የአፍሪቃ መሪዎች ተሰበሰቡ፣ አዉሩ ተለያዩ
ሰኞ፣ ጥር 30 2014ዳካር-ድፍን ሴናጋል በአፍሪቃ እግር ኳስ ግጥሚያ ድል ቦረቀች።የሙዩካ የቡያና መንደር-ግዛቷን አመፅ ደብቃ የእግር ኳስ እንግዶችዋን ለማስተናገድ ጠብ እርግፍ ስትል የሰነበችዉ ያዉንዴ ዋንጫዉን ወደ ዳካር ሸኝች። አዲስ አበባም የበረሐሌን በረሐ፣ የቄሌምን ጫካ የሚያረክስ ደሟን የቦረና-ኦጋዴን አሸዋን የሚያነድ ድርቋን ሸፋፍና በአፍሪቃ ቀለማት፣ ለአፍሪቃ አሸብርቃ፣ የአፍሪቃ መሪዎችን አስተናግዳ፣ የአፍሪቃ አንድነትን አርማ ለዳካሮች አስረክባ በድምፃዊቷ አገላለፅ «ሥራ አለ እንደገና አለች።» ዛሬ።የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ መነሻ፣የኢትዮጵያ መስተንግዶ ማጣቃሻ፣ የአፍሪቃ እዉነት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
ለሴኔጋሎች ድርብ ድል ዓይነት ነዉ ዛሬ።የእግር ኳስ ቡድናቸዉ የአፍሪቃን ዋንጫ ተሸልሞ፣ ከያዉንዴ፣ፕሬዝደንታቸዉ የአፍሪቃ ሕብረትን የሊቀመንበር ሥልጣን «ተሾመዉ» ከአዲስ አበባ፣ ዳካር ገቡ።ማኪ ሳል ብልጥ ናቸዉ።አንደበተ ርቱዕ፣ ደግሞም ተግባቢ፣ ቁጡ-ደግሞም ፈገግተኛ ፖለቲከኛ።በዙር የሚደርሰዉን የአፍሪቃ ሕብረትን የሊቀመንበርነት ሥልጣን በተረከቡ ማግስት ትናንት «ሕገ-መንግስትን የጣሰ የስልጣን ነጠቃን ለማስወገድ የአፍሪቃ ሕብረት ጠንካራ ርምጃ መዉሰድ አለበት» አሉ።
«ሥለዚሕ፣ በኔ አስተያየት ሕገ-መንግስትን የጣሳ የስልጣን መቋረጥን ለማስወገድ የአፍሪቃ ሕብረት አበክሮ መስራት፣ከእስካሁኑ የበለጠ በጣም ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት።(መፈንቅለ መንግስት) አድራጊዎችና እነሱ የሚመሯቸዉ ሐገራት በማዕቀብ መቀጣት አለባቸዉ።»
ያዉንዴ ላይ የተተከለዉ የሴኔጋል ሕዝብ አይንና ጆሮ የመሪዉን ንግግር ሊያድመጥ፣ እድምታዉን ሊያስተነትን ቀርቶ የመሪዉን ጉዞ ዓላማም በቅጡ አያዉቅም ነበር።ሰዉዬዉ ጮሌ ናቸዉ።ከአዲስ አበባ ዳካር ሲገቡ የሕዝባቸዉን ስሜት-ስሜታቸዉ አስመስለዉ የአንድ ቀን ብሔራዊ ፌስታ አዉጀዉ ላፍታም ቢሆን ከሕዝባቸዉ ተቀየጡ።በሕዝባቸዉ ታወሱም።
የዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበሩበት ዘመን እንደ አባታቸዉ ሁሉ ሶሻሊስታዊ መርሕን አቀንቃኝ፣ የማርክሲስት-ሌኒኒስት አስተምሕሮን አፍቃሪ ነበሩ።አብዛኛዉ ዓለም ማርኪሲዝምን በቃኝ-ሲል፣ በቃኝ ብለዉ የሴኔጋልን ገዢ ፓርቲ ተቀላቀሉ።
ሲመቻቸዉ የቀድሞ አለቆቻቸዉ ታማኝ፣ ታዛዥ፣ አገልጋይ ሆነዉ ከፋቲክ ከተማ ከንቲባነት ወደ ነዳጅ ድርጅት ስራ-አስኪያጅነት፣ ከማዕድን ሚንስትርነት ወደ ጠቅላይ ሚንስትርነት፣ ከምክር ቤት እንደራሴነት ወደ አፈ-ጉባኤነት ሲያድጉ-ሲመነጉ ዓመታት አስቆጠሩ።
የአለቆቻቸዉ በተለይ የፕሬዝደንት አብዱላሒ ዋዴ ትዕዛዝ ሲቆረቁራቸዉ ተቃዋሚ አደራጅተዉ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ተቆጣጠሩ።2012 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)። ጠቅላይ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን ብቻ 1.3 ቢሊዮን (CFA) መዝረፋቸዉ የተረጋገጠዉም ያኔ ነዉ።ሳል ባለፈዉ ዕሁድ መፈንቅለ መንግስት አድርጊዎችን ሕገ-መንግስትን በመጣስ ወነጀሉ።እሳቸዉ ያኔ ያን ያክል ገዘብ የዘረፉት የሴኔጋል ሕገ-መንግስት ፈቅዶላቸዉ ይሆን? አናዉቅም።
