የመምህራን እጥረት በጀርመን
ማክሰኞ፣ ጥር 23 2015በአሁኑ ጊዜ የጀርመን የትምህርት ስርዓት ትልቅ ፈተና ገጥሞታል። የጀርመን ትምህርት ቤቶች በአስርሺህዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ መምህራን ያስፈልጓቸዋል።ችግሩን ለመፍታት አስተማሪዎችን ከውጭ የመቅጠር እቅድ ቢኖርም ቢሮክራሲው ጥረቱን ወደ ኃላ በመጎተት ይተቻል። አሁን አሁን በሀብታምዋ ሀገር በጀርመን እድሳት የተነፈጉ፣ ግድግዳቸው የተጎዳ እና መጸዳጃዎቻቸው የተሰባበሩ ትምህርት ቤቶችን ማየት የተለመደ ሆኗል የሚለው የዶቼቬለው የራልፍ ቦደን ዘገባ ለእድሳት ተብሎ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም ያነሳል።ብዙዎቹ ዋይ ፋይ እንደሌላቸው የኮምፕዩተሮች እጥረት እንዳለም ይገልጻል። የትምህርት ጉዳዮች ተመራማሪዎች ፣ የጀርመን የትምህርት ስርዓት ለዚህን መሰሉ ችግር የተዳረገው በትክክለኛው መንገድ ባለመተዳደሩና በደካማ እቅድ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከዚህ ቀደሙ የላቀ ቁጥር ያላቸው የውጭ ተማሪዎች ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲዋሀዱ መርዳት የሚጠበቅባቸው ትምህርት ቤቶች አዲስ ፈተና ውስጥ ይገኛሉ። ችግሩ ተጨማሪ ፈተና ሆኖባቸዋል።ስለ ችግሩ አስተያየታቸውን ከተጠየቁ የትምህርት ቤቶች ሃላፊዎች አብዛኛዎቹ እንደተናገሩት የመምህራን እጥረት በጣም ትልቁ ፈተና ነው።በሮበርት ቦሽ ተቋም ተመራማሪ ዳግማር ቮልፍ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ በጀርመን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ መምህራን እጥረት አለ።
«በአሁኑ ጊዜ ከ30 ሺህ እስከ 40ሺህ መምህራን እጥረት አለ።»
በ16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች የትምህርት ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው ግን በሀገሪቱ አለ የተባለው የመምህራን እጥረት በሮበርት ቦሽ ተቋም ከተባለው ዝቅ ያለ ነው። ስብሰባው እጥረቱን 12 ሺህ ነው ያለው። የጀርመን መምህራን ማኅበር እንደሚለው ችግሩ አሁን የተከሰተ ሳይሆን ረዥም ጊዜ አስቆጥሯል። የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሃይንዝ ፔተር ማይዲንገር
„የማስጠንቀቂያ ደውሎች መሰማት ከጀመሩ ብዙ ጊዜያት ተቆጥረዋል።በጀርመን የመምህራን እጥረት ከተከሰተ 10 ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁን ግን ጎልቶ የሚታይና እጅግ የከፋም ሆኗል።በዚህ ስራ ላይ ለብዙ ዓመታት ቆይቻለሁ።በአሁኑ ጊዜ ያለው ከዛሬ 50 ዓመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ነው ከፍተኛ የመምህራን እጥረት ነው።በእርግጥም ይህ አንድ ነገር ነው ማለት ይቻላል።»
የሮበርት ቦሽ ተቋም ካለፈው ጥቅምት እስከ ህዳር ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት 1055 የትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎችን ስለ ችግሩ አነጋግሮ ነበር። ከትምህርት ቤቶች ሃላፊዎች 67 በመቶው የመምህራን እጥረት ከባድ ፈተና ሆኖብናል ብለዋል። ከመካከላቸው 22 በመቶው በትምህርት ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ገቢራዊነት አዝጋሚ መሆንን እንደ ችግር አንስተዋል። 21 በመቶው የቢሮክራሲው መንዛዛት ሌላ ችግር መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን 20 በመቶው የመምህራን እጥረት ስራችን ላይ ጫና አድርጎብናል ብለዋል።
