የአፍሪቃ ውስጥ ጉዞዎች
ዓርብ፣ የካቲት 1 2011በአፍሪቃ አህጉር ከሚኖረዉ ሦስት አራተኛ ያህሉ ህዝብ ወጣት ወይም ከ 35 ዓመት በታች ነው ተብሎ ይገመታል። ስለሆነም ይህ ዝግጅት የወጣቶችን ጉዳይ ነዉ የሚዳስሰዉ። አፍሪቃ ውስጥ መጓዝ በርካታ ፈተናዎች አሉት። ከፈተናዎቹ አንዱ እንደ ልብ ከአንድ ሀገር ወደሌላኛው መንቀሳቀስ አለመቻል ነው። ስለሆነም ቪዛ መጠየቅ ያስፈልጋል። አንድ ጋናዊ ለምሳሌ 27 የአፍሪቃ ሀገራትን ያለ ቪዛ መጎብኘት ወይም መዳረሻ ላይ ቪዛ ጠይቆ ማግኘት ይችላል። አንድ ደቡብ ሱዳናዊ ደግሞ ወደ 48 የአፍሪቃ ሀገራት ለመጓዝ ቪዛ ያስፈልገዋል። ሌላው ደግሞ ቪዛ መጠየቅ ቢቻልም የግድ እያንዳንዱ ጠያቂ ያገኛል ማለት አለመሆኑ ነዉ። በዚሁ ጉዳይ ላይ የናይጄሪያዊ ወጣቶች « ቪዛ ለማግኘት በጣም አድካሚ ነው ቪዛ የሚያስፈልግበት ቦታ ለመጓዝ ከታቀደበት ጊዜ ብዙ ቀደም ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። » « ናይጄሪያ ሙሰኛ እንድትሆን ነው የዳረጓት። አብዛኞቹ ሀገራት ወደ እኛ መምጣት አይፈልጉም። ምክንያቱም ሰዎቻቸውን ሙስና እናስተምርባቸዋለን። ከዛም እነሱ ሀገራቸው ሄደው ሌሎችን ያስተምራሉ ብለው ያምናሉ። በዚህም ምክንያት እኛም እንድንመጣ አይፈልጉም።» ይላሉ።
ሌላው በአህጉሩ ከሚኖሩ አፍሪቃውያን ይልቅ ከሌላ አህጉር የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች ቅድሚያ ሲሰጣቸው ይታያል።ደቡብ አፍሪቃ ለምሳሌ ለሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ገደቦች ሲኖሯት ከአውሮጳ ፤ ከአሜሪካ ወይም ከአውስትራሊያ የሚጓዙትን በደስታ ትቀበላለች። ከኬፕታውን እስከ ካይሮ ድንበር እያቋረጠች አገር የጎበኘችው መስከረም ኃይሌም ይህንን ታዝባለች። «የካናዳ ፓስፖርት ስለነበረኝ ድንበር ላይ አላንገላቱኝም።» ሌላው መስከረም በጉዞዋ የታዘበችው ነገር በአፍሪቃውያኑ ዘንድ ራሱ ጥቁር አገር ጎብኝዎች ብዙም አለመለመዳቸው ነው።
የገንዘብ አቅሙ ኖሮት ለሚጓዝ 115 ደሴቶች ያሏት ሲሸልስ ብቸኛዋ ቪዛ የማትጠይቅ አፍሪቃዊት ሀገር ናት። ይህም በምዕራባዊያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃውያንም ዘንድ ተመራጭ የእረፍት ሀገር አድርጓታል። ሩዋንዳ ፣ጋና እና ቤኒንም ለሌሎች አፍሪካውያን የቪዛ መስፈርቶቻቸውን ቀንሰዋል። ሁሉንም የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራትን ያካተተ ባይሆንም ለሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ እና ኬንያ በጋራ የሚያገለግል የምስራቅ አፍሪቃ የቱሪስት ቪዛ መጠየቅ ይቻላል።
የምስራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት የሆኑት ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ በጋራ የሚገለገሉበት የምስራቅ አፍሪቃ ፓስፖርት እንዲኖራቸው መስማማታቸው ይታወሳል። ይህንንም አዲስ ኤሎክትሮኒክስ ፓስፖርት አብዛኞች ሀገራት ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።
ሌላው ደግሞ እኢአ በ 2016 ዓ,ም የተጀመረው እና በዓለም ዙሪያ እኢአ በ 2020 ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የአፍሪቃ ህብረት ሀገራት የጋራ ፖስፖርት ነው። ይህም ንግድን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል። ከቪዛ ባሻገር ደግሞ አፍሪቃ ውስጥ መጓጓዝን ከባድ የሚያደርገው ውድ መሆኑ ነው።
