የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ወዴት እያመራ ነው?
እሑድ፣ የካቲት 19 2015ብዙም ይቆያል ተብሎ ያልተገመተው የዩክሬኑ ጦርነት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አጥፍቶ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ ንብረትም እያወደመ አንድ ዓመት አልፎታል። ጦርነቱ ከሀገራቸው ያፈናቀላቸው ከ 8 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን በተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት የስደት ሕይወት እየገፉ ነው። እዚህ ጀርመን ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የዩክሬን ስደተኞች ይገኛሉ። የዩክሬኑ ጦርነት ዳፋ ከአውሮጳ አልፎ ለመላው ዓለም ተርፏል። በዓለም ዙሪያ የሸቀጦች አቅርቦትን በማስተጓጎል የምግብና የኃይል አቅርቦት ዋጋ እጅግ እንዲያሻቅብ አድርጓል። የብዙ ሀገራትን ኤኮኖሚም አናግቷል።ያስከተላቸው ማኅበራዊ ቀውሶችም ብዙ ናቸው። ዓመት ያለፈው ጦርነት ማብቂያው የት ነው የሚለው ጥያቄ ባየለበት በዚህ ወቅት ላይ ዩክሬን ጦርነቱን ማሸነፍ አለባት የሚለው ምዕራቡ ዓለም ታንኮችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ለዩክሬን ማጉረፉን ቀጥሏል። ለወደፊቱ ቃል የተገባላት ድጋፍም የትየለሌ ነው። ወታደራዊ እገዛው የዩክሬን አበሳ ማብዛቱ አይቀርም በማለት ስትዝት የከረመችው ሩስያ ፣ ኒኩሊዬርን ጨምሮ ከጦር መሣሪያ ቁጥጥር ውል መውጣቷን ይፋ ማድረጓ የጦርነቱን አድማስ እንዳያሰፋ አስግቷል። አስጊነቱ ይበልጥ እየጨመረ የሄደው የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ወዴት እያመራ ነው? ምዕራባውያንና ሩስያ ዓለምን ያናወጠውን ይህን ጦርነት ማስቆም ለምን ተሳናቸው? ከዚህ ጦርነት ዓለም ምን ትምሕርት ሊወስድ ይችላል? የዛሬው እንወያይ የሚያተኩርባቸው ነጥቦች ናቸው። በውይይቱ የሚሳተፉ ሦስት እንግዶች ተሳትፈዋል። እነርሱም ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር፣ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ የምጣኔ ሀብት ምሁር እንዲሁም ገበያው ንጉሴ የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ናቸው። ሙሉውን ውይይት ለማዳመጥ ከታች የሚገኘውን የድምጽ ማዕቀፍ ይጫኑ፦
ኂሩት መለሰ