የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን ይዞታ የቃኘው ውይይት
ሐሙስ፣ የካቲት 16 2015የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀንን የአሠራር እና የአዘጋገብ ዳሰሳ እንደዚሁም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን የግጭት አገናዛቢ አርትኦት ፖሊሲዎች እና አተገባበራቸው በሚል ርዕስ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች አዲስ አበባ ላይ ቀርበዋል። በየመብቶች እና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል አማካኝነት ለውይይት የቀረቡት ሁለቱ ጥናታዊ ጽሑፎችም በዘርፉ ባለሙያዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ላለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሁኔታን የቃኘ «ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የግጭት አገናዛቢ አርትኦት ፖሊሲዎች እና አተገባበራቸው» የሚል የመነሻ ጥናት እና «የግጭት አገናዛቢ አዘጋገብ ዳሰሳ በኢትዮጵያ» በሚመለከት ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች በየመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከከል አማካኝነት ለውይይት ቀርበዋል። ትናንት ይፋ በሆኑት በእነኝህ ሁለት ጽሑፎች አማካኝነትም ባለፍት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ የነበረችበትን ምህዳር በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙኃን ተግዳሮት እንደዚሁም ተቋሞቹ ከአድማጮች ተመልካቾቻቸው ጋር በምን መልኩ ደርሰዋል የሚለውን በስፋት ለመዳሰስ ሙከራ አድርጓል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የዓለም የፕረስ ቀንን በምድሯ ያከበረችው ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እየታሠሩ፣ የህትመት ውጤቶች እየመነመኑ እና ሚዛኑን የጠበቀ መገናኛ ብዙኃን ማየት እየቸገረ የመምጣቱን ምክንያት ምን እንደሆነ አቶ ፍቃዱ ሀይሉ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ኃላፊ ተናግረዋል።
በጥናቱ እስካሁን ወደ 60 የሚሆኑ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ሁለት ጋዜጠኞች ሕይወታቸው ማለፉ ተመልክቷል። «ጋዜጠኞች አንዱን ወገን ካልያዙ መሥራት በተቸገሩበት ወቅት ሚዛናዊ ሆኖ መሥራት ፍፁም አስቸጋሪ ሆንዋል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ አወቃቀር ካልተስተካከለ በቀር» ሲሉ ለዶቼ ቬለ/ DW/ የገጹት ደግሞ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ናቸው።
በውይይቱ ላይም የኢትዮጵያ መገንኛ ብዙኃን ከ2018 በኋላ ምን ይመስላል የሚለው ምልከታ ወደ ፊት ምን መደረግ እንዳለበት ለመነጋገር እና መፍትሄ ለመፈለግ ምክንያት ይሆናል ነው የተባለው። በኢትዮጵያ ያሉትን 117 የመገናኛ ብዙኃንን የሥራ እና የአዘጋገብ ሁኔታ በስፋት የዳሰሰው ጥናታዊ የጽሑፍ አቅራቢዎች ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ ሞገስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሁኔታ አቶ ወንድወሰን ንጉሤ «የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የግጭት አገናዛቢ አርትኦት ፖሊሲዎችና አተገባበራቸው» በሚል ባቀረቧቸው ጽሑፎች ከመድረኩ ተወያዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።
ሃና ደምሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