አሰፋ ወንዳያ ከኢትዮጵያ፦ በጣም አስቸጋሪ ነው ለምሳሌ እኔ ካለሁበት ወልድያ ጅቡቲ እና ሰሜን ሡዳን ቅርብ ናቸው። ግን በቀላሉ አየር ቀይሬ ልመለሥ ብል በጣም ከባድ ነው።
ጊካሽ ሞሽን ከኬንያ ፦ የአፍሪቃ መሪዎች ላላ ማለት እና በወረቀት ላይ መፈረም ብቻ ሳይሆን በተግባርም አንድ መሆን አለባቸው። እውነቱን ተናገር ብትሉኝ ግን ይህ በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ብዬ አልገምትም። ስለዚህ መሪዎቻችን ይሰሙን ዘንድ ድምፃችንን ከፍ ማድረግ ያለብን እኛ 77 ከመቶ የምንሆነው ወጣቶቹ ነን።
ኢብራሂም ጃሎ ከጋምቢያ፦የዚህ አህጉር ሰዎች ተጋፍጠን ያለነው በአሁኑ ሰዓት ብዙ ነው። በአፍሪቃ ህብረት አማካኝነት ሁሉም ሰዎች በነጻነት ሊንቀሳቀሱ እና ሊሰሩ ይገባል።
ያህያ ባድዬ፦ የ አፍሪቃ ህብረት አመራሮች ደካሞች ናቸው። ለራሳቸው ህዝብ ፍላጎት ሳይሆን ለራሳቸው ነው የሚጥሩት ። ለአፍሪቃ አንድነት ነው መፍትሄው። አፍሪቃ ከባሪያነት ተላቃ ራሷን ነፃ ማውጣት አለባት።
ተሾመ አበራ ከ ጅዳ ፦ የማወራው ያየሁትን የሀገሬን ነው። ከመታወቂያ እስከ ቪዛ አድካሚነቱ እንዳለ ሆኖ የሚበተነው ገንዘብ እጅግ በጣም ያስመርራል
ኤማ ታዚስ ፦ ከለንደን ብራስልስ በ 50 ዩሮ በረራ አለ። ከካሜሮን ኪጋሊ ለመጓዝ ግን 540 ዩሮ ነው ሲል አስተያየት ሰጥቷል። ናይጄሪያዊው ሶሎሞን ኤኮ እና ኬናዊቷ ትሬሲ ካሩኪ በዚህ የዶይቸ ቬለ DW አካዳሚ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። አፍሪቃ ውስጥ ጉዞ ለምን እንደዚህ ተወደደ ሰለሞን?« መጀመሪያ የጉዞውን አይነት መለየት አለብን። ለስራ፣ ለመዝናናት ወይስ ዘመድ ጥየቃ ብለን። በአጠቃላይ ግን አፍሪቃ ውስጥ በርካታ ምክንያቶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓዝ በጣም ከባድ ያደርጉታል። አንዱ የፖሊሲ ችግር ነው። ይህም ብዙ አፍሪቃውያን እንዳይጓዙ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያት ይመስለኛል። ሌላው የኢኮኖሚ ችግር ነው። »
ትሬሲ ለአፍሪቃ ትልቁን ነገር የምንፈልግ ከሆነ ለሁሉም ሰዎች ተደራሽ እንዲሆን መጣር ማስፈለጉን ትናገራለች። በዚህም ስትል ትሬሲ የአውሮጳ አገሮች አንድነትና አብሮነት የሚገለጽበት «የሸንገን ቪዛ» በምሳሌነት ትጠቅሳለች» አውሮጳ ውስጥ ሁሉም ሀገራት ኢኮኖሚያቸው ተመሳሳይ አይደለም። ግን በሸንገን አካባቢዎች ያለ ምንም ችግር 26 ወይም 28 ሀገራት መጓጓዝ ይቻላል። ስለዚህ ማህበረሰቡን የምናጠናክርበት ንቅናቄ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ናይጄሪያ ላይ ወይም ቶጎ በጤናው ዘርፍ ላይ ብዙ የሰው ኃይል ካለ ለምን ኬንያ ላይ መስራት እንደማይችሉ ምክንያቱ አይገባኝም። ስለዚህ አህጉራችንም እኛም ባለን አቅም ትርፋማ ልንሆን እንችላለን። ለምሳሌ የአፍሪቃ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው። አብዛኞቹም ወጣቶች ነን። ስለዚህ ይህንን ገደብ እራሳችን ላይ የምንጥል ከሆነ መቼም ተግባራዊ አናደርገውም።»
ይሁንና መሻሻል እየታየነው ይላል በየሳምንቱ ለስራ ከምስራቅ ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚመላለሰው አበበ ግርማዬ ከዚህ ቀደም ይገጥሙት የነበሩትን ፈተናዎች እያስታወሰ። « ቪዛ መጠየቅ አለ። አፍሪቃ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ የቢጫ ወባ ካርድ ያስፈልጋል። የቀጣይ በረራዎችም ብዙም አልተስፋፉም። የኢትዮጵያን ፓስፖርት ይዞ መጓዝ ብዙ ፈተናዎች አሉ። ይሁንና ብዙ መሻሻያዎችን እያየሁ ነው። »
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