1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቃዮች ሮሮ ከኪረሙ ወረዳ

ዓርብ፣ ኅዳር 9 2015

​​​​​​​በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ በመስከረም ወር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ዐስታወቁ። ከወረዳው ሃሮ፣ ቦቃና የተለያዩ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ሰዎች በወረዳው ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4Jkmp
IDPs from Horo guduru wollega
ምስል Seyoum Getu/DW

ኪረሙ ወረዳ ከ52ሺ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉ ተገልጧል

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ውስጥ በመስከረም ወር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ ዐስታወቁ። ከወረዳው ሃሮ፣ ቦቃና የተለያዩ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ሰዎች በወረዳው ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም ወደ ቀዬአቸው የተመለሱ ዜጎችም ለሁለተኛ ጊዜ መፈናቀላቸውን እየገለጹ ነው። የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት በበኩሉ ሰብአዊ ድጋፍ በቅርቡ ለተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚያቀርብ አመልክቷል። በኪረሙ ወረዳ ከ52ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ ከዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በኪረሙ ወረዳ ስር በሚገኙ የተለያዩ ስፋራዎች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው በወረዳው ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ተገልጸዋል፡፡ በወረዳው ሃሮ ከሚባል ቀበሌ የተፈናቀሉ አንድ ነዋሪ ሰብአዊ ድጋፍ ባለፉት ሁለት ወራት እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ በኪረሙ ወረዳ በተለይም ከመንገድ መዘጋት ጋር ተያይዞ ለከፍተኛ ችግር እንደተጋለጡ ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ ከነቀምቴ ወደ ኪረሙ እና ከቡሬ ወደ ኪረሙ የሚወሰደው መንገድ ከተዘጋ ረጅም ጊዜ እንደሆነውም ጠቁመዋል፡፡

በኪረሙ ወረዳ ቦቃ ቀበሌ ነዋሪ እና ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላው ነዋሪም ከመስከረም ወር ወዲህ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳላገኙ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው የነበሩ ሲሆን፤ ባለፈው ነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም ዳግም ተፈናቅለው ወደ ወረዳው ከተማ ተመልሰው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ወረዳውን ከሌሎች አካባቢዎች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች እስካሁን አለመከፈታቸውን ጠቅሶ የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ እና ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ሐሳብ አቅርበዋል።

IDPs from Horo guduru wollega
ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የተፈናቀሉ ዜጎች ሻምቡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተሰባስበው ይታያሉምስል Seyoum Getu/DW

ዐሥራ ሰባት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ያለው የምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው እንደነበር የዞኑ አስተዳደር መረጃ ያመለክታል፡፡ በዞኑ ስር ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል በ13ቱ ወረዳዎች ውስጥ ባለፈው ዓመት በነበረው የፀጥታ ችግር ሰዎች ተፈናቅለው መቆየታቸውን የምስራቅ ወለጋ ዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ወይም ቦሳ ጎኖፋ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኜ ላቺሳ ተናግረዋል፡፡

ተፈናቅለው ከነበሩት መካከል 110ሺ የሚደርሱት ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው የነበሩ ሲሆን፤ በኪረሙ ወረዳ ደግሞ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ከነበሩት መካከል 5ሺ የሚደርሱት ከወር በፊት በነበረው አለመረጋጋር ዳግም መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡ አንጻራዊ ሰላም በሚታይባቸው ስፍራዎች እንደ ዲጋ ወረዳ፣ ጉቱ ጊዳ፣ ስቡ ስሬ፣ ዋዩ ጡቃ ወረዳዎች እንዲሁም ሊሙ ወረዳን ጨምሮ ለ2ኛ ዙር በመስከረም ወር ሰብአዊ ድጋፍ ማድረሳቸውን አክለዋል፡፡ በኪረሙና ግዳና አያና ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ደግሞ በትራንስፖርት እና መንገድ ችግር የተነሳ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የነዋሪዎች እንግልት

«በኪረሙ በነበረው የጸጥታ ችግር የሰዎች ንብት ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል፡፡ በሰዎች ላይ ጉዳትም ሲደርስ ቆይተዋል፡፡ ከ5ሺ በላይ የሚሆኑት ነዋሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ ነው የተፈናቀሉት፡፡ ወደ ኪረሙ የሚወስደው መንገድ መበላሸትና ከነቀምቴ ግዳአያና መንገድ መቆራረጥ ምክንያት በወቅቱ ድጋፍ ማድረስ አልተቻለም፤ ለወረዳው የተመደበው ድጋፍም ተከማችቶ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ሰብአዊ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ሰዎች ይደርሳል፡፡ ከ52ሺ በላይ ሰዎች በወረዳው ተፈናቅለው ነበር አሁን ቁጥሩ ጨምረዋል ብለዋል።» በምስራቅ ወለጋ ዞን አብዛኛው ወረዳዎች ውስጥ 240ሺ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ የዞኑ ቦሳ ጎኖፍ መረጃ ያስረዳል፡፡

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