አሁን ለተከሰተው ከፍተኛ የመምህራን እጥረት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ የጀርመን መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ማይዲንገር ይናገራሉ።እርሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳን የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም ለመምህርነት የሚሰለጥኑት ባለሞያዎች ቁጥር ካለፉት 20ና 30 ዓመታት ወዲህ በእጅጉ እየቀነሰ መሄዱ አንዱ መንስኤ ነው። የመምህራን የስራ ዋስትናም እንደ ቀድሞው የተጠበቀ አለመሆኑ አሁን የከፋ ሁኔታ ላይ ለሚገኘው የመምህራን እጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል።
«አንዱ ምክንያት ፖለቲካው ነው። ባለፉት 12 ዓመታት የወሊድ መጠን እየጨመረ የሄደ ቢሆንም ፖለቲካው በጣም ዘግይቶ ለጉዳዩ ትኩረት የሰጠው። የዚህ ውጤት ደግሞ አሁን እየታየ ነው። በዚህ ወቅት ለመምህራን ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያዎች ሲወጡ አልነበረም።በሁለተኛ ደረጃ ከለፉት 20 እስከ 30 ዓመታት ድረስ የመምህራን ማሰልጠኛዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ተደርጓል።በዚህ የተነሳም በመምህርነት የሰለጠኑት ቁጥር በጣም ጥቂት ነው። ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ በአንድ ዓመት ብቻ ጀርመን ከገቡት የዩክሬን ስደተኞች ውስጥ 200 ሺሁ ህጻናት ናቸው። አዎ ትምሕርት ቤቶች ለዚህ ምንም ዝግጅት አላደረጉም ነበር።»
በጀርመን ሕግ እድሜያቸው ከ6 ዓመት እስከ 16 ዓመት የሆኑ ልጆች መማር አለባቸው። የጀርመን የኤኮኖሚ ተቋም እንደገመተው 7.5 ሚሊዮን ይሆናሉ ከሚባሉት የዩክሬን ህጻናት 3.5 በመቶ የሚሆኑት እንኳን ጀርመን የሚገቡ ከሆነ ሀገሪቱ 13 ሺህ አምስት መቶ ተጨማሪ መምህራን ያስፈልጓታል። የአሁኑ የመምህራን እጥረት ብቻ ሳይሆን የወደፊቱም እጅግ አሳሳቢ መሆኑ ነው ከወዲህ የሚነገረው።እስከ ጎርጎሮሳዊው 2030 ችግሩ ሊባባስ ይችላል የሚል ግምት አለ።በተለይ የትምህርት ጉዳዮች አዋቂው ቮልፍ እንደሚሉት አሁን ስራ ላይ ላይ የሚገኙት በ1960ዎቹ የተወለዱ መምህራን ጡረታ ሲወጡ በጀርመን የመምህራን እጥረት ይበልጥ ይባባሳል የሚል ስጋት አለ።
«በዘርፉ ይበልጥ ታዋቂ የሆኑት ተመራማሪው ክላውስ ክሌመን ያሉትን ብንከታተል በጎርጎሮሳዊው 2030 ከ80 ሺህ በላይ መምህራን የሚፈለጉባቸው ክፍት የስራ ቦታዎች ይኖራሉ ።እዚህ ላይ እጅግ አንገብጋቢ እርምጃ መውሰድ ይገባል። የመምህራን እጥረት ብቻ ሳይሆን ህጻናት በመደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲታቀፉ የወጣውን አካታች ፖሊሲ ለመተግበር የሚያስፈልጉት የማኅበራዊ ጉዳዮች ሠራተኞች፣የስነ ልቦና አገልግሎት ሰጭዎች እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞችም እጥረትም ያጋጥማል ።»
