የሥነ-ሕዝብ ዓለም አቀፍ ጉባኤ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 9 2012ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በተለይ በወሊድ ጊዜ ሕይወታቸውን የሚያጡ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ የታለመው ያስገኘው ውጤት እና ተያያዥ ጉዳዮች በቅርቡ ኬንያ ላይ ተገምግመዋል። ባለፈው ሳምንት ከኅዳር 2 እስከ 4 ለሦስት ቀናት ናይሮቢ ኬንያ ላይ የተካሄደው ጉባኤ በዚህ ረገድ የተከናወኑ ተግባራትን በመቃኘት በቀጣይ ዕቅዱን ለማሳካት ተጨማሪ ርምጃ ለመውሰድ ያለመ መሆኑ ተገልጿል። ጉባኤው የዛሬ 12 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ካይሮ ላይ ሲካሄድ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በናይሮቢው ስብሰባ ላይም ዳግም አፅንኦት ሰጥቶ አንስቷቸዋል። ሴቶች ጥቂት ልጆችን ብቻ ወልደው ጤናማ ሕይወትን መኖር ከቻሉ ኅብረተሰቡ ከዚህ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል መርሆ ያዘለው ጉባኤ መከላከል በሚቻል የጤና ችግር በየዕለቱ ከ800 የሚበልጡ ነፍሰጤር ሴቶች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ አመልክቷል። በየዓመቱ 90 ሚሊየን የሚሆኑ ሴቶች ሳያስቡበት እንደሚፀንሱ፤ ከሦስት ሴቶች አንዷ ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባት የዓ.ም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
በጎርጎሪዮሳዊው 1094ዓ.ም ካይሮ ላይ በተካሄደው ተመሳሳይ ጉባኤ የሴቶች መብት እና እኩል መብት መከበር ለዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን በመተማመን 179 ሃገራት መርሃግብሩን ተቀብለውት በየግል ተግባራዊ ዕቅድ ለመንደፍ ተስማምተውበት ነበር። በዚህኛው ጉባኤ ላይ የተገኙት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች ግን የያኔው ዕቅድና መርሃግብር ሥራ ላይ እንዳልዋለ ያነሳሉ። የጀርመኑ ዓለም አቀፍ ሥነ-ሕዝብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሬናተ ቤኸር ዛሬም ሴቶች የራሳቸውን ጉዳይ የመወሰን መብታቸው ተግባራዊ አልሆነም ባይ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉትም ከሁለት አስርት ዓመት በላይ ጉዳይ ተነስቶ ዓለም አቀፍ መነጋገሪ ብቻ ሳይሆን የተግባር ዕቅድ ወጥቶለትም፤ ዛሬም ከ200 ሚሊየን የሚበልጡ ሴቶች መቼ፣ የት ወይም ከማን ልጅ መውለድ እንዳለባቸው የመወሰን መብቱ የላቸውም። ሃሳባቸውን በምሳሌ ሲዘረዝሩም፣ የቤተሰብ ምጣኔ፤ ከላየ ፅንስን የመጠቀሙ ውሳኔ፣ የሴቶችን ጤና የሚከታተሉ ሃኪሞን የማማከርም ሆነ ሕይወታቸው ለአደጋ ሳይዳረግ ፅንስ ማቋረጥ የመቻሉ ጉዳይ ለአንዳንዶች የተለመደ ቀላል ዕድል ቢሆንል በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ሴቶች ግን ዛሬም ትልቅ ችግር መሆኑንም ይናገራሉ።
«የካይሮው ጉባኤ ሥነ-ሕዝብን የተመለከተ ሳይሆን የግለሰቦች ጉዳይ ትኩረትእንዲያገኝ በማድረግ በኩል መሠረታዊ ርምጃ የወሰደ ነበር። እውነቱን ለመናገር በዚህ ጉዳይ ሴቶች ለራሳቸው እንዲወስኑ ማድረግ ይገባል። በእነሱ ላይ ምንም ነገር መጫን አይኖርብንም። ጉዳዩ ሴቶች በዚህ በኩል ውሳኔ መወሰን እንዲችሉ መብቱን የመስጠት ነገር ነው።»
