1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ለናምቢያ የመለሰችዉ ቅርስና ዉዝግቡ 

ረቡዕ፣ የካቲት 27 2011

በቅኝ ግዛት ዘመን ከናሚቢያ የተዘረፉ ቅርሶችን ጀርመን  መመለሷን የባደን ቩተንበርግ ፌደራል ግዛት አስታወቋል። ከመቶ ዓመታት በላይ በሽቱትጋርት ቤተመዘክር መቆየቱ የተነገረው መጽሐፍ ቅዱስ እና አለንጋ በጎርጎሪዮሳዊው 1893 ዓ/ም  ከናሚቢያ የተዘረፈ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3ELaQ
Präsentation von Raub-Kulturgütern Hendrik Witbooi
ምስል picture-alliance/dpa/M. Murat

የተመለሰው የናሚቢያ መጽሐፍ ቅዱስ እና አለንጋ


ጀርመን የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ከነበረችው ናሚቢያ የወሰደችውን መጽሐፍ ቅዱስ እና አለንጋ ከአንድ ክፍለ-ዘመን በኋላ መልሳለች። ቅርሶቹ የናሚቢያ ጀግና የሚባሉት ሄነሪክ ዊትቦይ ነበሩ።
ደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ናሚቢያ ከጎርጎሮሳዉያኑ ከ1884 እስከ 1919 ድረስ በጀርመን ቅኝ ግዛት ስር የቆየች ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት  100 ሺህ የሚደርሱ ናምቢያዉያን ለነፃነት ባደረጉት ተጋድሎ መገደላቸዉ ይነገራል።
በወቅቱም በናሚቢያ ሄነሪክ ዊትቦይ የተባሉ የሀገሬዉ ተወላጅ  የናማ ጎሳዎችን ፤ ሳሙኤል ማሃሬድ የሄሬሬ ጎሳዎችን በመምራት በጀርመን ቅኝ ገዢዎች ላይ አምፀዋል። 
በእነዚህ  ናሚቢያ የነፃነት ታጋዮችና በቅኝ ገዢዎቹ መካከልም ዋተርበርግ በተባለ ቦታ ጦርነት ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ጦርነት የተሸነፉት ናሚቢያዉያን በመሆናቸዉ ብዙዎቹ  ናሚቢያ ዉስጥ አማሂክ በተባለ  በረሃ በአንድ ማጎሪያ ዉስጥ እንዲታሰሩ ተደርገዋል። እዚያም በዉሃ ጥምና በረሃብ ብዙዎቹ ሞተዋል። 
ይህንን ዕልቂት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1985 የ20ኛዉ  ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዉ የዘር ማጥፋት ብሎ ፈርጆታል። የጀርመን መንግስትም ለዚህ የታሪክ ጠባሳ ዕዉቅና በመስጠት  ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ  በናሚቢያ የዘር ማጥፋት መፈፀሙን አምኖ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።ጀርመን ዕልቂቱን አምና ለመቀበልና ይቅርታ ለመጠየቅ ዘግይታለች የሚሉ ናሚቢያዉያን የመኖራቸዉን ያህል ችግሩ በተከሰተባት በናሚቢያም ቢሆን ትኩረት የተነፈገዉ መሆኑን የናማ ጎሳዎች ማህበር ሊቀመንበር ላዛሪዝ ካራቢቦ ይናገራሉ።
"እስካሁን ድረስ  በናሚቢያ ስርአተ ትምህርት እና በናሚቢያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የዘር ማጥፋት ታሪክ በጣም በትንሹ  ነው የተካተተዉ። ያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ጫና ያለበት ነዉ። እናም በናሚቢያ ያ ታሪክ  ለምን ችላ እንደተባለ ተከታታይ ዉይይቶች አሉ። ይኽ ታሪክ እንዴት መያዝ እንዳለበት ናሚቢያ የራሷ ፍልስፍና እና አቋም የሌላት ያስመስላል።  
በናሚቢያ በቅኝ ግዛት ወቅት ተፈፀመ ከሚባለዉ ዕልቂት በተጨማሪም የሟቶቹ የመገልገያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶች በቅኝ ገዢዎቹ ከሀገሪቱ መዘረፋቸዉ ይነገራል።ከነዚህ ቅርሶች መካከል ከመቶ ዓመታት በላይ በጀርመን ሀገር  ሽቱትጋርት ቤተመዘክር የቆዩ ሁለት ቅርሶች ያለፈዉ ሐሙስ በጎርጎሮሳዉያኑ የካቲት 28 ቀን 2019 ዓ.ም ለናሚቢያ መመለሱን የባደንቩተንበርግ  ፌደራል ግዛት  ገልጿል።
የተመለሰው የናሚቢያ ቅርስ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጀግና እና የናማ ጎሳ መሪ የነበሩት የሄንሪክ ዊትቦይ መጽሐፍ ቅዱስ እና አለንጋ ሲሆኑ፤ በጎርጎሪዮሳዊው 1893 ዓ.ም  ተዘርፈው ለቤተ መዘክሩ በ1902 ዓ.ም በስጦታ የተበረከቱ ናቸው። ከዚህ አኳያ ቅርሱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠዉ ነዉ ይላሉ የአፍሪቃ ቤተ-መዘክር ኃላፊ ሳንድራ ፍራዉከር
