የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር የስልጣን መልቀቅያ ማመልከቻ አስገቡ
ሰኞ፣ ጥር 8 2015
የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ስልጣን መልቀቅ እንደሚፈልጉ አስታወቁ። የጀርመን ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ SPD ፖለቲከኛ ክሪስቲነ ላምብሬሽት ከስልጣን መልቀቅ እንደሚፈልጉ ያስታወቁት በፅሁፍ ለመራሔ መንግሥት ቢሮ ባስገቡት ማመልከቻ መሆኑ ታዉቋል። የ 65 ዓመትዋ የጀመርን መከላከያ ሚንስትር በማመልከቻቸዉ ፤ጠቅላይ ሚኒስትር ኦላቭ ሾልዝ ከተሾሙበት የመከላከያ ሚኒስትርነት ሥልጣን እንዲያነስዋቸዉ ጠይቀዋል።
የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ፖለቲከኛዋ «መገናኛ ብዙኃን ለወራቶች በእኔነቴ ላይ በሚያወጡዋቸዉ ዘገቦች የተነሳ፤ የዜጎችን ፍላጎት ያላማከለ ግን ስለሃገሪቱ ወታደሮች እና ጦር ሠራዊት ብሎም የፀጥታ ጉዳይ እየተነሳ በመሆኑ» ከስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸዉን በምክንያትነት ለጀርመን መራሔ መንግሥት ቢሮ በፃፉት የሥልጣን መልቀቅያ ማመልከቻ ገልፀዋል። የጀርመንዋ መከላከያ ሚኒስትር በማመልከቻቸዉ ላይ በመቀጠል፤ በመከላከያ ሚንስትር ስር የሚገኙ ደኅንነታችን ለማስጠበቅ ሌት ተቀን እየሰረሩ ያሉትን ሁሉ አመሰግናለሁ ለወደፊቱም ጥሩ መልካም እንዲገጥማቸዉ እመኛለሁ ብለዋል ። በጎርጎረሳዉያኑ 2021 ዓ.ም መጨረሻ የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ሆነዉ የተሾሙት እና ዛሬ በገዛ ፈቃዳቸዉ የስልጣን መልቀቅያ ያስገቡትን ክሪስቲነ ላምብሬሽትን ቦታ የሚተካ የሁለት ሦስት ሴቶች ስም በወሬ ደረጃ ይሰማ እንጂ፤ እስካሁን አዲስ ስለሚተኩትም ይሁኑ በገዛ ፈቃዳቸዉ ስልጣን ለመልቀቅ ማመልከቻ ስላስገቡት መከላከያ ሚኒስትር ጉዳይ ከጀርመን መራሔ መንግሥት ቢሮ የተሰማ ነገር የለም።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