1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ንግድአፍሪቃ

የ2023 የጀርመን አፍሪቃ ንግድና ኤክስፖ

ማክሰኞ፣ የካቲት 21 2015

https://p.dw.com/p/4O4Pg
Äthiopien Addis Abeba | Deutsche Botschaft PK zu Made in Germany Africa Expo 2023
ምስል Seyoum Getu/DW

መድረኩ ከየካቲት 23-25 ቀን ድረስ ይቆያል ተብሏል

«ሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪቃ» የተሰኘውና በርካታ አምራቾች እና ነጋዴዎችን ያገናኛል የተባለው መድረክ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው ። የአዲስ አበባ የአፍሪቃ የፖለቲካ ማዕከልነትን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ተሰናዳ የተባለው ይህ የንግድ መድረክ በንግዱ ዘርፍ ቁልፍ ለሆኑ የአፍሪቃ ኢንዱስትሪዎች መድረክ ለመስጠት አልሞ የተዘጋጀም ነው ተብሏል ፡፡ ከፊታችን ሐሙስ የካቲት 23  ጀምሮ እስከ የካቲት 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. የተሰናዳው ይህ መድረክ በአፍሪቃ ምድር ትልቁ የጀርመን ዝግጅት ነው ተብሏልም ። 

ከ2 ሺህ 500 በላይ ጀርመናውያን እና የአፍሪካ ባለሙያዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ ዲፕሎማት እና የመንግስት አካላት በመታደም የንግድ ትስስሮችን ያጠናክሩበታል የተባለው ሜድ ኢን ጀርመኒ መድረክ ለአፍሪካ ገበያ በልዩነት የተዘጋጁ ታዋቂ ምርቶች፣ የምርት መለያዎች እና አገልግሎቶች የሚለዋወጡበት ነው ተብሏል፡፡ በርካታ ጎብኚዎች እና ውሳኔ ሰጪ አካላት የሚታቀፉበት ነው የተባለው ዝግጅቱ ከንግድ ባዛር ጎብኚዎች በተጨማሪ የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች እና ዲፕሎማቶችንም አካቶ እንደሚካሄድ ነው የተገለጸው፡፡ ሁነቱን አስመልክቶ አዘጋጆች ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መድረኩ በአይነቱ የተለየና ግዙፉም ነው ብለዋል፡፡

Äthiopien Addis Abeba | Deutsche Botschaft PK zu Made in Germany Africa Expo 2023
«ሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪቃ» የተሰኘውና በርካታ አምራቾች እና ነጋዴዎችን ያገናኛል የተባለው መድረክምስል Seyoum Getu/DW

ስክንድር ነጋሲ የንግድ ትርዒት አማካሪና የዚህ መድረክ አስተባባሪ ናቸው፡፡  “በአፍሪካ አሁን ላይ ወደ መካከለኛ ገቢ እያደጉ ያሉ ሰዎች መበራከታቸው መሰል ሁኔቶችን ለማዘጋጀት ጊዜው ነው ያስብላል፡፡ አፍሪቃ አሁን የተሻለ ከፍ ያለ ምርትና አገልግሎት ያሻታል፡፡ ይህ ፍላጎት የጀርመን ምርት ላይ በተለይ ከፍ ማለቱ የዚህ አይነቱን መድረክ እንድናሰናዳ ገፋፍቶናል፡፡ የዚህ መድረክ ዋና ሃሳብ ንግድ ማከናወን ሳይሆን የጀርምንና አፍሪካ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ ነው፡፡ ጀርመን በንግዱ ተሳትፎ በአፍሪካ የነበራትን ለስላሳ እርምጃም ለመቀየር ያለመ ነው፡፡ የአፍሪካውያን የጀርመን ምርት ፍላጎት ማደግ እና የጀርመን መንግስትም ትኩረት ለአፍሪካ ከባለፈው ሁኔታ አሁን መጠንከሩ ስለ ሁኔቱ እንድናስብ ገፋፋን፡፡ የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል በመሆኗ ለሁነቱ በተመረጠች ኢትዮጵያ የፊታችን ሓሙስ ከአፍሪካ የሚመጡ ተወካዮች ከከፍተኛ የጀርመን ልዑካን ጋር ይገናኛሉ” ሲሉም የሁነቱን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡

