የአየር ንብረት ለውጥ እና የአፍሪቃ ወጣቶች
ዓርብ፣ መስከረም 23 2012በመላው ዓለም በተለይም አውሮፓ ውስጥ በየሳምንቱ ዓርብ አደባባይ የሚወጡት ወጣቶች ቁጥር ተበራክቷል። ይህም መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ፈጣን ርምጃ እንዲወስዱ ግፊት ለማድረግ ነው። «በባዶ ቃላት ሕልሜን፤ ልጅነቴን ቀምታችሁኛል። እኔ እንደውም ዕድለኛ ነኝ። ሌሎች ሰዎች እየተሰቃዩ ነው። ሰዎች እየሞቱ ነው።»ትላለች የአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት እንዲያገኝ የምትሟገተው ስዊድናዊት አዳጊ ወጣት ግሬታ ቱንበርግ።
ወጣት በሚበዛባት አፍሪቃ የአየር ንብረት ለውጡ ዕውን ከሆነ ሰነበተ። ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ንፁህ የመጠጥ ውኃ በማያገኝባት ናይጄሪያ « በአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት የውኃ እጥረት እዚህ ናይጄሪያ ውስጥ እየተጋፈጥን ያለነው ዋንኛ ችግር ነው። በየዓመቱ እዚህ የዝናብ መጠን እየቀነሰ እና እየደረቀ ነው። በዚህም የውኃ እጥረት የተነሳ በከብት አርቢዎች እና በገበሬዎች መካከል ግጭት ይቀሰቀሳል። ሁለቱም አካላት ደግሞ ለንግዳቸው ውኃ ያስፈልጋቸዋል። በሌላ በኩል ማኅበረሰቡን ዛፎችን እንዳይቆርጥ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል። እና ዛፍ መቁረጥ የአየር ንብረት ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ባለማወቅ ብዙ ሰዎች ናይጄሪያ ውስጥ ዛፎችን ይቆርጣሉ።» ይላል አንድ የናይጄሪያ ወጣት።
ዩጋንዳዊቷ ወጣት ደግሞ « እኛ ዩጋንዳዊያን በርካታ ጠንካራ ክስተቶችን አስተናግደናል።» ትላለች ሌሎች ደግሞ በመላው ዓለም እየተካሄደ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ የተቃውሞ ሰልፍ ተቀላቅለውዋል። «እኛ ዩጋንዳውያን የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች ነን። የዓለም አቀፉን ለውጥ ተቃውሞ የተቀላቀልነው ዓለማችን በአፋጣኝ እና በሰዓቱ ርምጃ መውሰድ እንድትጀምር ስንል ነው።»
የአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት እንዲያገኝ ስዊድናዊቷ ግሬታ ቱንበርግ መሟገት ከጀመረች ካለፈው ዓመት አንስቶ በዚህ ፍራይደይስ ፎር ፊውቸር በሚል መሪ ቃል በሚደረገው ሰልፍ በመላው ዓለም ከ 90 ሃገራት በላይ ተሳትፈዋል። ግሬታ በቅርቡ በኒው ዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይም ተገኝታ ለዓለም መንግሥታት ቅሬታዋን እምባ እየተናነቃት ገልፃለች።« ይህ ትልቅ ስህተት ነው። እኔ እዚህ ሳይሆን ወደ ትምህርት ቤቴ ተመልሼ በሌላኛው የአትላንቲክ በኩል ነበር መገኘት የነበረብኝ። እኛ ወጣቶችን እንዴት ብትደፍሩን ነው? «በባዶ ቃላት ሕልሜን፤ ልጅነቴን ቀምታችሁኛል። እኔ እንደውም እድለኛ ነኝ። ሰዎች እየተሰቃዩ ነው። ሰዎች እየሞቱ ነው» አጠቃላይ ስነ ምህዳሩ እየወደመ ነው። የሰው ልጅ የመጥፋት አደጋ በተጋረጠበት ሰዓት እናንተ ስለ ገንዘብ እና ስለ ዓለማዊ የምጣኔ-ሐብት ዕድገት ማውራት ላይ አተኩራችኋል። እንዴት ብትደፍሩ ነው?»
