1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክአፍሪቃ

ነፃ የምክር አገልግሎት በስልክ

ዓርብ፣ መጋቢት 30 2014

ጃፓን በሚገኝ አንድ የሕፃናት እና ወጣቶች ማዕከል ውስጥ ስልክ የሚደውሉት ሰዎች ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ በሰው ኃይል ብቻ ደዋዮቹን ለማስተናገድ ከባድ ሆኖባቸዋል። ለዚህም በቴክኒዎሎጂ አማካኝነት ሰው ሠራሽ ዕውቀትን (Artificial intelligence) ተጠቅመው ችግሩን ለማቃለል እየሞከሩ ነው።  ምን ያህል ስኬታማ ሆነው ይሆን?

https://p.dw.com/p/49ewG
Äthiopien Alegnta Hotline
ምስል Alegnta

በሰሜን ምሥራቅ ቶኪዮ ኢዶጋዋ አውራጃ "Heart Port" የተባለ የልጆች ምክር መስጫ ማዕከል ይገኛል።  ማዕከሉ ውስጥ የሚሠሩት ሰዎች እጅጉን በሥራ ተጠምደዋል ትላለች ቦታውን በአካል ተገኝታ የጎበኘችው የዶይቸ ቬለ ባልደተባ ካትሪን ኤርድማን። ወደ ማዕከሉ በቀን 500 ያህል ጊዜ ስልክ ይደወላል። ካለፈው የካቲት ወር አንስቶ ግን የስልክ ጥሪዎቹን ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በቴክኒዊሎጂ አማካኝነት ሰው ሰራሽ ዕውቀትን ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም እንደሚመለሱ የማዕከሉ ኃላፊ ካኦሪ ኮውሳካ ይናገራሉ። "አገልግሎቱ ሁለት ልዩ ባህሪዎች አሉት። አንደኛው እያንዳንዱ ንግግር ቃል በቃል ይመዘግባል። ስለዚህ ስልኩን የሚመልሰው ሰው ምንም ነገር መፃፍ አይጠበቅበትም።  ሁለተኛው ደግሞ ተቆጣጣሪው በቀጥታ ጠረቤዛው ላይ ሆኖ ከኮምፒተሩ ላይ ማንበብ ይችላል."

ከሙከራ ፕሮጀክቱ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን አግኝተናል ይላሉ ሌላኛው የማዕከሉ ሠራተኛ ቶሞያ ያኮሃማ "በጣም ከባድ የሆነ ሁኔታ ካለ ለምሳሌ በልጆች ላይ ጥቃት ደርሶ ከሆነ፤ ሠራተኛው ከደዋዩ ጋር መነጋገር ይችላል ። ሌሎች ደግሞ ልጁ የት እንደሚኖር እና ስለ ቤተሰቡ ሁኔታ በተመሳሳይ ጊዜ ለማወቅ መሞከር ይችላሉ።»

ፕሮጀክቱ እንደ «ፖሊስ»፣ «የቤት ውስጥ ጥቃት » የሚሉ አንዳንድ ቁልፍ ቃላትን ሲሰማ የሠራተኞቹ ኮምፒውተር ላይ ቀይ እንደሚያበራ የማይከሉ ኃላፊ ኩውሳካ በመግለፅ ማሽኑ እንዴት እንደሚሰራ ያብራራሉ። «ማስጠንቀቂያው ኮምፒውተሩ ላይ ብልጭ ድርግም ይላል፣ ተቆጣጣሪውም ወዲያውኑ ይህን ያያል፡ ያኔም ቅድሚያ የሚሰጠው ስልክ እንዳለ ስለሚረዳ ማንበብ ይጀምራል።»

ባለፈው አመት የጃፓን ፖሊስ ከ100,000 በላይ  ለአደጋ የተጋለጡ የሕጻናት ጉዳዮችን መዝግቧል። ከነዚህ መካከል 80 በመቶ ያህሉ ቸልተኝነት ወይም ስድብ የመሳሰሉ የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። የማዕከሉ ኃላፊ ኮውሳካ እንደሚሉት የኮቪድ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት የሚደውሉላቸው ልጆች ቁጥር ቀንሶ ነበር። «ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ብዙ ጉዳዮች ችላ እንደተባሉ እና በተመሳሳይ ጊዜ ወላጆቻቸው ሁል ጊዜ በዙሪያቸው ስለነበሩ ለችግር የተጋለጡ ልጆች ምክር እና እርዳታ ለማግኘት በጣም ከባድ እንደነበር እንገምታለን።»

