1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: ማንነት እና የወጣቶች ምልከታ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2017

ማንነት: በዚህ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ምልከታ የገለፁልን ተማሪ ሩሃማ ታዲዮስ እና ተማሪ ናሮቤ ስዩም ናቸው። ተማሪ ሩሃማ ማንነት በህይወታችን ውስጥ የተለየ ቦታ ልንሰጠው ይገባል ትላለች ፡፡ ተማሪ ናሮቤ በአንጻሩ ማንነት አሥፈላጊ ቢሆንም ብዙም ቅድሚያ ወይንም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን አይገባም» ስትል ሞግታለች።

https://p.dw.com/p/4loPE
ሩሃማ የ11ኛ ክፍል ናሮቢ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው ። ከአወያይዋ ሊዳን ዳኜ ጋር ቆመው
ምስል S. Wegayehu/DW

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: ማንነት እና የወጣቶች አተያይ

በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሩሃማ ታዲዮስ እና ናሮቤ ስዩም በዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ላይ እንግዳ ሆነው ቀርበዋል ፡፡ ሩሃማ የ11ኛ ክፍል ናሮቢ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው ፡፡ ሁለቱ ወጣቶች ማንነት በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ውይይት የየራሳቸውን ምልከታ ገልጸዋል ፡፡
ተማሪ ሩሃማ ማንነት በህይወታችን ውስጥ የተለየ ቦታ ልንሰጠው ይገባል ትላለች ፡፡ ማንነት ግላዊ ወይም ቤተሰባዊ በሚል ሊገለጽ እንደሚችል የጠቀሰችው ሩሃማ “ እንደ አዳጊ ሴቶች ማንነታችንን ካወቅን ራሳችንን ከሌሎች ነገሮች በመቆጠብ ህይወታችንን በአግባቡ እንድንመራ ያስችለናል፡፡ እንዲሁም ወደፊት መድረስ ያለብንን ቦታ እንድንለይ የተቀረጽንብት ማንነት የራሱ  አስተዋፅኦ አለው” ብላለች ፡፡

ሩሃማ የ11ኛ ክፍል ናሮቢ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው ። ከአወያይዋ ሊዳን ዳኜ ጋር ቆመው
ሩሃማ የ11ኛ ክፍል ናሮቢ ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው ፡፡ ምስል S. Wegayehu/DW

ተማሪ ናሮቤ በአንጻሩ ማንነት አሥፈላጊ ነው ሥትል ከሩሃማ ሀሳብ ጋር እንደምትስማማ ትናገራለች ፡፡ ነገር ግን ማንንታችን ላይ ብዙም ቅድሚያ ወይንም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን አይገባም የምትለው ናሮቤ “ ማንነት ጠቃሚ የመሆኑን ያህል አጥበቅን ከያዝነው ራስን አጥብቆ ወደ መውደድ / self center / የሆነ ባህሪ እንድንይዝ ሊያደርገን ይችላል ፡፡  ይህም ሌሎች ከእኛ የተለየ ማንንት ላላቸው ሰዎች ዕውቅና መስጠትና አብሮ ለመኖር ልንቸገር እንችላልን “ ብላለች ፡፡

ማንነት ተፈጥሯዊና አሥፈላጊ ነው የሚል እምነት እንዳለቸው የጠቀሱት ተማሪ ሩሃማ እና ተማሪ ናሮቤ “ በተለይ እኛ አዳጊ ሴቶች የበታችነትና የመሸማቀቅ ሥሜት ሊሰማን አይገባም ፡፡ ግላዊና ማህበራዊ ማንነታችንን በተገቢው ቦታ ብቻ በመጠቀም በራሳችን የመተማማን ልምድ ልናዳብር ይገባል፡፡ በተለይም የራሳችንን ዓላማ በመያዝ በትምህርት ፤ በእውቀት እና  በቴክኖሎጂ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ መጣር አለብን “ ብለዋል ፡፡

#ዝምታሰባሪአዳጊሴቶች #GirlzOffMute

ሊሻን ዳኜ / ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ልደት አበበ