የምናዉቀዉ አዲስ አበባ ላይ ለሁለት ቀን የተሰበሰቡት የአፍሪቃ መሪዎች፣ ሳል እንዳሉት ለመፈንቅለ መንግስት አድራጊዎች ምሕረት እንደሌላቸዉ መወሰናቸዉን ነዉ።ISS በሚል የእንግሊዝኛ ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ አንዴይ አሳሞሐ፣«ዉሳኔዉ የሚጠበቅ ነበር ይላሉ።» ችግሩን ማስወገድ ግን አይችልም።
«ጉባኤዉ ይሕን እንደሚያደርግ በጣም ስንጠብቅ ነበር።ይሁንና ዉሳኔዎች ብቻቸዉን ችግሩን አያስወግዱትም።ዉሳኔዉን ገቢራዊ ለማድረግ ጠንካራ እርምጃዎች ሊከተሉ ይገባል።ከዚሕ ቀደም ዉሳኔዎች ሲደረጉ አይተናል።ገቢራዊ ሲሆኑ ግን ብዙ አላየንም።»
የዉሳኔ ነገር።የአፍሪቃ ሕብረት ወላጅ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት 50ኛ ዓመት በ2013 ሲዘከር፣ የአፍሪቃ መሪዎች አጀንዳ 2063 ያሉትን የሐምሳ ዓመት መርሕ አፅድቀዉ ነበር።መርሑ ከያዛቸዉ ወርቅ ወርቅ ሐሳቦች አንዱ «የጠመንጃዉ ላንቃን ማዝጋት» የሚለዉ ዕቅድ ነበር።በዕቅዱ መሠረት ብዙ ሐገራትን የሚያወድመዉን ጦርነት፣ግጭት፣የነፍጥ አመፅና ግድያዎችን እስከ 2020 መቆም ነበረባቸዉ።
በአፍሪቃ ሕብረት የሠላምና የፀጥታ ኮሚሽን ሥር ዉሳኔዉን እንዲያፅፈፅም የተሰየመዉ ግብረ-ኃይል የበላይ የነበሩት አምባሳደር ራምታነ ላማምራ ያኔ እንዳሉት ግጭትና ጦርነት ካልቆመ አፍሪቃ ስለ-ዕድገት ብልፅግና ልታስብ አትችልም።
«የአፍሪቃ መሪዎች የጠመንጃዉን ላንቃ ማዘጋት ካልቻሉ፣ ለአሐጉሪቱ የሚነድፏቸዉ ትላልቅ ፕሮጄክቶች ሁሉ ዉጤታቸዉ ባዶ ወይም በጣም ትንሽ መሆኑን ተረድተዋል።»
ዘንድሮ 2020ም 2021ድም አልፈዉ 2022 ሁለተኛ ወሩን ይዟል።አፍሪቃም ከሊቢያ እስከ ሞዛምቢክ፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ እስከ ናጄሪያ፣ ከማሊ እስከ ሶማሊያ፣ ከቡርኪናፋሶ እስከ ቻድ፣ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እስከ ኢትዮጵያ ብዙ ስም በተሰጣቸዉ አማፅያንና በየመንግስታቱ ጦር ዉጊያ ተመሰቃቅለዋል።
አፍሪቃ ዉስጥ የሠፈረዉ ከ20 የሚበልጡ የአዉሮጳና የአሜሪካ ሐገራት ጦር «ጠላት» የሚለዉን እየገደለ ይገደላል።ማሊና ቡርኪና ፋሶ ዉስጥ በቀጥታ፣ ቻድ ዉስጥ በተዘዋዋሪ የተደረጉት መፈንቅለ መንግስታት ዋና ምክንያት በየሐገራቱ ከሸመቁ ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር የሚደረገዉ ዉጊያ ያስከተለዉ ዉድቀት ነዉ።
የአዲስ አበባ ጉባኤተኞች ያለፈ ዉሳኔያቸዉ ክሽፈት፣ ያመራራቸዉ ዉድቀትን አጋላጭ ስለሆነ ክሽፈት-ዉድቀቱን እንዳልሆነ-ሸፋፍነዉ ሕዝባቸዉን ባዳዲስ ዉሳኔ አንበሻብሸዉ ወደየመጡበት ሔዱ።አዲስ አበባም የዛሬ ስምንት ዓመቱን፣ ያዉም ከወረቅት ያላለፈዉን፣ ያዉም የድፍን አፍሪቃ ዉሳኔን መዘንጋት አይደለም የራስዋን ጉድ፣ጉድፍ፣ነዉር በአብለጭላጭ ጌጥ ደብቃ ትናንትን ለረሱት እንግዶችዋ ሰለሞን ሙጬ እንደታዘበዉ፣ አሸብርቃ ነበር።
አዲስ አበባ ለትላልቅ እንግዶቿ ክብር «ስትብለጨለጭ» ከአብአላ እስከ በረሐሌ የሚገኙ የአፋር ከተሞችና መንደሮች እየጋዩ ነዉ።ከአካባቢዉ የሚወጡ ዘገቦች እንደጠቆሙት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በአፋር ክልል ላይ አዲስ በከፈተዉ ጥቃት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።300 ሺሕ ሕዝብ ተፈናቅሏል።
ሕወሓት የአማራና የአፋር ክልሎችን ለቅቆ መዉጣቱን ካወጀ በኋላ፣ መሪዉ የስማ በለዉ ድርድር መጀመሩን ለዓለም እያስታወቁ፣ የአፍሪቃ-አሜሪካ ዲፕሎማቶች ለሽምግልና በሚራወጡበት መሐል አፋር እንዲሞት፣ እንዲፈናቀል፣ እንዲሰደድ የተፈረደበት ምክንያት በርግጥ ለብዙዎች አሳዛኝ ግራ አጋቢም ነዉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ለጉባኤተኞች ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ግን 15 ወራት ያስቆጠረዉ ጦርነት ሕግ-የማስከበር ባሕሪ ያለዉ ነዉ።