በአሁኑ ጊዜ ከጀርመን ተማሪዎች ሰባት በመቶ ብቻ ናቸው መምህር ለመሆን የሚሰለጥኑት ።ከመካከላቸው የተወሰኑት ከጊዜ በኋላ ይህን አቋርጠው ሌላ የትምህርት ዘርፍ ሊቀይሩ ይችላሉ ።ታዲያ ወጣቶች በመምህርነት ሞያ እንዲሰማሩ እንዴት መበረታታት አለባቸው? ከጀርመን ፌደራል ግዛቶች አንዳንዶቹ ችግሩን ለመፍታት ፉክክር ላይ ናቸው። ምሥራቅ ጀርመን የሚገኘው የብራንደንቡርግ ግዛት ከዚህ ቀደም ያልነበረ የስራ ዋስትና ለመስጠት ተጨማሪ ቃል ገብቷል።ግዛቱ መምህራን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ የመንግስት ሰራተኝነት ደረጃ ይሰጣቸዋል ብሏል።
ሜዲንገር በዚህ ረገድ የአንዳንድ የጀርመን ፌደራል ግዛቶችን ተሞክሮ አካፍለዋል።
«የባይረን ግዛትን እንደምሳሌ ብንወስድ የግዛቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርኩስ ዞደር በሚቀጥለው ዓመት በተቻለ መጠን በርካታ አስተማሪዎችን ከሌሎች ግዛቶች የመመልመል እቅድ አላቸው። »
ባለጸጋው የደቡብ ጀርመኑ ግዛት ባቫሪያ ከሌሎች ግዛቶች ለሚመጡ መምህራን ድጎማ ለመስጠትና የመምህራንን ደሞዝ ሊያሳድግ አቅዷል። ሜዲንገር ግን መምህራን ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም የሚፈልጉት ይልቁንም ዋናው ስራቸው ላይ ማተኮር እንጂ ብለዋል። በሌሎች ተጨማሪ ስራዎችና ፕሮጀክቶች ላይ መጠመድም አይገባቸውም ይላሉ ይሁንና በማኅበራቸው ትዝብት የስራ ባልደረቦቻቸው ከማስተማሩ ጎን ለጎን ተጨማሪ ስራዎች ይሰጧቸዋል። ከመካከላቸውለመጻህፍት መግዣ የሚውል ገንዘብ ማሰባሰብ ፣ ከትምህርት ቤት ውጭ የሚካሄዱ የተማሪዎች ጉዞዎችን ማዘጋጀት እና ሌሎች ሃላፊነቶች እና ፕሮጀክቶችን መስራትም ይኖርባቸዋል።
ለችግሩ መፍትሄ እንዲጠቁም የጀርመን ፌደራል ግዛቶች ሚኒስትሮች ጉባኤ የሰየመው ኮሚሽን ካቀረባቸው ሃሳቦች ውስጥ መምህራን ጡረታ የሚወጡበትን ጊዜ እንዲያራዝሙ ማበረታታት ፣ተጨማሪ ሰዓታት እንዲሰሩ መፍቀድ የመማሪያ ክፍሎች ማስፋት እና በረዳትነት ሊሰሩ የሚችሉ ተመራቂ ተማሪዎችን መቅጠር የሚሉት ይገኙበታል።ጉባኤው በትርፍ ጊዜ ማስተማር እንዲገደብም ይፈልጋል። ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ከመምህራን 49 በመቶው የትርፍ ጊዜ ሰራተኞች ናቸው። የሰራተኛ ማኅበራት ግን ሃሳቦቹን ውድቅ አድርገዋል። ጀርመን አሁን በጣም የሚያስፈልጓት የሂሳብ የኬሚስትሪ የፊዚክስ የሙዚቃና የስነ ጥበብ መምህራን ናቸው።የትምህርትና የሳይንስ ሰራተኞች ማኅበር በቅርቡ የመምህራንን የስራ ጫና ለመቀነስ ተጨማሪ የአስተዳደርና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሊጂ ባለሞያዎች እንዲመደቡ በቅርቡ ጠይቋል። ከውጭ ለሚመጡ መምህራን የሚሰጠውን እውቅና ማፋጠንም በመፍትሄነት ተቀምጧል። ቮልፍ እንደሚሉት ግን ፍላጎቱ ቢኖርም እንዲህ በቀላሉ የሚሳካ አይሆንም
«በመሰረቱ ከውጭ የሚመጡ መምህራን በጀርመን ባለው እውቅና በማግኘት ሂደት ቢሮክራሲ ምክንያት በመምህርነት እውቅና የማግኘት እድላቸው አነስተኛ ነው።መምህርነት ቁጥጥር የሚደረግበት ሞያ ነው።ወደ ስራው መግባት የሚቻለው በህጉ መሰረት በሚካሄድ የሞያዊ እውቅና አሰጣጥ ደንብ መሰረት ነው።ይህ አንዱ ነው።ከፌደራሊዝም ጋር የተያያዘው ችግር ደግሞ የፌደራል ግዛቶች እውቅና አሰጣጥን በተመለከተ ተመሳይ ደንቦች የሏቸውም። ከውጪ ዲግሪ ያላቸው መምህራን ጀርመን ውስጥ በመምህርነት የመስራት ፍላጎት አላቸው። ሆኖም በጣም በጣም ጥቂቶች ናቸው የሚሳካላቸው።የዚህም ምክንያቱ በስርዓቱ ውስጥ ያለው ቢሮክራሲ ነው። »
በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ውስጥ ከሚያስተምሩ የውጭ ዜጎች አብዛኛዎቹ ከአውሮጳ ሀገራት የመጡ ናቸው። ከነዚህ ከጎረቤት ፈረንሳይ የሆኑት ቁጥር ከፍተኛ ነው።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