ሓሙስ የሚከፈተው የ2023ቱ የጀርመን-አፍሪካ ንግድና ኤክስፖ አዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ከጀርመን ንግድ ሚኒስቴር፣ አከባቢ ጥበቃ እና የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ከጀርመን ባደን ቩትበርግ (Baden-Württemberg) እና ባቫሪያ (Bavaria) ግዛቶች ጋር በትብብር ያዘጋጁት ነው ያሉት ደግሞ በኤምባሲው የኢኮኖሚ፣ ባህል እና ፕሬስ ክፍል ዋና ፀሃፊ ኦኑል የል ናቸው ፡፡

Äthiopien Addis Abeba | Deutsche Botschaft PK zu Made in Germany Africa Expo 2023
«ሜድ ኢን ጀርመኒ-አፍሪቃ» ስለተሰኘው መድረክ በጀርመን ኤምባሲ ገለጣምስል Seyoum Getu/DW

“ይህ ሁነት ለቁልፍ የአፍሪካ ኢንደስትሪዎች እና ዘርፈ ብዙ ግንኑነቶች መነሻ የሚሆን ነው ፡፡ ከበርካታ አገራት የመጡ ተሳታፊዎችን የሚያገናኘው ኤክስፖ እና የፓነል ውይቶችም የጀርመን-አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ የ2023 የአፍሪካ ፋይናንስ፣ የባቫሪያ የአፍሪካ ተሳትፎ የአፍሪካ ነጻ ኢኮኖሚያዊ ቀጠና እድልና ተግዳሮቶቹ በሚሉና በሌሎችም ርዕሶች ሃሳብ ይለዋወጣሉ፡፡ ከ2 ሺህ 500 በላይ የጀርምን እና አፍሪካ ዲፐሎማቶች፣ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች የሚታደሙበት መድረኩ አብይ የግንኑነት ነጥቦች ላይ ለመምከር የተለየ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ በተጨማሪም የጀርምን እና አፍሪካ ተወካዮቹ በትምህርት ላይም ሃሳብ ይለዋወጣሉ ፡፡ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የከተማ ንጽህና፣ ስነህንጻ እና አከባቢ ጥበቃ ብሎም በዲጂታላዘሽን እና የማሽነሪዎች አምራች ስራ ላይ የተሰማሩ የጀርመን ኩባንያዎች ተወካዮችም የዚህ መድረክ ተሳታፊ ሆነው ልምዳቸውን ያጋራሉ፡፡ እንደ ግብርና ላሉ ድጋፍ የሚሆን ፋይንናንስን በተመለከተም ከዓለም ባንክ (WB) እና ከዓላመቀፉ የንዘብ ፈንድ (IMF) ጋርም ውይይት ይደረጋል፡፡ የጀርመን ሕግጋት ላይም ለኢትዮጵያ እና አፍሪካውያን ባለሞያዎች ገለጻ ይደረጋል ፡፡ በጀርመን በግዙፍ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ተምሳሌት የሆኑ ሁለቱ የጀርመን ግዛቶች ባደን ቩትበርግ (Baden-Württemberg) እና ባቫሪያ (Bavaria) ተወካዮች ሁነቱን ለማድመቅ አዲስ አበባ ይገኛሉ” በማለት ትኩረት ስላገኘው መድረክ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ እስጥፋኖስ ሳሙኤል ደግሞ ዘላንድ የተሰኘው የጀርመን ኢኮኖሚ ግዙፍ ባለድርሻ ክልል የሚሰኘውን ባደን ቩትበርግ - የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ተወካይ ናቸው፡፡ እንደሳቸውም ገለጻ ይህ መድረክ ለጀርመን ኩባንያዎች የአፍሪካ ተሳትፎ ልዩ ምእራፍ የሚከፍት እና ለንግድ ድርጅቶች የላቀ እድል ሚፈጥር ነው፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