ዜናውን በአጠቃላይ በጽሑፍም ከታች ማንበብ ይቻላል ።
አርዕስተ ዜና
*በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ጥር 17 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. አቡነ መንፈስ ቅዱስ የተባለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን መቃጠሉ ተገለጠ ። በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስትያን ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት እየደረሰ ምእመናን እና ቀሳውስት ላይም አሰቃቂ ግድያዎች ተፈጽመዋል ።
*ጣሊያን ከኢትዮጵያ የወሰደችውን የመጀመሪያውን ከሞተሩ ውጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተሠራ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ በይፋ አስረከበች ። አውሮፕላኑ የተወሰደው ፋሺሽት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት መሆኑን የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ ።
*በሱዳን ተፋላሚዎች የእርስ በእርስ ጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ስምንት ሚሊዮን መድረሱ አንዳሳሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዐስታወቀ ።
*የጀርመኑ ግዙፍ የበረራ ተቋም ሉፍታንዛ የበረራ አስተናጋጆች ማኅበር (UFO) ከሠራተኞች ደሞዝ ክፍያ ድርድር ዛሬ በመውጣቱ በሉፍታንዛ አዲስ የሥራ ማቆም አድማ ተጠራ ። በ11 የበረራ ጣቢያዎች ከ1,100 በላይ በረራዎች አንድም እንደሚሰረዙ አለያም መዘግየት እንደሚገጥማቸው ተዘግቧል ።
ዜናው በዝርዝር
ቦሰት፥ ኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ተቃጥሏል
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ጥር 17 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. አቡነ መንፈስ ቅዱስ የተባለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን መቃጠሉ ተገለጠ ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ የአከባቢው ነዋሪ እንዳሉት ቤተክርስትያኑ የተቃጠለው እኩለ ሌሊት ገደማ 5፡00 ሰአት ገደማ ላይ ነው ። ቤተክርስትኑ ከወረዳው ከተማ ወለንጪቲ 5 ኪ.ሜ. ገደማ ብቻ ርቆ ገጠር ውስጥ የሚገኝ ነው ተብሏል ። በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ስለደረሰው ቃጠሎ ዶቼ ቬለ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን ምስራቅ ሸዋ አገረ ስብከት እንዲሁም ከቦሰት ወረዳ ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም ። የቤተክርስትያኑ ትክክለኛ የቃጠሎ መንስኤ ማወቅ አዳጋች ነው ያሉት አስተያየት ሰጪ፦ ከጽላቱ ውጪ በቤተ ክርስቲያኑ የሚገኙ ነዋዬ ቅድሳት እና ጣራ ግድግዳው መቃጠሉን ማመልከታቸውን ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዘግቧል ። በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስትያን ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት እየደረሰ ምእመናን እና ቀሳውስት ላይም አሰቃቂ ግድያዎች ተፈጽመዋል ።
ቱሉ ቦሎ፥ ኦሮሚያ ክልል የእንቅስቃሴ ገደብ
