1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 845.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ ክፍያ በኢትዮጵያውያን ትከሻ ላይ ተጫነ?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 27 2017

ገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን 845.3 ቢሊዮን ብር የንግድ ባንክ ዕዳ ከነወለዱ ለመክፈል ተረክቧል። መንግሥት ንግድ ባንክን ለመታደግ በተከተለው አካሔድ ትምህርት እና ጤና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለመሥራት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ ሊያውል አሊያም ገቢውን ለማሳደግ ተጨማሪ ግብር ሊያስከፍል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/4miPh
የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ስድትስ ኪሎ
በአዋጁ መሠረት ገንዘብ ሚኒስቴር የሚያወጣቸው የመንግሥት የዕዳ ሠነዶች ከሦስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው ይጠናቀቃሉ።ምስል Eshete Bekele/DW

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ ክፍያ በኢትዮጵያውያን ትከሻ ላይ ተጫነ?

ገንዘብ ሚኒስቴር 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የዕዳ ሠነድ በማውጣት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ እንዲከፍል የሚፈቅድ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። በአዋጁ መሠረት ከሚወጣው የዕዳ ሠነድ ውስጥ 845 ቢሊዮን 316 ሚሊዮን 570 ሺሕ 114 ብር ዕዳ ለመክፈል የሚውል ነው።

የተቀረው 54 ቢሊዮን 683 ሚሊዮን 429 ሺሕ 686 ብር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የታቀደ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ አስረድተዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች “ሠርተው መመለስ ስላልቻሉ” በንግድ ባንክ ምክንያት “የኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ቀውስ እንዳይፈጠር” መንግሥት እርምጃውን እንደወሰደ ዶክተር ኢዮብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።  

በአዋጁ መሠረት የሚወጡት የመንግሥት የዕዳ ሠነዶች ከሦስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው ይጠናቀቃሉ። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥት “በአንድ ጊዜ 900 ቢሊዮን ብር መክፈል ስለማይችል በዓመታት ከፋፍሎ ለመክፈል የሚረዳው ሠነድ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ለዕዳ ክፍያው “ከውጪ የሚመጣ ብድር የለም” ያሉት ኢዮብ “ከሀገር ውስጥ ካለው ኤኮኖሚ ገቢ ሰብስበን የምንከፍለው ነው” በማለት አስረድተዋል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የወሰዱት ብድር ከባንኩ አጠቃላይ ሐብት 60 በመቶ ድርሻ አለው።

በአዋጁ መሠረት የሚወጡት የመንግሥት የዕዳ ሠነዶች በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በንግድ ባንክ ሥምምነት የሚወሰን ወለድ ይከፈልባቸዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “የማስቀመጫ ወለዱን 7 በመቶ ቢያስከፍል በዓመት 63 ቢሊዮን ብር” ይደርሳል ሲሉ ይናገራሉ።  ወለዱ በራሱ ወለድ እንደሚኖረው የሚናገሩት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ወለዱ ብቻ 200 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ይሰጋሉ። 

በሦስት ዓመታት የሚከማቸው ወለድ ተጨምሮ በአጠቃላይ ገንዘብ ሚኒስቴር ለንግድ ባንክ መክፈል የሚጠበቅበት የገንዘብ መጠን ወደ 1.1 ትሪሊዮን ብር ከፍ ሊል እንደሚችል ዶክተር አብዱልመናን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የወሰዱት ብድር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ሐብት 60 በመቶ ድርሻ አለው።ምስል Eshete Bekele/DW

በየካቲት 2013 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን በማቋቋም ሀገሪቱን ሰንጎ ለያዛት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ መፍትሔ ለማበጀት ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል።

የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን “በራሱ ይኸንን ዕዳ ያለማቋረጥ መክፈል ባለመቻሉ ዘላቂ መፍትሔ ማድረግ ስለሚያስፈልግ እነዚህን የተጠራቀሙ ዕዳዎች ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር በመውሰድ በብድር ሠነድ መልክ መክፈል አስፈልጓል” ሲሉ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ የመጀመሪያው ሙከራ እንዳልተሳካ ተናግረዋል።

ከፍተኛ ዕዳ የተጫነባቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የትኞቹ ናቸው?

መንግሥት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሠነድ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ዕዳ ማለትም 191 ቢሊዮን 79 ሚሊዮን ብር ወደ የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን በማዘዋወር ቀዳሚ ነው። የሀገሪቱን የስኳር ፍላጎት መሙላት፣ ያቀዳቸውንም ፋብሪካዎች መገንባት የተሳነው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በሁለት ዙሮች 163 ቢሊዮን ብር ተዘዋውሮለታል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 80 ቢሊዮን 179 ሚሊዮን ብር፣ የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የአሁኑ የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩኘ 22 ቢሊዮን 768 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን 5 ቢሊዮን 483 ሚሊዮን ብር ለዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ተዘዋውሮላቸዋል።

ደንበኞቹ የሚከፍሉትን ታሪፍ በከፍተኛ መጠን የጨመረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 3 ቢሊዮን 369 ሚሊዮን ብር እንዲዘዋወርለት ተደርጓል። 

ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተሰጠው ብድር “ንግድ ባንክን ለአደጋ የሚያጋልጥ” ሲከፋም አጠቃላይ የባንክ አገልግሎት ዘርፍን “ለችግር የሚዳርግ ነው” የሚል ማስጠንቀቂያ ዓለም ባንክን ከመሳሰሉ ተቋማት ይደመጥ እንደነበር የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን ያስታውሳሉ። ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ የብድር ጥያቄ ሲቀርብ የግል አመልካቾች እና የመንግሥት ተቋማት የሚስተናገዱበት መንገድ ነው። 

“አንድ ነጋዴ ቢያመለክት በጣም መጠነ-ሰፊ የሆነ ግምገማ ተካሒዶ ነው ብድር የሚሰጠው” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው የመክፈል አቅሙ፣ ማስያዣ፣ የገበያ ሁኔታ፣ የወደፊት ትንበያ፣ የተበዳሪው ባህሪን ጨምሮ “የማይታይ ጉዳይ የለም” ሲሉ ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ አመልካቾች ከጠየቁት የብድር መጠን በታች ይሰጣቸዋል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከንግድ ባንክ ተበድሮ ያልመለሰው 80 ቢሊዮን 179 ሚሊዮን ብር ወደ የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ተዘዋውሮለታል። ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

ይሁንና “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ እንደዚህ አይነት ግምገማ የለም።” ተቋማቱ ያቀዱት “ፕሮጀክት ያዋጣል አያዋጣም”  የሚለው ጉዳይ ከግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ በመንግሥት ዋስትና የጠየቁት ብድር ሲሰጣቸው ቆይቷል።  “ዛሬ ዕዳው ሲመጣ ግን ሕዝብ ይወስዳል። መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው” ይላሉ ዶክተር አብዱልመናን።

“ታላቁ ብሔራዊ ብክነት?”

ገንዘብ ሚኒስቴር የዕዳ ሠነድ እንዲያወጣ የሚፈቅደው አዋጅ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። አዋጁ ከመጽደቁ በፊት አስተያየት ካቀረቡ የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያስከተሉትን ኪሳራ “ብሔራዊ ብክነት” ብለውታል።

የስኳር ፋብሪካዎች እና የማዳበሪያ ማምረቻዎችን ለመገንባት የተወጠኑትን ጨምሮ “በወቅቱ ኢሕአዴግ እንደ ትልቅ እምርታ ሲገልጻቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች ብሔራዊ ውድቀት መሆናቸውን በግልጽ ይኸ አሐዝ ብቻ አመላካች ነው” ሲሉ ዶክተር ደሳለኝ ተችተዋል።

“በኢሕአዴግ ወቅትም፤ አሁን በብልጽግና መራሹ ወቅትም ማንም ሰው በዚህ ሀገራዊ ብክነት ዙሪያ የተጠየቀ ሰው መረጃ የለኝም” ያሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባል “በፊት ካልተደረገ ለምን ቢያንስ ዛሬ አይደረግም?” ሲሉ ጠይቀዋል።

የከሰረው ገንዘብ “ታላቁ ብሔራዊ ብክነት ሊባል የሚችል ነው” ያሉት ዶክተር ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው ውይይት “ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ሰዎች ተለይተው ተጠያቂ እንዲሆኑ የማይደረገው ለምንድነው? በዚህ ዙሪያስ ምን እየተሠራ ነው?” የሚል ጥያቄ ለገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ አቅርበዋል።

የንግድ ባንክ ውድቀት “ሀገራዊ ጥቅምን የሚጎዳ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ እሱን ላንፈቅድ እንችላለን” ያሉት ዶክተር ደሳለኝ “አጠቃላይ በማክሮ ኤኮኖሚው ላይ፣ በኢትዮጵያ ፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ፣ በገበያ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ችግር ምንድነው?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለከፍተኛ ኪሳራ ሲዳረጉ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ለምን ተጠያቂ አልሆኑም የሚል ጥያቄ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢቀርብላቸውም ጉዳዩን ምላሽ ሳይሰጡ አልፈውታል። ምስል Eshete Bekele/DW

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ “ከፍተኛ የአሠራር ችግር የነበረባቸው” የመንግሥት የልማት ድርጅቶች “ፕሮጀክቶች በአግባቡ ሳይጠኑ ወደ ሥራ” መግባታቸው ለተፈጠረው ችግር አንድ ገፊ ምክንያት እንደነበር ተናግረዋል።

የተጠያቂነት ጉዳይን በተመለከተ ግን ዶክተር ኢዮብ ሰምተው እንዳልሰሙ አልፈውታል።

ዶክተር ኢዮብ “በመንግሥት ላይ የፊስካል ጫና ያመጣል። ምንም ጥያቄ የለውም” ሲሉ ዳፋ እንደሚኖረው አምነው ተቀብለዋል። “ይኸ የፊስካል ጫና በዓመታት የተከፋፈለ” በመሆኑ እንዲሁም መንግሥት የገቢ አቅሙን “የማሳደግ ሥራ እየሠራን ስለሆነ ከአጠቃላይ የፊስካል ማዕቀፍ [አንጻር] ስናየው ዘላቂ ነው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው “ተጨማሪ ወጪ ያመጣብናል። ግን የፊስካል መዛባት፤ የማክሮ መዛባት የሚያመጣ አይደለም” የሚል ማብራሪያ አቅርበዋል።

ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት ግን ጉዳዩ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሕዝብን ኃይለኛ ጫና ውስጥ ሊከት የሚችል ነው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው እንደሚሉት መንግሥት መንገድ ለመገንባት፣ ትምህርት ለማስፋፋት፣ የጤና ተቋማት ለመሥራት የሚችልበትን ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ ለማዋል የሚያስገድደው ፊስካል ጫና አንደኛው ይሆናል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ይኸን አካሔድ ካልተከተለ ዕዳውን ለመክፈል የገቢ ምንጮቹን መጨመር ይኖርበታል። በዚህኛው አካሔድ “ዜጎች የሚከፍሉት ግብር ላይ ይጫንባቸዋል። ወደ ፊት ማንኛውም ቀዳዳ እየተፈለገ ዜጎች ላይ ተጨማሪ ግብር ይጣላል ማለት ነው” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን አብራርተዋል።

ሁለቱም የዕዳ ክፍያ እና የንግድ ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የተያዘው ውጥን የሚያስከትሉት ጫና በሕዝብ ላይ እንዲወድቅ የሚያደርግ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳውን መክፈል ተስኖት ንግድ ባንክ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ቢገጥመው ተመልሶ ብር ወደ ማተም ሊገባ እንደሚችል ዶክተር አብዱልመናን ይሰጋሉ። መንግሥትም የዕዳ መክፈያ ጊዜውን ሊያራዝም ይችላል። ይኸ ደግሞ ችግሩን ወደ ሌላ ትውልድ የሚያሻግር ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