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከግማሽ ዓመት በፊት የዓለምን የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ በቃኘበት ዘገባ ይፋ እንዳደረገው፤ በመላው ዓለም ከሚደርሰው ሞት 25 በመቶ የሚሆነው እየተበላሸ በመጣው የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ ምክንያት ነው። ከሰሀራ በስተ ደቡብ የሚገኙ ሀገራትም በተለይ በድርቅ እና ርሀብ እየተጎዱ ይገኛሉ። ይህም ወደ ሌላ ችግር ያመራል።« ድህነት አለ፣ የምግብ ዋስትና ስጋት አለ፣ ሥራ አጥነት አለ። እኩል ያለመሆን ጉዳይ አለ። እነዚህ ሁሉ ጉዳዩች በማኅበረሰባችን ላይ ትልቅ ችግር ይፈጥራሉ ። አፍሪቃ ውስጥ አብዛኛን ጊዜ አክራሪነት፣ ተቃራኒነት የመሳሰሉት የሚፈጠሩት ሰዎች ሌላ ምንም አማራጭ ስለሌላቸው ነው።» ይላሉ። የቶጎ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ልኡክ የቡድን መሪ ሙባራክ ሞካኢላ።
ደሳለኝ ፍሬው ። የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው። የሚሰራው ደግሞ በእሱ እና በጓደኛው ባቋቋሙት የጤና ቀበና ግንፍሌን እናጽዳ ማሕበር ነው። የአካባቢ ጥበቃ አስፈላጊነትን አምነው መንቀሳቀስ የጀመሩት ገና ከ 14 ዓመት በፊት ነው። « ስማችን ወይም ስያሜያችንም እንደሚለው ከቀበና እና ግንፍሌ ነን። በወንዞቻችን እና አካባቢያችን የነበረው የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ሁሉ ማጣታችንን ስላየን እና በአጠቃላይ በአባባቢው ያለው ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ በመሄዱ የምንችለውን ለመስራት ተነሳን።» ይላል ደሳለኝ። የዛሬዎቹ ጎልማሶች ለዚህ ሥራቸው ከ10 ዓመት በፊት የምድራችን ጀግና የሚል ሽልማት ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ ተቀብለዋል። ደሳለኝ ከቃል ባለፈ ኢትዮጵያኑ ሥራቸውን በተግባር ማሳየት ከጀመሩ እንደቆዩ ይናገራል። « ስላልተጮኸለት ነው እንጂ ብዙ መሬት የረገጡ ስራዎችን ሰርተናል። ዘንድሮ ባለው የዛፍ ተከላ ስነ ስርዓት ላይ በንቃት ተሳትፈናል።»
የDW ጋዜጠኛ አህመድ ሳሊሱም የአፍሪቃ ወጣቶች የአካባቢ አየር ንብረት ለውጡ ሰለባ መሆናቸውን አውቀው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ነው የሚያስረዳው። « አፍሪቃ ውስጥም በርካታ ግሬታዎች አሉ ነገሮች እንዲቀየሩ ጥረት የሚያደርጉ። መንግሥታቸውንም ለዚህ ተጠያቂ ስለሚያደርጉ በአሁኑ ወቅት መሪዎች የአየር ንብረት ላይ አተኩረው መሥራት ጀምረዋል።»ይሁንና ርምጃው በቂ አይደለም ባይ ነው አህመድ። ናይጄሪያዊው የአየር ንብረት ተሟጋች ኢሳህ ኑሁ ደግሞ ከአፍሪቃ ይልቅ የምዕራባውያን ሃገራት ትልቅ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ይላሉ። « ለአየር ንብረት ለውጡ ምክንያት በርግጥ ፍትህ ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ አፍሪቃ በተለይ ደግሞ ናይጄሪያ የምትበክለው ድርሻ መጠነኛ ነው። ብዙ ሁሉም ሃገራት ተሰባስበው በጋራ መስራት አለባቸው። እኛ መንግሥታችንን የምንለው የተባበሩት መንግሥታት፣ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ቀርባችሁ ፍትህን ተረዱ ነው። የአፍሪቃ ሃገራት የሙቀት ልቀታቸውን ይቀንሱ የምትሉ እናንተ ይበልጥ የምትበክሉት ለመሆኑ ምን እያደረጋችሁ ነው ? ነው ጥያቄው? በርግጥ የናይጄሪያ የህዝብ ቁጥር ከ 200 ሚሊዮን በላይ ነው። የህዝባችን ቁጥር በጨመረ መጠን ደግሞ የፍላጎት መጠናችንም ይጨምራል። በዚያም ላይ ለምድር ወገብ ምን ያህል ቅርብ እንደሆንን ተመልከቱ። ስለዚህ ሁሉም ይህችን ምድር የሚወድ ህዝብ ሁሉ በአየር ንብረት ለውጡ ላይ እንስራ ስንል ጥሪ እናቀርባለን። ምክንያቱም ቀውስ ውስጥ ነው የምንገኘው። »
ደሳለኝ በአፍሪቃ ሃገራት ዘንድ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በጋራ የመቆም ነገር ቢታይም ዘላቂ ልማት በማካሄድ እና ገንዘብ መድቦ በማሰራት ላይ ውስንነት አለ ይላል። ይሁንና እያንዳንዱ ሰው የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት ይችላል።« ምንም እንኳን የበለፀጉት ሀገራት ትልልቁን ድርሻ ቢወስዱም እኛም አካባቢን ከመበከል ረገድ የየራሳችን የሆነ የማይናቅ ድርሻ አለን። ስለዚህ የየዕለት ስራዎቻችንን ለአካባቢ ተስማሚ፣ ዘላቂ የሆነ መፍትሄዎችን በመጠቀም መቅረፍ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርብናል።»
ልደት አበበ/ ሚሚ ሜፎ
ሸዋዬ ለገሰ