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች ተጥሏል በተባለው የአንቅስቃሴ ገደብ የተነሳ የማኅበረሰቡ እለታዊ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ተገለጠ ። ባለፉት ጥቂት ቀናት በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በእየመንገዱ ተቃጥለው ማየታቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል ። ከተለያዩ አከባቢዎች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት፦ እሁድ አመሻሽ 12፡00 ሰአት በጀመረው የእንቅስቃሴ ገደብ የተነሳ ከአከባቢ አከባቢ የሚንቀሳቀስ ማኅበረሰብም ሆነ ተሽከርካሪዎች አይስተዋሉም ። «ሰዎች የጫኑ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ወደ ወልቂጤና ጅማ» ማለፋቸውን የወሊሶ ተሽከርካሪዎች ግን እየተንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን የዐይን እማኞቹ ተናግረዋል ። ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአዲስ አበባ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ለኦሮሚያ ክልል ፀጥታ እና ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች ቢደውልም ኃላፊዎቹ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ጥረቱ አለመሳካቱን ገልጧል ። የእንቅስቃሴ ገደቡ እንዲጣል ጥሪ ያደረገው አካልን በተመለከተ አስተያየት ሰጪዎቹ በይፋ የሚገልጹት ነገር አለመኖሩንም አክሏል ። ተጨማሪ ዘገባ በዜና መጽሄት ይኖረናል ።
ሮም፥ጣሊያን የወሰደችውን በኢትዮጵያ የተሠራ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ በይፋ አስረከበች
ጣሊያን ከኢትዮጵያ የወሰደችውን የመጀመሪያውን ከሞተሩ ውጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ የተሠራ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ በይፋ አስረከበች ። ይኽ «ፀሐይ» የሚል መጠሪያ ያለው አውሮፕላን ወደ ጣልያን የተወሰደው ፋሺሽት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት መሆኑን የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት በቀድሞ አጠራሩ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጻቸው፦ «የኢጣልያ መንግሥት በይፋ «ፀሐይ»ን ያስረከበበትን እለት ለኢትዮጵያውያን ታላቅ የኩራት ቀን» ብለውታል ። "ፀሐይ" በጎርጎሮሳዊው በ1935 ዓ.ም በጀርመናዊው መሐንዲስና በመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ አውሮፕላን አብራሪ በሉድቪግ ቬበር እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ትብብር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራ አውሮፕላን ነው ሲሉም ዐቢይ በኤክስ ገጻቸዉ ጽፈዋል ። የኢጣልያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ከጎርጎሮሳዊው 1941 ዓ.ም አንስቶ በኢጣልያ አየር ኃይል ቤተ-መዘክር ውስጥ የሚገኘው አውሮፕላኑ የመጀመሪያ በረራውን በታኅሣሥ 1928 ማካሄዱን አስታውቋል ። በዚሁ ወቅትም ቬበር አውሮፕላኑን ከአዲስ አበባ አስነስተው 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ለ7 ደቂቃ ማብረራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል ። አሁን ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው የፀሐይ አውሮፕላን የቀድሞ ቀለም ብርማ ግራጫ ነበርም ተብሏል ። የአውሮፕላኑ ርክክብ የተካሄደው ዐቢይ ጣሊያን ባስተናገደችው የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው ። አውሮፕላኑ ፀሐይ የሚለው ስያሜ የተሰጠው ለንጉሡ ልጅ ለልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ነው ።
ካርቱም፦በሱዳን ጦርነት የተፈናቀሉ 8 ሚሊዮን ግድም ደረሱ