«የቅርሱ መመለስ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠዉ ነዉ። ምክንያቱም ሄነሪ ዊትቦይ በናምቢያ በምሳሌነት የሚታይ ብሄራዊ ጀግና ነዉ። እናም ከዚህ በኋላ ከሀገር በቀል አጋሮቻቻን ጋር መነጋገር እንጀምራለን።»
ሄነሪክ ዊትቦይ በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅኝ ገዥዎች የተጠመቁ ናምቢያዊ ሚሲዮናዊ ክርስቲያን ቢሆኑም፤ በኋላ ላይ ግን የጀርመን ቅኝ አገዛዝን በመቃወም ትግል ያካሄዱና በተለይም በናማ ጎሳዎች ዘንድ በአርአያነት ይታዩ የነበሩ ሰዉ ናቸዉ። በዚህ ትግል ወቅትም በ1905 በቅኝ ገዢ ወታደሮች ተገድለዋል። የእኚህ ሰዉ የግል መገልገያ ቁሳቁሶች እንዲመለሱም የናሚቢያ መንግስት ለዓመታት ጀርመንን ሲጠይቅ ቆይቶ የተፈቀደ ቢሆንም። 
የቅርሶቹን መመለስ በተመለከተ ናሚቢያ ከጀርመን መንግስት ጋር ስምምነት ባደረገበች ወቅት ቁሳቁሶቹ የግል መገልገያ ከመሆናቸዉ ጋር ተያይዞ ለማን ይሰጡ የሚለዉ ጉዳይ  ከፍተኛ ዉዝግብ አስከትሏል። ጉዳዩ በናሚቢያዉያን መካከልም ልዩነት ፈጥሯል። አንዳንዶቹ በቀጥታ ለሚመለከታቸዉ አካላት ይሰጥ ሲሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሐሳቡን ይቃወሙታል።
የናሚቢያ ፕሬዝዳንት ሃጅ ጃይንጎብ ቅርሶቹ በቪትቦይ የትዉልድ ስፍራ ቤተመዘክር ተሰርቶላቸዉ እስኪገቡ ድረስ በሀገሪቱ ብሄራዊ ቤተ መዘክር ይቆያሉ ቢሉም ሁሉንም የናማ ጎሳ አባላት የሚያስማማ አልሆነም።በጀርመን ሀገር የሽቱትጋርት ህገመንግስት ፍርድቤት ጉዳዩን ዉድቅ አደረገዉ እንጅ በተለይም የናማ ጎሳ መሪዎች ማህበር  በህጋዊ መንገድ የቅርሶቹን መመለስ ለማሳገድ ሞክሮ ነበር።  የናማ ጎሳ መሪዎች ፀሐፊ ላዛሪዛ ካራቢቦ ቅርሱ በማይመለከታቸዉ አካላት ዕጅ ነዉ ባይ ናቸዉ።
«ቁሳቁሶቹ የግለሰብ ንብረቶች ናቸዉ።የመንግስት ንብረት ቢሆን ኖሮ ቤተክርስቲያን ወይም ለቤተሰብ ይሰጥ ነበር። ቤተሰብም ምን እንደሚደረግ ይወስን ነበር። ነገር ግን እዚህ ነገሮችን የምንሰማዉ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ግንኙነት ወይም ፍላጎት በሌላቸዉና በማይመለከታቸዉ ሰዎች ነዉ።»
ፒተር ካታያቪቪ የተባሉ የናሚቢያ ባለስልጣን ግን ትችቱን አይቀበሉትም።እንዲያዉም በጉዳዩ ሁሉም ናሚቢያዉያን ሊሳተፉ ይገባል ይላሉ።
«የዚህ እንቅስቃሴ ምልከታ ወይንም ፍላጎት ላይ ቀና የሆነ ቁጥብነት ኖሮ ሊኾን ይችላል። እስከማዉቀዉ ድረስ መንግሥት በሩን ክፍት አድርጎ ነዉ የቆየዉ። የዚህ ስምምነት አካል ያልሆኑ ናሚቢያዉያን ሁሉ በጉዳዩ ሊሳተፉ እንደሚገባቸው ሊያምኑበት ይገባል ምክንያቱም መጨረሻ ላይ ጥቅሙ የጥቂት ሰዎች ብቻ አይደለምና።»ብለዋል።
ቅርሶቹ የ120 ዓመት ዕድሜ ያላቸዉ  ሲሆን፤ በቅኝ ግዛት ወቅት ተዘርፈዉ በሽቱትጋርት ቤተ መዘክር  ከተቀመጡ  ቁሳቁሶች  መካከል ሲመለስ ይህ የመጀመሪያዉ ነዉ።ይህ የጀርመን ርምጃ ያለፈዉን የታሪክ ጠባሳ ባያጠፋዉም ወደ ዕርቅ የሚወስድ ነዉ ተብሏል። የባደን ቡተርግ ግዛት የሳይንስ ሚንስትር ተሬዛ ባወር በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግርም
«የቅኝ ግዛት ታሪክን ወደኋላ መልሰን እንዳልተደረገ ማድረግ ባንችልም በእርቅ ሂደቱ ውስጥ አንድ ጠቃሚ እርምጃ  በመዉሰድ ኃላፊነታችንን ግን እንወጣለን» ብለዋል።
የርክክብ ሥነስርዓቱም የናሚቢያ መሥራች አባት የሚባሉት ሳም ኒዮማን ጨምሮ ሦስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በተገኙበት ተፈጽሟል።
የጀርመን መንግስትም ቅርሶቹን ከመመለስ ባሻገር  በናሚቢያ የሚገኙ የምርምር ተቋማት እና ቤተመዘክሮች በጋራ ለሚሰሩት ሥራ  የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል። 

Deutschland Rückgabe sterblicher Überreste aus Deutscher Kolonialzeit
ምስል picture-alliance/AA/A. Hosbas
Hendrik Witbooi
ምስል picture-alliance/akg-images

 

ፀሀይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