«የኢትዮጵያ ፈተና በተፈጥሮዉ ዉስጣዊ እና ሕግና ሥርዓት የማስከበር ጉዳይ ነዉ።ይሁንና የዉጪ ተዋንያን ጣልቃ በመግባታቸዉ ምክንያት የዉስጥ ጉዳያችንን መፍታቱ ሲበዛ ከባድ ሆኗል።በዚሕ ፈታኝ ወቅት ላደረጋችሁልን ድጋፍ፣ ትብብርና ችግራችንን በመገንዘባችሁ በዚሕ አጋጣሚ ሁላችሁንም ላመሰግን አዉዳለሁ።»
ኢትዮጵያ፣ ከሰሜኑ ጦርነት በተጨማሪ ወለጋ፣በኒ ሻንጉል፣ ጋምቤላና ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በጎሳ ግጭት፣ በሽፍቶች ጥቃትና ዘረፋ ብዙ ሰዎች ይገደሉ፣ይፈናቀሉ፣ ይዘረፉባታል።ቦረናና ኦጋዴንን የመታዉ ድርቅ ደግሞ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የቀድንድ ከብቶችን እየፈጀ ነዉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባባሪያ ቢሮ (ኦቻ) እንደሚለዉ የሰሜኑ ጦርነት፣ የደቡብና የምስራቁ ድርቅ፣ በየአካባቢዉ ከሚደረገዉ ግጭት ጋር ተዳምሮ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጥ ኢትዮጵያዊን አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ ጠባቂ አድርጎታል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF ተወካይ ጂያንፍራንኮ ሮቲጂሊያኖ እንደሚሉት ደግሞ እድሜያቸዉ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ኢትዮጵያዉያን ሕፃናት 37 ከመቶዉ በቂ ምግብ አያገኙም።ከሚሞቱት ሕፃናት 45 ከመቶዉ የሚሞቱት የምግብ እጥረት በሚያስከትለዉ ችግር ነዉ።
«ኢትዮጵያ ዉስጥ ዕድሜያቸዉ ከ5 ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት 37 ከመቶዉ ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።ከሚሞቱት ሕፃናት 45 ከሞቶዉ የሚሞቱት ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ነዉ።»
ጦርነት፣ግጭት፣ድርቅ፣ የምግብ እጥረት ሚሊዮኖችን የሚያፈናቅል፣ የሚያሰቃይ፣ የሚያስርብባት ኢትዮጵያ ርዕሰ-ከተማዋ ላይ አንዴ ዲያስፖራ፣ ሌላ ጊዜ ድል አድራጊ ሹመኛ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ የአፍሪቃ መሪዎች እያለች እንግዶችን ማንበሻበሽ መቻሏን ያዩ-ምንታዝበዉ ይሆን?
በቅርቡ የአፍሪቃ ሕብረትና የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ብራስልስ ዉስጥ ይደረጋል።በመጪዉ ሰኔ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪቃ ሕብረት የተለወጠበት 20ኛ ዓመት ይዘከራል።ያሁኑ 35ኛዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች መፈንቅለ መንግስት፣የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት፣ የምግብ ዋስትናን ከመሳሰሉ ጥቅል ርዕሶች በተጨማሪ፣ የቻድን ሽግግር፣ የኢትዮጵያን ጦርነት፣ የሱዳንን ዉዝግብ፣የሳሕል አካባቢን ቀዉስ አንስተዉ ተነጋግረዋል።ለየጉዳዩ «መፍትሔ» ያሉትን ዉሳኔም አሳልፈዋል።ገቢር ይሆን-ይሆን? ሌላ ጥያቄ።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