቀጠለው የዩክሬን ጦርነት የተነሳ ሩስያ ላይ ማእቀብ በመጣሉ አውሮጳውያን ከሩስያ ያስገቡ ለነበረው ነዳጅ አማራጭ የኃይል ምንጭ መፈለግ ያሻቸዋል። በዚሁ ሳምንት የአውሮጳ ሚንሥትሮች ባካሄዱት ስብሰባ ከሩስያ ባሕር አቋርጦ ይገባ ከነበረው ነዳጅ ከሁለት ሦስተኛው በላይ እንዳይገባ ለማገድ አዲስ የማእቀብ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ትውልደ ሴኔጋል ፈረንሳዊቷ ንዲያርካ ምቦጂ፦ ዋና መሥሪያ ቤቱን ጀርመን በርሊን ከተማ ያደረገው ኮውሪ ኢነርጂ የተሰኘው ኩባንያ መሥራች እና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። የዩክሬን ጦርነት እና የአውሮጳውያኑ የማእቀብ ውሳኔ አውሮጳውያኑን ሌላ የአማራጭ ኃይል እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል ይላሉ።
«በዩክሬን ጦርነት የተነሳ የኃይል አቅርቦት ምንጫችንን ማሰባጠር እንደሚያስፈልገን መመልከት ይቻላል። አፍሪቃ እንደ ተፈጥሮ ጋዝ አይነት እምቅ የተፈጥሮ ሐብቷን ብንመለከት ያ የለውጥ መንገድ ነው። አፍሪቃ ውስጥ ያለውን ጠቀሜታም መመልከት እንችላለን።»
ንዲያርካ ምቦጂ፦ «አፍሪቃ የአውሮጳን የኃይል አቅርቦት ቀውስ ለመፍታት ቁልፍ ሚና ትጫወታለች» ሲሉም አክለዋል። በተለይ ደግሞ በአፍሪቃ ከርሠ ምድሮች ውስጥ ታጭቆ የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ «ጠቀሜታው እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም» ብለዋል።
የኃይል አቅርቦት የተጠማችው ጀርመንን እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያሻውን አፍሪቃ ያቀራረበው ይህ «የጀርመን አፍሪቃ የኢንርጂ ጉባኤ» የተከናወነው የጀርመን መራኄ-መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ በቅርቡ አፍሪቃን ከጎበኙ እና ነዳጅ እና ጋዝ ወደ አውሮጳ ለመላክ አስፈላጊ መሠረተ-ልማቶችን በመገንባቱ ረገድ ድጋፋቸውን ለመስጠት ውል ከፈረሙ በኋላ ነው።
ምንም እንኳን ከአፍሪቃ መጠነ ሰፊ የሐይድሮጂን ኃይል ለማስገባት ጀርመን ብታቅድም አፍሪቃ ውስጥ ያለው ነዋሪ ከግማሽ በላዩ የንጹህ ኃይል አቅርቦት ምንጭ የለውም። ያም በመኾኑ በርካታ ነዋሪዎች የኃይል ምንጭ ለማግኘት ደኖችን ይመነጥራሉ፤ እንደ ኩበት ያሉ ለባዮማስ አስፈላጊ ግብአቶችንም በእየ ቤታቸው ያነዳሉ። ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ውስጥ 95 በመቶ ነዋሪዎች የኃይል ምንጫቸው የባዮማስ ግብአቶች ናቸው። ይህም በሀገር ምርት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ የኢትዮጵያ የውኃና ኢነርጂ ሚንስቴር ዴኤታ ሱልጣን ዋሊ በዶይቸ ቬለ ተጠይቀው ተናግረዋል። እንዲያም ኾኖ ግን ኢትዮጵያ የኃይል ምንጩዋን ከኃይድሮኤሌክትሪክ ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ለማሸጋገር ጥረት እያደረገች መኾኗንም በቃለ መጠይቁ ወቅት ተናግረዋል።
