የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ተፈናቃዮች አቤቱታ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 3 2015በቅርቡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው በዞኑ ከተማ ሻምቡ የተጠለሉ ተፈናቃዮች በቂ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው አመለከቱ ተፈናቃዮቹ ላለፉት ሶስት ሳምንታት የሚቀየር ልብስ እንኳ ሳይኖራቸው በጠባብ ክሎች ተፋፍገው እንደሚኖሩ ነው የሚገልጹት። የኦሮሚያ ክልል ቡሳጎኖፋ (አደጋ ስጋት ሥራ አመራር) በበኩሉ ለተፈናቃዮች «በቂ» የምግብ እና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ድጋፍ የዞን ከተማ በሆነችው ሻምቡ ደርሶ ለተረጂዎች እየተከፋፈለ ነው ይላል።
ወጣት ጫልቱ መኮንን በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ናት። አዳጊ ወጣቷ ወደ ቤተሰቦቿ ዘንድ ተመልሳ የእረፍት ጊዜዋን በማሳለፍ ላይ ሳለች በሆሩጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በታጣቂዎች የተከፈተባቸውን ጥቃት ሽሽት የዞኑ ከተማ ሻምቡ ውስጥ ወደ ሚገኘው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ ከመላው ቤተሰቦቿ ጋር ከተፈናቀለች እነሆ ሶስት ሳምንታት ተቆጠሩ።
አስተያየቷን ለዶይቼ ቬለ ያጋራችው ወጣቷ አሁን ከአንድ እህቷ ጋር ከ50-90 ሰዎች ተፋፍገው በሚያድሩበት ክፍል፤ ምንም ምቹ ሁኔታ ለተፈናቃዮቹ ባልተፈጠረበት ኑሮዋን ትገፋለች። የተፈናቃዮቹ መጨናነቅ የፈጠረውን ጫና መቋቋም የተሳናቸው ታናናሽ ወንድሞቿ ግን ለህመም በመዳረጋቸው ወላጆቿ በሻምቡ ከተማ የሚከራይ ቤት ፍለጋ ቢወጡም አልሆነላቸውም ትላለችም።
«በዚህ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአንድ ዶርም 80-90 እየሆነን ነው የምናድረው። እስካሁን እየረዳን ያለው ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ ነው። እንደ ጉንፋን ያለው ተላላፊ በሽታ ሁላችንም አዳርሶናል። እናትና አባቴ አሁን የኔ ታናናሾች የሆኑ ሁለት ወንድሞቼን ይዘው የቤት ክራይ ፍላጋ ወጥተዋል። እኔ አሁን ከአንዷ እህቴ ጋር ነው በዚሁ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ መቆየትን ምርጫ ያደረኩት። ያለን ንብረት ገሚሱ ተዘርፎ ሌላውም ወድሟል። ወላጆቻችን ከእንግዲህ እኛን ለማሳደግም ሆነ ለማኖር አቅም የላቸውም። እንደው ህይወታችን ለመታደግ ብለን ነው እዚህ ያለነው» ትላለች።በምዕራብ ኦሮሚያ የቀጠለው የታጣቂዎች ጥቃት ግድያ ማባባሱ
ወጣቷ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ከተፈናቃዮቹ መሃል ሆና ቃለ ምልልስ በምትሰጥበት ሰዓት የሕጻናቱ ዋይታ እና ጫጫታ ጎልቶ ይሰማል። በጃርቴ መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ያፈናቀላቸውን ክስተት ስትናገርም፤ እናት እንኳ ልጇን ይዛ ለመውጣት ዕድል እንዳልነበራት ታስታውሳለች። «ከወላጆቼ ጋር ተጠፋፍተን መንገድ ላይ እየተፈላለግን መጥተን ነው በሻምቡ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተገናኝተን የተሰባሰብነው» ስትልም የክስተቱን አስከፊነት ታስረዳለች።
ከጃርደጋ ጃርቴ የተፈናቀሉ እና በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ሌላው ተፈናቃይ እና የተፈናቃዮቹ አስተባባሪ እንደሚሉት በዚሁ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ውስጥ ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። እኚሁ ተፈናቃይ እንደሚሉት መጠለያ በመጥፋቱ በሻምቡ ከተማ መናኻሪያ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ቁጥርም ከዚህ እጥፍ የላቀ ነው።
«እኛ ያው ህይወታችን ብቻ ለማውጣት ነው ብዙዎች ሲሞቱ ቤት እየተሰበረ ሲዘረፍ ተመልከተን የወጣነው። ታግተው የተወሰዱና ይኑሩ ይሙቱ የማይታወቅም በርካቶች ናቸው። ይህንን ተመልክተን ልጆቻችን ይዘን በነፍስ ለመውጣት ሸሽተን መጣን። እስካሁን ለብሰን የወጣነውን ልብስ እንደ ለበስን ነው ያለነው። ምግብም እምብዛም የለም። እስካሁን የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በሚያደርግልን ድጋፍ ነው ህይወት የምንገፋው። በመንግሥት በኩል የሌሊት ልብስ እና የተወሰኑ ማብሰያ ተሰጥቶን ሌላው ገና እየመጣ ነው ከማለት ውጭ የደረሰን ነገር የለም» ሲሉም የአስቸኳይ እርዳታ አስፈላጊነት አንስተውልናል።በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተጠለሉ የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ተፈናቃዮች
የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በአዲስ አጠራሩ (ቡሳ ጎኖፋ) በቅርብ ጊዜው የሆሮ ጉዱሩ የተለያዩ ወረዳዎች ግጭት 61 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለተለያዩ ቀውሶች መዳረጋቸውን ያነሳል። ሻምቡን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የዞኑ አከባቢዎች በቂ የተባለውን የምግብና ምግብ ነክ የእርዳታ ቁሳቁሶች ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ወደ ስፍራው መላካቸውንም የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ ከድር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። እስካሁንም ድጋፉን የጫኑ 20 ተሸከርካሪዎቹ በስፍራው ደርሰው የ13 ተሸከርካሪ የድጋፍ ቁሳቁስ ተራግፈው ለተረጂዎች ተከፋፍለዋል ብለዋል። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተለይም በቅርቡ የነዋሪዎች መፈናቀልና ግጭት በበረታባቸው የጃርደጋ ጃርቴ እና አሙሩ ወረዳዎች ግጭት፤ ተፈናቅለው ወደ ሻምቡ ከተማ የተሰደዱቱ ተፈናቃዮች «የአማራ ታጣቂዎችን» ሲከሱ፤ ከአከባቢው ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተጠለሉት ደግሞ መንግሥት «ሸነ» ሲል በሽብርተኝነት የፈረጀውና እራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ጦ»” ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ስዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