ላለፉት 25 ዓመታት በዚህ ረገድ የተሠራውን ለመገምገም ከመላው ዓለም የመብት ተሟጋቾች በናይሮቢው መድረክ ተገኝተዋል። ይህ መድረክም እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030 ድረስ የታለመውን በማነቃቃት የተሻለ ሥራ ለማከናወን ግፊት የሚያደርግ እንዲሆን ነው የታሰበው። ተሳታፊዎቹ ትኩረት አድርገው የተነጋገሩባቸው ጉዳዮችም፣ በአጠቃላይ የጤና ጥበቃው አካልነት በተለይ ለፆታዊ እና ለስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ያለው ተደራሽነት፣ የተመድ የሰነሕዝብ የገንዘብ ድጋፍን ዓላማዎች በማሳካት ረገድ የገንዘብ ምንጮችን የመለየት፤ የሕዝብ ብዛትና ስብጥርን ከኤኮኖሚ እድገት ጥንካሬ እና ከዘላቂ ልማት ስኬት አኳያ መጠቀምን፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እና እንደየሴት ልጅ ግርዛት የመሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስቆም፤ ሰብዓዊ ቀውስ እና አስጊ ሁኔታ ባለበት ሳይቀር የፆታ መብት እና የስነተዋልዶ ጤና መብትን መጠበቅን ይመለከታሉ። ባለፈው ሳምንት በናይሮቢ የተካሄደው ጉባኤ የቆየ ግብ ቢኖረውም ያንን ለማሳካት የተጀመረው እንቅስቃሴ አዲስ እድገት እንዲኖረው ያለመ ነው። ከተሳተፉት አንዷ ናይሶላ ሊኪማኒ ካይሮ ላይ ከዓመታት በፊት የተወጠነው እስካሁን ተግባራዊ ባለመሆኑ ዛሬም የሴቶችን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ ውርጃ እንደሚፈፀም ይናገራሉ።
«ላለፉት ዓመታት ምንም ያህል ገንዘብ ለዘርፉ ቢመደብም ለምሳሌ አሁንም አደገኛ ውርጃ ይፈጸማል። በየዓመቱ አሁንም 25 ሚሊየን ሴቶች ይህን ይፈፅማሉ፤ ሰባት ሚሊየኑ ደግሞ በዚሁ መዘዝ ሀኪም ቤት ይገባሉ። ዛሬም በለጋ ዕሜያቸው የሚዳሩት ሕጻናት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው። 12 ሚሊየን የሚሆኑት ልጃገረዶች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ይዳራሉ። እንዲህ ያለውን ነገር ለማስቆም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እንዲህ ባለው የጋራ መድረክ ልምዶችን በመለዋወጥ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይህን ለመለወጥ ቁርጠኛ ሆኖ ለመሥራት ተሰባስቧል።»
ሺ ዲሳይድስ/ ትወስናለች/ የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሴቶች መብት ተቆርቋሪ ንቅናቄ አባል የሆኑት ሊኪማኒ፤ እንደሚሉት የናይሮቢው ጉባኤ ከዓመታት በፊት ካይሮ ላይ የተወጠነውን ዳግም በመመልከቱ የትኛው ተግባራዊ ሆኗል የቱስ ጎድሏል የሚለውን በገሀድ ለማየት አስችሏል። ኬንያ ለሦስት ቀናት ያስተናገደችው ይህ ጉባኤ ከ25 ዓመታት በፊት በተመድ አስተባባሪነት የተከናወነው ዓለም አቀፍ የስነሕዝብ እና ልማት በቀጣይ ዓመታት ውስጥ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራበት ያሳሰበው መሠረታዊ ጉዳይ ከምን እንደደረሰ መመዘኛ አይነት ነው። ሆኖም አሁንም ከሁሉም አቅጣጫ የቀረቡት ዘረባዎች እና መረጃዎች ያመለከቱት ዛሬም ችግሩ ባለበት መቀጠሉን ነው። የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ፣ በዚህ ወቅት ለዓለም መሪዎች ባስተላለፉት መልእክት «በዓለም አቀፍ ደረጃ የወደፊት ተስፋ ዘላቂነት የሚኖረው አዋቂዎች እና አዳጊ ሴቶች በራሳቸው አካል የማዘዝ መብታቸው ሲከበር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በተመድ የዓለም ስነሕዝብ የገንዘብ ድጋፍ ባልደረባ አርቱር ኤርከር በበኩላቸው፤ ባለፉት 