«በአሁኑ ወቅት በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ብዙ እየሠራን ነው። በተለይ ደግሞ የኃይል ምንጫችንን በውኃ መዘውር በሚገኝ የሃይድሮፓወር ኃይል ብቻ ጥገኛ ከማድረግ ባሻገር ከፀሓይ፤ ከንፋስ፤ ከከርሠ-ምድር በሚገኙ የኃይል ምንጮች እና በሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጮች ቅይጥ በማድረጉ በኩል። ስለዚህ ለእኛ ከግልም ኾነ ከሕዝባዊ ተቋማት ጋር ጠንካራ ውይይት ለማድረግ ጠቃሚ ጉባኤ ነው።»
ያም ብቻ አይደለም። እንደ ሚንስትር ዴኤታው ከኾነ፦ «እንዲህ ያሉ ፕሮጄክቶችን አፍሪቃውያን ለብቻቸው ማስቀጠል አይችሉም። ከጀርመን እና ሌሎች ሐብታም የምእራቡ ዓለም ሃገራትም የገንዘብ ድጋፍ ያሻቸዋል።»
የኃይል አቅርቦት ቀውስ ውስጥ የገባው አውሮጳ በዋናነት ከአፍሪቃ 10 ሚሊዮን ቶን ታዳሽ የሐይድሮጂን ኃይል ለማስገባት ባለፈው ወር ውሳኔ አሳልፏል። ኢትዮጵያ በገፍ ካላት የከረሠ-ምድር ውኃ የሀይድሮጂን ኃይል ለማምረት እና ከገንዘብ ደጋፊዎች ጋር ለመደራደር ተስፋ መሰነቋም ተገልጧል። የከርሰ-ምድር ውኃ እና የጋዝ ክምችቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን እና ሌሎች አካባቢዎች በከፍተኛ መጠን እንዳለ ይነገራል።
የአፍሪቃ ኅብረት የኃይል እና የመሠረተ-ልማት ኮሚሽነር፦ አቡ ዛይድ አውሮጳ የኃይል አቅርቦት ረሐቡን ለማስታገስ ከአፍሪቃ ጋር ጠንካራ አጋርነት እንደሚያሻው አስረግጠው ተናግረዋል።
«ሁላችንም ዋስትናችን እስካልተረጋገጠ ድረስ አውሮጳ አስተማማኝ ዋስትና አይኖራትም። የአውሮጳ ዋስትና አሁን ስለ ጦር መሣሪያ አይደለም። ስለ ነዳጅ ድፍድፍ፣ የኃይል አቅርቦት እና ስለ ምግብ ነው። ስለዚህ፦ ሁላችንም ዋስትናችን እና ደኅንነታችን እስካልተረጋገጠ ድረስ አውሮጳ ውስጥ ማንም ዋስትናው ሊረጋገጥ አይችልም።»
የአፍሪቃ የኃይል ምክር ቤት (AEC) የጀርመን አፍሪቃ አጋርነትን ለማሳለጥ የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት ነው። አፍሪቃ እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2030 ከኃይል ድህነት ለመላቀቅ የፈጠራ እና የተቀናጀ መፍትኄዎች ያሿታል ሲል አጽንኦት ሰጥቷል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እምቅ የከርሠ ምድር ሐብቶቿን አምርቶ ወደ ገበያ ለማቅረብ አጋዥ የሚኾኑ የሰለጠኑ ባለሞያዎችን ከወዲሁ ማፍራት ይጠበቅባታል። ወጣቶቿም በምዕራቡ ዓለም ዩኒቨርሲቲዎች እና ተቋማት የዚህን ለአውሮጳ አንገብጋቢ የሆነውን የኃይል ምንጭ ምንነት እና ጥቅም በጥልቀት መመርመር ያሻቸዋል።
አፍሪቃ አንድ ጆንያ ሙሉ የካካዋ ጥሬ ምርት ልካ ባገኘችው የውጭ ምንዛሪ አንዲት ፍሬ ያለቀላት የቸኮሌት ብስኩትን ብቻ መግዛት አይነት ያልተመጣጠነ ንግድን መቀየር ያሻታል። ያን ለማድረግ አሁን አውሮጳ ከሚሻው የኃይል ምንጭ ምን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንችላለን የሚለው ላይ እጅግ ማስተዋል ያስፈልጋል። አውሮጳ እና አፍሪቃ የጋራ ተጠቃሚ የሚኾኑበትን መንገድ ማመቻቸትም ጥቅሙ ለሁለቱም ነውና።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ኢሳቅ ሙጋቤ
እሸቴ በቀለ