የደም ክምችት እጥረትን ለመቅረፍ የሚሠሩ ወጣቶች
ዓርብ፣ ኅዳር 17 2014ባለፈው ጥቅምት ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ባንክ ክምችት እጥረት እንዳጋጠመው በመግለፅ ሰዎች ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርቧል። የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን የደም ክምችቱን እጥረት ለማስወገድ በተለያዩ ሦስት ከተሞች የሚገኙና የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ወጣት በጎ ፈቃደኞች ናቸው። ሰላማዊት ዮሴፍ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ስትሆን ደም መለገስ ከጀመረች 10 ዓመት ያህል ሆናት። « 2004 የካምፓስ ተማሪ ሳለሁ ነው። ደም ባንኮች ግቢ መጥተው ተማሪዎችን የደም እጥረት አለ ብለው ሲያስተባብሩ ነው።» ሰላማዊት ከቅርብ አመታት አንስቶ ከ ሶስት እስከ አራት ጊዜ ደም ትለግሳለች።
ቃዲ ዐደም ሀጂ የጅማ ከተማ ነዋሪ ነው። ወጣቱ ደም ልገሳ የጀመረው የ 11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ሲሆን ከዛን ጊዜ አንስቶ ፍቃደኝነቱን አላቋረጠም። ይህም ለሌሎች ወጣቶች አርዓያ ተብሎ ተሸላሚ ለመሆን አብቅቶታል። አሁን በጅማ ከተማ የቀይ መስቀል ምክትል ኃላፊ ነው። « በዓመት አራት ጊዜ እየለገስኩኝ 75ኛ ጊዜዬን መስከረም 24 ቀን 2014 አክብሬያለሁ። በአጠቃላይ የኦሮሚያ ክልል ሞዴል ተብዬ ዋንጫ እና የምስክር ወረቀትም ተሸልሜያለሁ። » ቃዲ ባለሁት 18 ዓመታት ከ 2000 በላይ ወጣቶች ደም እንዲለግሡ ቅስቀሳ እንዳደረገም ለዶይቸ ቬለ DW ገልጿል። ደም ለመለገስ በጎ ፍቃደኝነት ብቻ መሆን በቂ አይደለም። ወጣቶቹ 18 ዓመት የሞላቸው እና ክብደታቸውም ቢያንስ 45 ኪሎ መሆን ይኖርበታል። ከዚህም ሌላ ጤናማ መሆን እና ከተላላፊ በሽታ ነፃ መሆን ያስፈልጋል። በአንድ ጊዜ ልገሳም የሶስት ሰዎችን ህይወት መታደግ እንደሚቻል ቃዲ ይናገራል። የደም እጥረት እንዲከሰት የሚያደርጉ «በርካት ምክንያቶች አሉ» የሚለው ቃዲ በዋና ምክንያትነት የሚጠቅሰው በሀገሪቱ ለተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች መዋሉን የሚያመለክት ነው። ከዚህ ባሻገር ደግሞ በሀገሪቱ የሚካሄደው ጦርነት የራሱ አስተዋፅዎ አድርጓል ይላል። « ለመኪና አደጋ፣ ለበርካታ ቀዶ ህክምና አገልግሎቶች ደም ያስፈልጋል። ለካንሰር ህክምና ለአንድ ሰው 8 ወይም 9 ዩኒት ደም ያስፈልጋል።
ሰሚራ ዑመር የሻሸመኔ ከተማ ደም ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናት። የ33 ዓመቷ ወጣት ለደም ባንኩ መስራት ከጀመረች ሦስት ዓመት ሆናት። በሻሸመኔ ያለው የደም ማሰባሰብ ሥራ በምን መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ ገልፃልናለች። « በብዛት ከ 18 እስከ 24 ዓመት ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለጋሾች አሉን። እነሱም በብዛት ተማሪዎች ናቸው። » ትላለች። በጅማ ከተማ የቀይ መስቀል ምክትል ኃላፊ ሆኖ የሚሠራው ቃዲም በከተማዋ የደም ልገሳ ማስተባበሩ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ይላል ። « በቀበሌ ደረጃ በትምህርት ቤቶች፤ በግልም በመንግሥትም ዮንቨርስቲዎች በጅማ ጥሩ መነቃቃት አለ።» የሚለው ቃዲ በርካታ በአመራር ላይ ያሉ ሰዎች ጭምር ደም እየለገሱ እንደሆኑ ይናገራል። ይሁንና ቀጣይነት እንዲኖረው ሰዎች አስታውሰው በየሶስት ወሩ ደም እንዲለግሱ ይመክራል። «በወጣቱ ዘንድ ስለ ደም ልገሳ ያለው ግንዛቤ የተለያየ ነው» የምትለው ሰላማዊት በሀዋሳ ከተማ ያለው የደም ማሰባሰብ ሥራ ካለው የደም ፍላጎት አንፃር ከዚህም በላይ ከፍ እንዲል ታሳስባለች። « የደም ፍላጎት እና የሚሰጠው ሰው ቁጥር ሀዋሳ ከተማ ውስጥ አይመጣጠንም» የምትለው ሰላማዊት አንድ ሰው ደም ሲሰጥ የሚወሰደው አንድ ዮኒት ደም ወይም 300 ml ወይም የአንድ የሚሪንዳ ጠርሙስ እንደሆነ ትገልፃለች።
የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳሬክተር አቶ ያረጋል ባንቴ ለዶይቸ ቬለ DW እንደገለፁት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ መደበኛ ህክምና ለመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ በወር ቢያንስ 30 000 ገደማ ሰው ደም መለገስ ይኖርበታል። ይህም የደም ልገሳ ባለፈው መስከረም ወር ላይ በመቀዛቀዙ የደም ባንክ ክምችቱ እጥረት ገጥሞት ነበር። « ረጅም ጊዜ መቀመጥ የማይችል ነገር ላይ እጥረቶች የተለመዱ ነው። ከዚህም ሌላ መስከረም ወር ላይ ደም የለገሱ ሰዎች ቁጥር 19600 ያህል ነው። ይህም ማለት በመደበኛ ህክምና ከሚያስፈልገን ቢያንስ በ10 ሺ ያነሰ ነው።» አቶ ያረጋል በምክንያትነት የጠቀሱት የደም ለጋሾች ቁጥር መቀነስ እንጂ የሚያስፈልገው መጠን በመጨሩ አይደለም ሲሉም አስረድተዋል። «የነሀሴ ወር ላይ በጣም በርካታ ሰዎች ደም በመለገሳቸው ቀጥሎ ያሉት ሁለት ወራት ላይ አዳዲስ ሰዎች ካልሆኑ በቀር እነዚያ ሰዎች ደም መለገስ ስለማይችሉ ማለት ነው።» አቶ ያረጋል አክለውም አንድ ሰው ደም ከለገሠ ጊዜ አንስቶ ታካሚው ጋር እስኪደርስ 35 ቀናት ያህል እድሜ ብቻ እንዳለው እና አንድ ሳምንት የሚያክል ጊዜው በተለያዩ ምርመራዎች እና ትራንስፖርት እንደሚጠፋ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