25 ዓመታት የተከናወኑት ተግባራት ያስገኙትን ውጤቶች ለማሳየት ይሞክራሉ። እሳቸው እንደሚሉት ጉባኤው ከተካሄደ ከ25 ዓመት ወዲህ ባሉት ዓመታት በወሊድ ጊዜ ሕይወታቸው የሚያልፈው የእናቶች በ44 በመቶ ቀንሷል። ከላኤ ፅንስ የሚጠቀሙ ሴቶች ቁጥር በ25 በመቶ በመጨመሩ በመላው ዓለምም አንዲት እናት የምትወልዳቸው ልጆች ቁጥር ከስድስት ወደ አራት ዝቅ ብሏል። ምንም እንኳን ነገሮች እየተሻሻሉ መሄዳቸውን ለማሳየት ቢሞክሩም የተመድ በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓ,ም ያስቀመጣቸውን የልማት ግቦች ከግብ ለማድረስ አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ያመለክታሉ። ለዚህም ደግሞ ትኩረት የሚደረግባቸው ሦስት ጉዳዮች አሉ፤
«በተለይ ደግሞ ፍላጎቶች ሁሉ እንዲሟሉ በ2030 ዜሮ እንዲሆኑ በምንፈልጋቸው የቤተሰብ ምጣኔን ሊያሳኩ በሚያስችሉ ሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል። ለመከላከል የሚቻል የወሊድ ጊዜ ሞትን ዜሮ ማድረግ፤ በያንዳንዷ ቀን ከወሊድ ወይም ከእርግዝና ጋር በተገናኘ 800 ሴቶች ይሞታሉ፤ ይህ ዜሮ እንዲሆን እንፈልጋለን። እንዲሁም ፆታዊ ጥቃት እና በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዜሮ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። እነኚህ ናቸው ዓለም ዋጋ እንዲሰጠው እና እንዲስማማበት የምንፈልጋቸው ሦስቱ ጉዳዮች።
እየጨመረ የሚሄደውን የዓለም የሕዝብ ቁጥር ለመቆጣጠር በሚል ለሚከናወኑ ተግባራት ላለፉት 50 ዓመታት የገንዘብ አቅርቦት የሚያደርገው ብቸኛ ተቋም የተመድ የዓለም ስነሕዝብ የገንዘብ ተቋም ነበር። በዓመት 1,3 ቢሊየን ዶላር በጀት አለው። የዛሬ 50 ዓመት ባላደጉት ሃገራት የወሊድ መቆጣጠሪያ ይጠቀሙ የነበሩት 2 በመቶ ብቻ ነበሩ፤ ዛሬ 37 በመቶ ደርሷል። ባለፈው ዓመድ ድርጅቱ 40 በመቶው ከላየ ፅንስ በነፃ እንዲዳረስ 200 ሚሊየን ዶላር መመደቡ ተገልጿል። እንዲያም ሆኖ አሁንም አፍሪቃ ውስጥ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ነው የሚነገረው። በምዕተ ዓመቱ አጋማሽ አፍሪቃ ውስጥ 2,5 ቢሊየን ሰዎች ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። እንዲያም ሆኖ ግን በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት በተለይም በምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ የወሊድ መጠን እየቀነሰ መሄዱን በወቅቱ ተገልጿል። ይህ ከታየባቸው ሃገራት ሩዋንዳ እና ኢትዮጵያ ይጠቀሳሉ። በደቡብ አሜሪካ እና እስያም ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የነበረው የወሊድ መጠን ለውጥ ቢታይበትም አነስተኛ ነው። በልዩነት የተጠቀሰችው ኢንዶኔዢያ የሕዝብ ቁጥሯ እድገት በዚሁ ከቀጠለ በጎርጎሪዮሳዊው 2050ዓ,ም 320 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚኖራት ከወዲሁ ተገምቷል።
በነገራችን ላይ የጉባኤው አስተናጋጅ ሀገር ኬንያ በቀጣይ ዓመታት በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታ ተኮር ጥቃቶችን ጨርሶ ለማስቆም እንደምትሠራ አመልክታለች። የሴት ልጅ ግርዛትም እስከጎርጎሪዮሳዊው 2022ዓ.ም ድረስ በግዛቷ እንዳይፈፀም ለማድረግ ፕሬዝደንቷ ዑሁሩ ኬንያታ ቃል ገብተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ/ቲም ሻወንበርግ
ማንተጋፍቶት ስለሺ