በሱዳን ተፋላሚዎች የእርስ በእርስ ጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ስምንት ሚሊዮን መድረሱ አንዳሳሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዐስታወቀ ። ከስድስቱ የሱዳን ስደተኞችን ከተቀበሉ ሃገራት አንዷ ወደ ሆነችው ቻድ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ከሱዳኑ ጦርነት መቀስቀስ አንስቶ መሰደዳቸው ተገልጧል ። ከ100,000 በላይ ስደተኞች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መሸሻቸውን ዓለም አቀፍ ድርጅቱ ዐስታውቋል ። የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በሦስት ቀናት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ስለ ሱዳን ስደተኞች አሳሳቢ ሁኔታ ተናግረዋል ። የሱዳን ተፈናቃዮች አስቸኳይ እና ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ መጠየቃቸውን ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ዐስታውቋል ። በሱዳን በተቀሰቀሰዉ ግጭት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን የሱዳን ስደተኞችን ለመርዳት የኢትዮጵያ መንግስት በተመድ (UNHCR) እና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ የሚያደርገውን ጥረት ኮሚሽነሩ መመልከታቸውንም መግለጫው ጠቅሷል ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው በኩርሙክ ጊዜያዊ ማቆያ ዉስጥ የሚገኙ ከ20ሺ በላይ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎቹን ይዞታ መመልከታቸውን የተናገሩት ፊሊፖ ግራንዴ ኢትዮጵያ ከሱዳን ለመጡት ተፈናቃዮች የምታደርገውን ልገሳ የሚያስመሰግን ብለውታል ። ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የላቀ ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። ለጋሽ ሃገሮች ተጨማሪ ድጋፍ ካላደረጉ ለተረጂዎች መድረስ «እጅግ በጣም ከባድ ይሆናል» በማለት ኮሚሽነሩ ጥሪ አስትላልፈዋል ።
ቤርሊን፥የጀርመን ምክር ቤት ለሆሎኮስት ፍጅት ሰለቦች ልዩ ዝግጅት አደረገ
የጀርመን ምክር ቤት በናትሲ መንግስት በሆሎኮስት ፍጅት የተፈጸመባቸውን ዛሬ በልዩ ሁናቴ ዘከረ። ስድስት ሚሊዮን ግድም አይሁዶች በተቀናጀ መልኩ እልቂት ከተፈጸመባቸው የሆሎኮስት ፍጅት ማጎሪያዎች በልጅነታቸው ነጻ የወጡ አዛውንት በልዩ ዝግጅቱ ላይ ታድመው ንግግር አሰምተዋል ። ጀርመን ውስጥ የቀኝ አክራሪ ጽንፈኞች መጠናከር እና ጸረ ሴማዊነት አስተሳሰብ እየጨመረ መምጣቱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንም ተናግረዋል ። በ12 ዓመታቸው ከኦሽዊትስ የናትሲ ማጎሪያ የተረፉት ኤቫ ሴፓይሲ ሥጋታቸውን እንዲህ ገልጠዋል ።
«ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች በድጋሚ መመረጣቸው እጅግ ያስፈራኛል ። እንዲህ ጠንካራ ሆነው ለዴሞክራሲያችንን የሥጋት ምንጭ እንዲሆኑ ሊፈቀድላቸው አይገባም ። »
ንግግር ያሰሙት የ91 ዓመቷ አዛውንት ከጀርመን ርእሰ-ብሔር ፍራንክ-ቫልተር ሽታይንማየር እና ሌሎች ታዋቂ ፖለቲከኞች ጋርም ምክር ቤት ውስጥ ተወያይተዋል ። የምክር ቤቱ የዛሬ ልዩ የመታሰቢያ «የዓለም አቀፍ የሆሎኮስት መታሰቢያ ቀን» ዝግጅት አካል መሆኑ ተገልጧል ። «ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት መታሰቢያ ቀን» በእየ ዓመቱ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ጥር 27 ቀን እንዲሆን የተወሰነው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው ። ዕለቱም ፖላንድ ውስጥ ግዙፉ የኦሽዊትስ ማጎሪያ ከናትሲዎች ነጻ የወጣበት ቀን ነው ። በኦሽዊትስ ማጎሪያ እና ማቃጠያ ጣቢያ ውስጥ ብቻ 1,1 ሚሊዮን ሰዎች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል ። አንድ ሚሊዮን ያህሉ አይሁዶች ነበሩ ።
