ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት መታሰቢያ ምንድን ነው?
ሐሙስ፣ ጥር 25 2015« ሆሎኮስት በናዚ አገዛዝ የተCf,ጨፉ አይሁዳዉያን የሚታሰቡበት እለት ነዉ። በጀርመን ይህ ታሪክ በየትምህርት ቤቱ በታሪክ ትምህርትነት ከጎርጎረሳዉያኑ 1968 ዓ.ም ጀምሮ መሰጠት ሁሉ ተጀምሯል።ጀርመናዉያን አሁን ይህንን የግፍ ታሪክ በይፋ መናገራቸዉ ያስመሰግናቸዋል።»
በጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ እንዲሁም የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ፤ ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የዋለዉን፤ የሆሎኮስት መታሰብያ ማለትም በናዚ ጀርመን በግፍ የተጨፈጨፉ አይሁዳዉያን የሚታሰቡበት ቀንን በተመለከተ፤ ከሰጡን ቃለ-ምልልስ የተወሰደዉን ነዉ። ባለፈዉ አርብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በናዚ በግፍ የተጨፈጨፉ ከ 5,6 እስከ 6,3 ሚሊዮን የሚደርሱ የአዉሮጳ አይሁዳዉያን ሰለቦች ታስበዋል። በጎርጎረሳዉያኑ ጃንዋሪ 27 ማለት ጥር 27 እለት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የሚታሰበዉ ይህ እለት በጀርመን በይፋ ከጎርጎረሳዉያኑ 1996 ዓመት ጀምሮ በተለያዩ ሥነ-ስርዓቶች መታስብ ጀምሯል።
የተመድ በጎርጎረሳዉያኑ ህዳር ወር 2005 ዓ.ም ባካሄደዉ ጠቅላላ ጉባዔ መጠናቀቅያ ላይ ይፋ ባደረገዉ የአቋም መግለጫ፤ ጥር 27 ማለትም በየዓመቱ ጃንዋሪ 27 እለትን ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት እልቂት መታሰቢያ ቀን ሲል ማወጁ ይታወቃል። እለቱ በዓለም ላይ ከነበሩት አይሁዳዉያን መካከል "አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብሎም ሌሎች አናሳ የተባሉ በናዚ በግፍ የተገደሉበት መታሰብያ እለት በመሆኑ፤ ሰዎች አለመቻቻል ፣ ዘረኝነትና ጭፍን ጥላቻ፤ ስለሚያስከትለው አደጋ ለዓለም ህዝብ ሁሉ የዘላለም ማስጠንቀቂያ ሆኖ እንዲያገለግል የታሰበ ነዉ ሲል" የተመድ እለቱን በመታሰብያነት የበየነበትን ምክንያት ገልጿል። የመጀመሪያው የዓለም አቀፉ የሆሎኮስት መታሰቢያ እለት በጎርጎረሳዉያኑ ጥር 27 ፤ 2006 ዓ.ም የታሰበ ሲሆን በዚሁ እለት በተካሄደዉ ሥነ-ስርዓት ላይ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የነበሩት ኮፊ አናን "የእልቂቱ ልዩ መሆን እና አሳዛኝ ክስተት ሊመለስ ሊታረም የማይችል ነው። የሰው ልጅ ግን የማስታወስ ችሎታዉ ዘላቂ እስከሆነ ድረስ ይህንን ሁኔታ በኀፍረት እና ፀፀት በማስታወስ ከአሰቃቂ ሁኔታ ራሱን ሊታደግ እና ሊያነቃ ይገባል" ሲሉ ተናግረዉ ነበር። የጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ ፤ የታሪክ ምሁርና በጀርመን ታዋቂ ደራሲ የሆኑት ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ፤ ስለሆሎኮስት መታሰብያ እለት ነግረዉናል።
«የሆሎኮስት ቀን በዓለም አአፍ ደረጃ ነዉ የሚከበረዉ። በእርግጥ እለቱ በጀርመን ትኩረት ተሰጥቶት ነዉ ታስቦ የሚዉለዉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥር 27 እለት በየዓመቱ እንዲታሰብ ከአወጀ በኋላ በዓለም አአፍ ደረጃ ይታሰባል።»
መታሰብያ እለቱ ለምን ጥር 27 ቀን ሆነ?
