«ወጣቶችን ከጎዳና ማንሳትና ፈተናው»
ዓርብ፣ ጥቅምት 7 2012የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኑሮዋቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን በተለይም ወጣቶችን በጀት መድቦ የማቋቋም ስራ እየሰራ እንደሆነ ይናገራል። ይህም ካለፈው ዓመት 2011 ዓ ም አንስቶ ተጠናክሮ እንደቀጠለ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አለሙ አሰፋ ይናገራሉ። « በአጠቃላይ እስከ 3500 ዜጎችን የማቋቋም ስራ ነው የተሰራው ከነዚህ መካከል 1400 የሚሆኑትን ከቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።» አብዲ ፣በአዲስ አበባ ሰርቶ ለመኖር ከወሰኑት የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል አንዱ ነው። ወጣቱ ባለፈው ዓመት በመንግሥት ድጋፍ የሙያ ስልጠና አግኝቶ የስራውንም ዓለም ለአንድ ወር ያህል ተቀላቅሎ ነበር። ይሁንና ከወራት በኋላ ኑሮውን መልሶ ጎዳና ላይ አድርጓል። « ልብስ ስፌት ሰልጥኜ ነበር። ስልጠናው ግን እንደው አለፋችሁ እንድንባል ነው እንጂ ብቁ አላደረጉንም» ሲል ይተቻል።የ 26 ዓመቱ አብዲ መንግሥትን የሚወቅሰው ራሳችንን ለመቋቋም የሚሆነን በቂ ገንዘብ አልሰጠንም በሚል ነው።ከዚህ በተጨማሪም በቂ ስልጠና አለማግኘታቸውንም እንደ ችግር ያነሳል። « መንግሥት ለመቋቋሚያ የሰጠን ገንዘብ ትንሽ ነው። ከ4000 ብሩ 3000ውን ከዛው ከመጠለያችን ሳልወጣ ነው የጨረስኩት። ለምንም ነገር አይሆንም»
ዳንኤል ብለን የምንጠራው ወጣት እንደ አብዲ በልብስ ስፌት ሰልጥኖ አሁንም በስራ ላይ ይገኛል። ወጣቱ ለስድስት ወር እንደሰለጠነ ነው የነገረን። ይሁንና መንግሥት በቅጡ አላቋቋመንም ሲል እሱም ይወቅሳል። « ከማሰልጠኛ ውጡና የራሳችሁን ቤት ተከራዩ ተባልን። 4000 ብሩ ለመቋቋሚያ በቂ አይደለም። ከምንኖርበት በጉልበት አስወጡን።»
የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አለሙ እንደሚያብራሩት ከሆነ ወጣቶቹ የተሰጣቸው መቋቋሚያ 4000 ብር ፣ሥራ ከጀመሩበት መሥሪያ ቤት ደሞዝ እስኪከፈላቸው ድረስ በቂ ነበር። « 4000 ብር የምንሰጣቸው እኛ መሠረታዊ የሆነውን የመቋቋሚያ ስራ ሰርተን ነው። ጥቅምት 1 የተቀጠረ የጎዳና ተዳዳሪ ደሞዝ የሚከፈለው ጥቅምት 30 ስለሆነ እስከዛው የሚበላው ነገር ስለማይኖረው፣ ለቤት ኪራይ፣ ለትራንስፖርት እና ለአልባሳት የሚሆን የመቋቋሚያ ፓኬጅ ነው።» ይላሉ አቶ አለሙ።
ዳንኤል በ800 ብር ቤት ተከራይቶ እንደሚኖር እና ለምግብ፣ ለትራንስፖርት እና ለሌሎች መሰረታዊ ነገሮች የሚተርፈው 400 ብር ብቻ እንደሆነ ገልፆልናል። በዚህ የተነሳም ወደ ጎዳና ህይወት እንዳይመለስ እሰጋለሁ ይላል። « ላለመውጣት እየሞከርኩ ነው። እኛም ጫፍ ላይ ነን። ፋብሪካ እየሰራሁ። ከጓደኞቼ ገንዘብ እየተበደርኩ ነው። ኑሮዬ እንደበፊቱ ነው። ምግብ እንኳን ከሆቴል እየለመንኩ ነው።»
አቶ አለሙ ወጣቶቹ ተከፈለን የሚሉትን ደሞዝም ያስተባብላሉ። ምንም እንኳን አብዲ እና ዳንኤል የተቀጠሩበት ደሞዝ ዝቅተኛ ከሚከፈላቸው የሙያ ዘርፎች ውስጥ ቢሆንም ሊሻሻል የሚችል እንደሆነ ያስረዳሉ። « በርግጥ የ2000 በታች የሚከፈላቸው አሉ። ይሔ ግን የመነሻ ደሞዝ ነው። በዛ ላይ በቀን ስምንት ሰዓት ከሆነ የሚሰሩት አራት ሰዓት ጨምረው ደሞዛቸውም በዛ ልክ ያድጋል። »
የጎዳና ተዳዳሪዎች የነበሩት ዳንኤልም ሆኑ አብዲ ከሱስ ነፃ ነን ይላሉ። ራሳቸውን ለማስተዳደርም ብቁ እንደሆኑ ይናገራሉ። መንግሥት እነዚህን ወጣቶች በሙያ ካሰለጠነ በኋላ ምን ያህል መርዳት ይገባዋል? ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የሶይሶሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው ያገለገለሉት ዶክተር የራስ ወርቅ አድማሴ ከአሁን በኋላ ያለው የወጣቶቹ ድርሻ ነው ይላሉ። « አንድ አቅሙ የደረሰ ሰው ኃላፊነት ይወስዳል። ሁልግዜ ለመወደድ መንግስት እንዲህ ማድረግ አለበት ማለት አያስፈልግም። መንግሥት ይህን መስራት ከጀመረ ቆይቷል። » ዶክተር የራስ ወርቅ እንደሚሉት ሌላም ችግር አለ። « ብዙ በሱስ የተጠቁ ልጆች አሉ። እነዚህን ልጆች በማስገደድ ካልሆነ በስተቀር በፍቃደኝነት ሊተው አይችሉም።»
በዓለም ባንክ ድጋፍ በ2012 ዓ ም ከኢትዮጵያ 11 ከተሞች 22,000 የሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳት እቅድ ተይዟል። ይህም በእነዚህ 11 ከተሞች ጎዳና ላይ ይኖራሉ ተብሎ ከተጠናው ኢትዮጵያዊ አንድ አራተኛ ያህል መሆኑ ነው። 13 000 ያህሉ ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ እንደሚነሱ ተነግሯል።
ልደት አበበ
ሂሩት መለሰ