ቤርሊን፦ግዙፉ የጀርመን የሠራተኞች ማኅበር (Verdi) አድማ ጠራ
የጀርመኑ ግዙፍ የበረራ ተቋም ሉፍታንዛ የበረራ አስተናጋጆች ማኅበር (UFO)ከሠራተኞች ደሞዝ ክፍያ ድርድር ዛሬ በመውጣቱ በሉፍታንዛ አዲስ የሥራ ማቆም አድማ ተጠራ ። የአየር መንገድ የደህንነት ሰራተኞች በጠሩት አድማ ጀርመን ዉስጥ በ11 የበረራ ጣቢያዎች ከ1,100 በላይ በረራዎች አንድም እንደሚሰረዙ አለያም መዘግየት እንደሚገጥማቸው የጀርመን ዜና አገልግሎት (dpa) ቀደም ሲል ዘግቧል። በበረራ መሰረዝ አለያም መዘግየት የተነሳም 200,000 ግድም መንገደኞች መስተጓጎል ይገጥማቸዋል ሲል የዜና ምንጩ አክሎ ዘግቧል ። አድማው ተጽእኖ ያሳረፈባቸው የበረራ ጣቢያዎች ፍራንክፉርት፤ ሐምቡርግ፤ ብሬመን፤ ቤርሊን፤ ላይፕትሲሽ፤ ዱይስልዶርፍ፤ ኮሎኝ፤ ሐኖቨር፤ ሽቱትጋርት፤ ኤርፉርት እና ድሬስደን ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል ። የበረራ አስተናጋጆች ማኅበሩ «ሉፍታንዛ ያቀረበው የመጨረሻው የደሞዝ ማሻሻያም በቂ አይደለም» ሲል ዛሬ አጣጥሎ ከሠራተኛ ማኅበር ጋ ሌላ ድርድር ለማድረግ ቀጠሮ ባለመኖሩም ማኅበሩ የሥራ ማቆም አድማ ለመምታት መዘጋጀቱን ዐሳውቆ ነበር ። ባለፈው ዐርብ የሉፍታንዛ አብራሪዎች እና የበረራ አስተናጋጆች ከእህት ኩባንያው ዲስከቨር ኤይርላይንስ ጋ በመሆን አድማ መትተው ነበር ። በዛሬው ዕለት ደግሞ ግዙፉ የጀርመን የሠራተኞች ማኅበር (Verdi) በጠራው የአንድ ቀን ለሥራ እንታገል ጥሪ ዐሥራ አንድ የጀርመን የተለያዩ የበረራ ተቋማት የደህንነት ሠራተኞች በመሳተፋቸው መስተጓጎል ተፈጥሯል ። ቬርዲ በነገው እለት በመላው ጀርመን የመጓጓዣ አገልግሎት የማቋረጥ አድማ ጠርቷል ።
አቢጃን፥ ሞሮኮ ለአፍሪቃ እግር ኳስ የሩብ ፍጻሜ ሳታልፍ በጥሎ ማለፉ ተሰናበተች
አይቮሪኮስት ያሰናዳችው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች በትናንትናው ዕለት በአስደማሚ ውጤት ተጠናቀዋል ። ትናንት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ ማሊ በጨዋታም ብልጫ ዐሳይታ ቡርኪናፋሶን 2 ለ1 በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፍ ችላለች ። ባለፈው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ በሩብ ፍጻሜው ፖርቹጋልን ያሰናበተችው ሞሮኮ ግን ትናንት ማታ ጉድ ሆናለች ። በደቡብ አፍሪቃ ቡድን የ2 ለ0 ሽንፈት የገጠማት ሞሮኮ ለአፍሪቃ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ሳትደርስ በጥሎ ማለፉ ለመሰናበት ተገዳለች ። በዚህም መሠረት፦ የፊታችን ዐርብ እና ቅዳሜ ለሩብ ፍጻሜ የሚፋለሙት ስምንት ቡድኖች ተለይተዋል ። ዐርብ ማታ፦ ናይጄሪያ ከአንጎላ ትጫወታለች ። ከሦስት ሰአታት በኋላ ደግሞ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ከጊኒ ጋ ትጋጠማለች ። አስተናጋጇ አይቮሪኮስት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ቅዳሜ ዕለት ከጠንካራዋ ማሊ ከባድ ግጥሚያ ይጠብቃታል ። ብዙም ሳይጠበቁ ታላላቆቹን ቡድኖች ገንድሰው ከጣሉ ቡድኖች መካከል ኬፕ ቬርዴ ትገኝበታለች ። ሞሮኮን ጉድ ያደረገችው ደቡብ አፍሪቃ ቅዳሜ ዕለት ትጠብቃታለች ። ከአፍሪቃ እግር ኳስም ባሻገር በዓለም አቀፍ ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት ሞሮኮ፤ ግብጽ፤ አልጄሪያ፤ እና ቱኒዝያ የምድብ ማጣሪያውን ሳያልፉ ተሰናብተዋል ። የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የፊታችን ረቡዕ ሳምንት ይጠናቀቃሉ ። የቅዳሜ ሳምንት የደረጃ፤ እንዲሁም በነጋታው እሁድ የዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