የመንግሥታቱ ድርጅት የሆሎከስት መታሰብያ ጥር 27 እንዲሆን ለምን እለቱን መረጠ? በጎርጎረሳዉያኑ ጥር 27 ቀን 1945ዓ.ም የሶቪዬት ህብረቱ ቀዩ ጦር ሠራዊት በአሁንዋ ፖላንድ ዉስጥ የሚገኘዉን የናዚ ከፍተኛ ማጎርያ እና የጭፍጨፋ ካምፕ አውሽዊትዝ ቢርከናውን ነፃ ያወጣበት እለት በመሆኑ ነዉ። ቀዩ ጦር የማጎርያ ካንፑን ከናዚ እጅ ነፃ ሲያለቅቅ በማጎርያዉ ዉስጥ የነበሩት ጥቂት በሕይወት የተረፉ ነገር ግን በስቃይ ላይ የነበሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ። የናዚ ጦር እንደ ራሱ ግዛት ተቆጣጥሮት የነበረዉን እና በአሁኑ ጊዜ ፖላንድ ዉስጥ የሚገኘዉ ኦሽዊትዝ ቤርክናዉ በተባለዉ የናዚ ማሰቃያና ማጎርያ ስፍራ ዉስጥ ብቻ 1.1 ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች በግፍ ተግድለዋል። አብዛኞቹ ተገዳዮች ማለትም 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑት አይሁዳውያን ነበሩ። ኦሽዊትዝ በአውሮጳ ናዚ ጀርመን የጅምላ ጭፍጨፋ ከፈጸሙባቸው በርካታ ቦታዎች አንዱ እና ግዙፉም እንደሆነ ይነገራል። ናዚ ጀርመን በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ለ 12 ዓመታት የፈፀማቸዉ ግፎች ከምንም የማይስተካከል ግፍ እንደሆነ በጀርመን ታዋቂ ደራሲዉ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ ተናግረዋል።
በጎርጎረሳዉያኑ 1945 ዓ.ም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዳውያን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጂፕሲ ወይም ሮማንስ የሚባሉት እንዲሁም፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ፈጻሚዎች፣ ወንጀለኞች ፣ የግዳጅ ሠራተኞች፣ የጦር እስረኞች፣ የጆሆቫ እምነት አራማጆች እንዲሁም ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው አናሳ የተባሉ ማኅበረሰቦች የናዚ የግፍ ጭፍጨፋ ሰላቦች ነበሩ። የጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ ዘንድሮ በተለይ በማንነታቸዉ በናዚ የተጨፈጨፉ ሰለቦችን አስታዉሷል። ክላዉስ ሺርድቫን የተባሉት በጀርመን የተመሳሳይ ፆታ ጉዳይን የሚከታተሉ ግለሰብ እንደተናገሩት፤ ይህ ጉዳይ በይfa እስኪነገር ብዙ ጊዜ ወስዷል።
«አሁንም ድረስ ልብ የሚነካ ነገር እንዳለ ነዉ የምንገነዘበዉ። እነዚህ ማኅበረሰቦች በጀርመን እዉቅና እና ክብርን እስኪያገኙ ድረስ ብዙ ጊዜ ወስዷል» የጀርመን ፓርላማ ፕሬዚዳንት ቤርብል ባስ በመታሰብያ ስነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በጀርመን ፀረ ሴማዊነት አሁንም መታየቱ አሳዛን ነዉ። «ጀርመን ዉስጥ በየቀኑ በአማካይ አምስት የፀረ-ሴማዊ ወንጀሎች እንደሚከሰት ተመዝግበዋል። ለምሳሌ የመታሰቢያ ዝግጅቶች ላይ ችላቻ ይነዛልl፤ የአይሁድ ተቋማትና ምኩራቦች ላይ ጥቃት ይሰነዘራል፣ ሰዎች አይሁዶች በመሆናቸው የጥላቻ እና ዛቻ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል። ይህ ታድያ ለሀገራችን ውርደት ነው። »
በጀርመን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ያጠናቀቁት እና የጀርመንን ታሪክ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት በጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ፤ የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ፤ የናዚ ጭፍጨፋ ከአይሁዳዉያን ሌላ አናሳ ይባሉ የነበሩ ማኅበረሰቦች ላይ ያነጣጠሮም እንደነበር ተናግረዋል።
ክላዉስ ሺርድቫን የተባሉት በጀርመን የተመሳሳይ ፆታ ጉዳይን የሚከታተሉ ግለሰብ በበኩላቸዉ፤ በጀርመን ፓርላማ ባለፈዉ ዓርብ እለት የተሰጠዉ ልዩ መታሰብያ ለማህበረሰቡ የተላለፈ መልዕክት እንደሆነ ነዉ የተናገሩት። "መታሰቢያ ሥነ-ስርዓቱ ለዕውቅና የተሰጠ ምልክት ከመሆኑም በላይ ለማኅበረሰቡ የተላለፈ መልዕክትም ነው።"
በእስራኤል ዉስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታሰበዉ የሆሎኮስት መታሰብያ እለት ጥር 27 እለት ለሁለት ደቂቃ ያህል፤ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ጥሪ በመላ ሀገሪቱ ይደወላል። ሰዉን ጨምሮ አውቶብስ፤ መኪና፤ ሁሉም የሚንሳቀስ ነገር ሁሉ ያቆማል። ሰዎች በሁለተኛዉ ዓለም የአስራ ሁለት ዓመታት ጦርነት ጊዜ፤ የናዚ የጥቃት ሰለባዎቹን ያስባሉ። በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚ ጦር አይሁዳዉያንን፤ እና ሌሎች አናሳ የተባሉ ማኅበረሰቦችን እየለየ ማጥቃቱ ለምን ይሆን?
በጀርመን የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ እና ታዋቂዉ ደራሲ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ ይህ አይነቱ የግፍ ጭፍጨፋ የበታችነት ስሜት የወለደዉ መሆኑን ተናግረዋል።
ስለዓለም አቀፉ የሆሎኮስት መታሰቢያ እለት ምንነት እና ስለዘንድሮዉ የአከባበር ሁኔታ የተጠናቀረዉን ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