Künstliche Intelligenz
ምስል Andrew Ostrovsky/PantherMedia/Imago

ንግግሮቹን ወደ ጽሑፍ መገልበጥ አንዱ የሙከራ ፕሮጀክቱ አካል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ልጆቹ ተጨማሪ እንክብካቤ ያስፈልጋቸው እንደሆነ መወሰን ነው። ይህም የ 20, 000 ሰዎች ጉዳዮችን በወስሰድ ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሯል። «የዚህ የሙከራ ፕሮጀክቱ ዋና አላማ ሰው ሠራሽ እውቀትን ተጠቅሞ  ልጆቹ ተጨማሪ እንክብካቤ እና ድጋፍ ያስፈልጋቸው እንደሆነ መወሰን ነው።»

ለዚህም ነባር ጉዳዮችን መሠረት አድርጎ ኮምፒውተሩ ሃሳብ ያቀርባል። ኃላፊዋ እንደሚሉት ከሆነ የብዙዎች ገጠመኝ እና አካሄድ ተመሳሳይ ነው።  ምንም እንኳን ስርዓቱ ውሱንነት ቢኖረውም  ጃፓናውያኑ የመጀመሪያውን ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝተውታል። «ሰው ሠራሽ እውቀት መጠቀም ብቃት ያለው ረዳት መሣሪያ ሆኖ አግኝተነዋል። 20,000 ያህል ጉዳዮች አሉን ። ማንም ሰው እነዚህን ሁሉ በጭንቅላቱ ሊይዝ አይችልም። ነገር ግን አርቴፊሻል እንተሌጀንስ ትልቅ እውቀቱን በማካፈል ሊረዳ ይችላል።»

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጊዜ ይቆጥባል። ይህም ተጨማሪ ጊዜ ልጆቹን ለመምከር እና ለመርዳት ሊውል ይቻላል።» ይላሉ ጃፓናዊዋ የፕሮጀክቱ ኃላፊ ካውሳካ። ኢትዮጵያ ውስጥስ እንደዚህ አይነት አገልግሎቶች እንዴት ይሰጣሉ? የሰው ሠራሽ ዕውቀት አማራጭ ይሆን ይሆን? « አለኝታ» ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ እንደዚህ አይነት አገልግሎት ሰጪዎች አንዱ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሴታዊት የተሰኘው ንቅናቄም አካል ነው። «ጾታን መሰረት ላደረገ ጥቃት ነጻ የስልክ መስመር አገልግሎት ይሰጣል።»  ትላለች የፕሮጀክቱ ኃላፊ ፌቨን ይግረመው። « በደንብ አገልግሎቱን ስለማናስተዋውቅ በተዘጋጀንበት መጠን አይደወልልንም።» ይህም ውድ ስለሆነ እንደሆነ ፌቨን ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች።   6388 ነፃ አገልግሎት የሚሰጡበት ስልክ ቁጥር ሲሆን ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል አንስቶ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ አራት አማካሪዎች ይሰራሉ» የምትለው ፌቬን « ሰዎች ቢደውሉ ስልክ እንመልሳለን» ትላለች።

Äthiopien Alegnta Hotline
ምስል Alegnta

« አለኝታ» ለጊዜው በሰው ኃይል ሊመለሱ የሚችሉ የስልክ ጥሪዎችን ይቀበላል። መረጃን በተመለከተም ጉዳዮ በሚደውሉት እና የምክር አገልግሎት በሚሰጡት ሰዎች መካከል ስለሚቀር ብዙ መረጃ አንሰበስብም ትላለች ፌቨን። ይህም ሚስጥር ለመጠበቅ ሲባል ነው።  «ሕፃናትን ጨምሮ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ይደውሉልናል» የምትለው ፌቨን አብዛኛው ሰው ግን ማንነቱ እየታወቀ በግልፅ ማውራት እንደማይፈልግ ተረድታለች። ታድያ በግልፅ ማንነታቸውን ለሌላ ሰው ለመናገር ለማይደፍሩ ሰዎች አርቴፊሻል ኢንቴሌጄንስ አማራጭ ይሆናቸው ይሆን? ተቀባይነቱስ? የሳይኮሎጂ ባለሙያ የሆነችው ፌቨን በእንዲህ አይነት የምክር አገልግሎት ላይ ሰው ሠራሽ ዕውቀት መጠቀም ጥሩ ነው ብላ አታምንም። ምክንያት የምትለው « ያ ሰው ስለሚናገረው ነገር አብሮ ሊሰማ፣ ሊታዘን ይገባል። እና ከሰው ጋር ሲያወሩ የበለጠ ለመናገር ፍቃደኛ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ።» 

ጃፓን ውስጥ ሰው ሠራሽ ዕውቀትን (Artificial intelligence) በመጠቀም እንዴት አንድ የልጆች ምክር መስጫ ማዕከል ውስጥ ሥራ ማቃለል እንደተቻለ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ጾታን መሰረት ላደረገ ጥቃት ነጻ የስልክ መስመር ስለሚሰጠው «አለኝታ» ፕሮጀክት የቃኘው የወጣቶች ዓለም ዝግጅትን በድምፅ  ያገኛሉ። 

ካትሪን ኤርድማን /ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