1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሰኞ፣ ሐምሌ 8 2016

የሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና -በአማራ ክልል ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው የኢንተርኔት ሞይል ዳታ ትናንት በአንዳንድ ከተሞች አገልግሎት መስጠት መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች አገልግሎቱ በተመረጡ ስልኮች ብቻ ነው የሚሰራው ብለዋል። -የኬንያ ፖሊስ በተደጋጋሚ ሰዎችን ሲገድል የነበረና ድርጊቱንም አምኗል ያለውን አ,ረመኔ ማሰሩን አስታወቀ። /አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ዳኛ ባለፈው ቅዳሜ ከግድያ ሙከራ የተረፉት የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ምሥጥራዊ የመንግሥት ሰነዶች በመያዝ የተመሰረተባቸውን ክስ ውድቅ አደረጉ።

https://p.dw.com/p/4iLHL


ባህርዳር       በአማራ ክልል በአንዳንድ ከተሞች የሞባይል ዳታ አገልግሎት ተጀመረ

በአማራ ክልል ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው የኢንተርኔት ሞይል ዳታ ትናንት በአንዳንድ ከተሞች አገልግሎት መስጠት መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ አገልግሎቱ መጀመሩን ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፣ ሆኖም በተመረጡ ስልኮች ብቻ ነው የሚሰራው ብለዋል።  
የደብረማርቆስ፣ የገንዳ ውሀና የባህር ዳር ከተሞች ነዋሪዎችም የተንቀሳቃሽ ስልክ ዳታ ስራ መጀመሩን ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በሌላ በኩል የአንዳንድ የወረዳ ከተማ ነዋሪዎች ግን አገልግሎቱን እንዳላገኙ በስልክ ነግረውናል፡፡ ከመካከላቸው እኝህ  የምስራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ነዋሪ አንዱ ናቸው፡፡  የባህርዳሩ ወኪላችን አለምነው መኮንን ስለ አገልግሎቱ መቀጠልም ሆነ ተጠቃሚዎች ስላነሷቸው ችግሮች  ከኢትዮ ቴሌኮም ተጨማሪ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው  ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡ የሞባይል ዳታና ሌሎች የአዲሱ የመገናኛ ቴክኖሎጂ አውታሮች በአማራ ክልል ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከተዘጉ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ሥራቸውን የሚያከናውኑ አካላት ለከፍተኛ ማሕበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ዶቼቬለ በተደጋጋሚ ዘግቧል ። 

ኬንያ        በፖሊስ የተያዘው ተጠርጣሪው አረመኔ ነፍሰገዳይ ድርጊቱን አመነ

የኬንያ ፖሊስ በተደጋጋሚ ሰዎችን ሲገድል የነበረና ድርጊቱንም አምኗል ያለውን አረመኔ ማሰሩን አስታወቀ። ተጠርጣሪው 42 ሴቶችን ከገደለ በኋላ የተቆራረጠ አካላቸውን በአንድ የናይሮቢ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማከማቸቱንም ፖሊስ አስታውቋል። ካለፈው አርብ አንስቶ አካላታቸው የተቆራረጠ የ9 ሰዎች አስከሬን በፕላስቲክ ውስጥ ተከቶ ተገኝቷል። የተቆራረጡት አስከሬኖች የተገኙት ደቡብ ናይሮቢ ውስጥ ሙኩሩ በተባለው የምንዱባን ሰፈር በሚገኝ ቆሻሻ መጣያ ስፍራ ነው። እጅግ የሚያሰቅቀው ይህ ተግባር መላ ኬንያውያንን አስደንግጧል። የኬንያ ፖሊስ ተጠባባቂ ኢንስፔክተር ጀነራል ዱግላስ ካንያ የ33 ዓመቱ ዋነኛው ተጠርጣሪ ኮሊንስ ጁሜይሲ ካሉሻ ትናንት ከእኩለ ለሊት በኋላ ከአንድ መጠጥ ቤት አቅራቢያ ተይዞ መታሰሩን ተናግረዋል። ነፍሰ ገዳዩ ሴቶቹን በስጦታ እያባበለ ከወሰዳቸው በኋላ እንደገደላቸውና የ42ቱን ሴቶች አካላት በጣለበት ስፍራ መቆራረጡን ማመኑንም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል። ነፍሰ ገዳዩ ክኽሉሻ ግድያዎቹ ከጎርጎሮሳዊው 2022 ዓም አንስቶ እስካለፈው ሐሙስ ጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 11 ቀን ድረስ መፈጸማቸውንም ተናዟል። እርሱ አንዳለው መግደል የጀመረው በባለቤቱ ሲሆን አንቆ ከገደላት በኋላ አስከሬኗን ቆራርጦ በዚሁ ስፍራ ጥሎታል። ፖሊስ ዛሬ እንደተናገረው እስካሁን ከቆሻሻ መጣያው 9 አስከሬኖች ተገኝተዋል። ሁለተኛ ተጠርጣሪ ነፍሰ ገዳይም ማሰሩን ፖሊስ አስታውቋል።  

መቅዶሾ       በሶማሊያው ፍንዳታ የሞቱት ቁጥር 9 ደረሰ

ትናንት ምሽት መቅዲሾ በሚገኝ አንድ የከተማይቱ ታዋቂ ምግብ ቤት ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ  የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ ማለቱ ተነገረ። አንድ የሶማሊያ የብሔራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት ባለስልጣን  ዛሬ እንደተናገሩት በጥቃቱ 9 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ፣ሌሎች 20 ደግሞ ቆስለዋል። ትናንት ማምሻውን ባለሥልጣናት በሰጡት መግለጫ የሞቱት አምስት ሰዎች ናቸው ብለው ነበር። በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚገኘው አደጋው የደረሰበት ምግብ ቤት በወቅቱ የእግር ኳስ ጨዋታ በመከታተል ላይ በነበሩ በርካታ ወጣቶች የተሞላ ነበር። ለፍንዳታው እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ ሃላፊነት የወሰደ ወገን የለም። ሆኖም መንግሥታዊው የሶማሊያ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት ጥቃቱ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው በሚባለው በአሸባብ ተፈጽሟል ሲል ዘግቧል። ባለፉት ቅርብ ወራት መሰል ጥቃት ጋብ ያለ መስሎ ነበር።ይሁንና ከእሁዱ ጥቃት በፊት ቅዳሜ ከሚገኙበት ከመቅዲሾ ዋነኛ እስር ቤት ለማምለጥ የሞከሩ 5 የአሸባብ ተዋጊዎች ተገድለው ነበር። በወቅቱም ሦስት የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች መሣሪያ መታጠቅ በቻሉ በእስረኞቹ ሲገደሉ ሌሎች 18 ደግሞ መቁሰላቸውን አንድ የእስር ቤቱ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

ኪጋሊ   ካጋሜ ዳግም ይመረጣሉ ተብሎ የሚጠበቀው የሩዋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ

ሩዋንዳውያን ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ዛሬ ድምጻቸው ሲሰጡ ውለዋል። የዛሬው ምርጫ ውጤት ከዛሬ 30 ዓመት አንስቶ ሩዋንዳን የሚመሩትን የፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜን ሥልጣን ያራዝማል ተብሎ ይጠበቃል። ዛሬ መራጩ ህዝብ ድምጹን ለመስጠት በሀገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከማለዳው 11 ሰዓት አንስቶ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን መከፈት ሲጠባበቅ ነበር። በአንዳንድ ድምጽ መስጫዎች ረዣዥም ሰልፎች ነበሩ። ሲመርጥ የመጀመሪያው መሆኑን የተናገረው  በሞተር ብስኪሌት የህዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ላይ የተሰማራ አንድ ሩዋንዳዊ ፣ የምመርጠው ካጋሜን ነው ፤ እርሳቸውን የሚመስል መሬ አይቼ አላውቅም ብሏል።  እኚህ መራጭ ደግሞ የምመርጠው ብዙ ያደረገልንን ሰው ነው ይላሉ  ።
«የመጣሁት ጥሩ መሪ ለመምረጥ ነው። የምመርጠውንም አውቃለሁ። ይህ ሰው በልቤ ውስጥ ነው፤እስካሁን ብዙ ያደረገልንና ለእድገታችንም ያገዘን ሰው ።ለዚህ ነው በጠዋት የመጣሁት።»
ሌላዋ ድምጽ ሰጭ ደግሞ መምረጥ ጠቃሚ ነው ብለዋል። «ለኔ ድምጽ መምረጥ አስፈላጊ ነው። ህዝቡ መሪዎቹን መምረጥ የሚችልበት በጥሩ ዴሞክራሲ የመኖር እድል ይሰጠናል።የሚሰሩት ለኛ ነው። የሚወክሉት እኛን ነው። የሀገራችንን እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችለውን ይወስናሉ።» የምርጫ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት 14 ሚሊዮን ህዝብ ካላት ሩዋንዳ 9.5 ሚሊዮኑ ድምጽ ለመስጠት ተመዝግቧል። የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫው ውጤት ዛሬ ማምሻውን ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። ምርጫውን እንደሚያሸንፉ የሚጠበቀቁት የካጋሜ ተቀናቃኞች ከሩዋንዳ የአረንጓዴዎቹ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፍራንክ ሀቢኔዛ እና የግል ተወዳዳሪው ፊሊፕ ምፔዪማና ናቸው። በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓም በተካሄደው ምርጫም የካጋሜ ተቀናቃኞች ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ነበሩ ።የ66 ዓመቱ ካጋሜ ትንሽቷን ምሥራቅ አፍሪቃዊት አገር ሩዋንዳን መምራት የጀመሩት በጎርጎሮሳውያኑ 1994 የአማጽያን መሪ ሆነው የሩዋንዳን መንግሥት ከተቆጣጠሩና በሀገሪቱ ሲፈጸም የነበረውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ካስቆሙ በኋላ ነበር። በመጀመሪያዎቹ 6 ዓመታት ምክትል ፕሬዝዳንትና   ነበሩ።  ካጋሜን በሩዋንዳ አስደናቂ እድገት በማስመዝገብ የሚያወድሷቸው እንዳሉ ሁሉ በፈላጭ ቆራጭነት የሚያወግዙዋቸውም አልጠፉም።  

አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ዳኛ ባለፈው ቅዳሜ ከግድያ ሙከራ የተረፉት የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ 

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ምሥጥራዊ የመንግሥት ሰነዶች በመያዝ የተመሰረተባቸውን ክስ  ውድቅ አደረገ። ትራምፕ ከዚህ ቀደም የሾሟቸው ዳኛ ኤሊን ካነን ጉዳዩን በሚያየው በልዩ መርማሪው ምደባ ሕጋዊነት ላይ  ባላቸው ጥርጣሬ መነሻነት እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። ትራምፕ ከሰነዶቹ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው ባለፈው ዓመት ነበር። ይህም ትራምፕ ከተከሰሱባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ትራምፕ የቀረበባቸው ክስ ፕሬዝዳንትነት ሳሉ ከጎርጎሮሳዊው 2017 እስከ 2021 ድረስ  በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው የሚገባ የሚባሉ  ምስጢራዊ ሰነዶችን በሕገ ወጥ መንገድ ማከማቸት የሚል ነበር። በነሐሴ 2022 ዓ.ም. የፌደራል መርማሪዎች ፍሎሪዳ የሚገኘው የትራምፕ መኖሪያ ቤት በርብረው ትልቅ ሚስጥር የተባሉትን መረጃዎች ወስደዋል። ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን በመጪው ምርጫ የሚወዳደሩት ትራምፕ ምርመራውን በማደናቀፍም ተከሰው ነበር። ትራምፕ ክሱ ባለፈው ዓመት በሚያሚ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ ተናግረው ነበር።


ዋሽንግተን     ትራምፕ በእድል ወይም በእግዚአብሔር ከሞት ተረፍኩ አሉ

ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ ከተሞከረባቸው ግድያ የተረፉት በእድል ወይም በእግዚአብሔር ነው ሲሉ ተናገሩ። ብዙዎች እግዚአብሔር እንዳተረፈኝ ይናገራሉ ሲሉ ለኒውዮርክ ፖስት ቃለ ምልልስ የሰጡት ትራምፕ ሟች ነበርኩኝም ብለዋል። በእድል ወይም በእግዚአብሔር አሁንም አለሁ ሲሉም ተናግረዋል። ትራምፕ ለዋሽንግተን ኤግዛማይነር እንደተናገሩት በወቅቱ ፍልሰትን ወደ ሚመለከተው ፖስተር ፊቴን ማዞሬ ሕይወቴን አትርፎታል ብለዋል። እሳቸው እንዳሉት አልፎ አልፎ እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ደጋፊዎቻቸው እየተመለከቱ መናገር እንደሚያዘወትሩ ገልጸዋል።ያን ባላደርግ ኖሮ ግን ዛሬ መናገር አልችልም ነበር ያሉት ትራምፕ ያከማቸው ዶክተርም መትረፋቸውን ተአምር ማለቱን ተናግረዋል።  

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።