1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቱ ስለ ኮሮና ክትባት ምን ማወቅ ይኖርበታል?

ዓርብ፣ ነሐሴ 21 2013

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 2,3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮቪድ-19 መከላከያ መከተባቸውን የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዕለታዊ መግለጫ ይጠቁማል። ክትባቱ በአስራዎቹ ለሚገኙ ወጣቶች ገና መሰጠት አልተጀመረም። ይሁንና ወጣቱ ስለ ክትባቱ ምን ያህል ግንዛቤ አለው? ምንስ ማወቅ ይጠበቅበታል?

https://p.dw.com/p/3zXDn
USA Impfung Jugenliche
ምስል Jeff Kowalsky/AFP/Getty Images

ወጣቱ ስለ ኮሮና ክትባት ምን ማወቅ ይኖርበታል?

ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስተኛው ዙር የኮሮና ስርጭት ማዕበል እየጀመረ መሆኑን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ሰሞኑን ጠቁመዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ክትባት እየተሰጠ ያለው አዲስ አበባ ውስጥ ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ነው። ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ሆነው ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ወይም በሥራቸው ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችም መከተብ እንደሚችሉ ጤና ሚኒስቴር ይጠቁማል። በክልሎች ደረጃ ደግሞ ዕድሜው ከ55 ዓመት በላይ የሆነው ነው። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መከተብ ቢፈልጉ እንኳን ተጓዳኝ ህመም ወይም በሥራቸው ምክንያት ለበሽታው ተጋላጭ ካልሆኑ ዕድሉ የላቸውም። ይሁንና ዕድሉን ቢያገኙ ለመከተብ ምን ያህል ፍቃደኛ ናቸው? ስለ ክትባቱስ ምን ያህል ያውቃሉ? 
ዮናስ 20 ዓመቱ ነው። መከተብ አለመከተቡን በራሱ መወሰን ይችላል። የኮሮና መከላከያ ክትባት መከተብ አይፈልግም። ይህም « በክትባቱ ላይ እምነት ስለሌለኝ ነው»
የ 22 ዓመቷ ብርቱካን ግን ዕድሉን ብታገኝ « የተሞከረ እና ውጤጣታ የሆነ ክትባት ነው ያለው»በሚል ከመከተብ ወደኋላ አትልም። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ንጉሡ ደግሞ በኮሮና በሽታም ይሁን በመከላከያ ክትባቱ ላይ ያለው አመለካከት ከሌሎቹ ወጣቶች ጨርሶ የተለየ ነው። ከክትባት ይልቅ ዝንጅብል እና በርበሬን ይመርጣል። « ለበሽታው ቦታ አልሰጠውም።» የሚለው ንጉሡ ባህላዊ መድኃኒቶችን ይጠቀማል። በሽታውን ከከባድ ጉንፋን ለይቶም አያየውም። መክሊት በአንፃሩ በሽታውን እንደ ጉንፋን አቅልላ አታየውም። ተመርምራ አይረጋገጥ እንጂ ከዚህ ቀደም ዮኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የያዛት ኮሮና ለመሆኑ አትጠራጠርም። በዚህም የተነሳ  የ20 ዓመቷ ተማሪ መከተቡን ትመርጣለች። « ምልዕክቶቹን አሳይቼ ነበር። ነገር ግን በቂ መመርመሪያ ስላልነበራቸው አልመረመሩኝም።»
የኮሮና መከላከያ ክትባትም ቢሆን እንደ ማንኛውም መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በተለይ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ከክትባቱ በኋላ የደም መርጋት መከሰቱ አስትራዜኔካ የተባለውን ክትባት ስም አጠልሽቶ ነበር። ጀርመን ሀገር ላይ እንደውም ለተወሰነ ጊዜ ክትባቱ ከ 60 ዓመት በታች ላሉ ሰዎች እንዳይሰጥ ተከልክሎ ነበር። ይህም የዚህ የደም መርጋት የደረሰባቸው ሰዎች ከዚህ ዕድሜ በታች ስለነበሩ ነው። አሁን ላይ ግን ማናቸውም 18 ዓመት  የሆናቸው ሰዎች ክትባቱን በፍላጎት መውሰድ ይችላሉ። ባዮንቴክ ወይም ፋይዘር እና ሞደርና የተባሉት የኮሮና መከላከያ ክትባቶች ደግሞ ከ16 ዓመት ጀምሮ ያሉ ወጣቶች እንዲከተቡ የተፈቀደ ሲሆን ከዚህ ወር አንስቶ እንደውም ከ 12 ዓመት ጀምሮ ያሉ አዳጊ ወጣቶችም ቢከተቡ ስጋት እንደሌለው የጀርመን የክትባት ኮሚሽን STIKO አስታውቋል። ዩናይትድ ስቴትስ 10 ሚሊዮን ገደማ የሚደርሱ ወጣቶችን ከትባለች።  ከተከተቡት ውስጥ ከ 10 ሺ ወጣት ውስጥ አንድ ወጣት ላይ ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የልብ ጡንቻ መቁሰል ተከስቷል። ችግራቸውም በህክምና መፍትሄ ማግኘት ችሏል። 
18 ዓመት ያልሞላቸውን ልጆች ለመከተብ ደግሞ የወላጅ ወይም የአሳዳጊን ፍቃድ ያሻል። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፍሬህይወት የ 13 ዓመት ልጅ አላቸው። ዕድሉ ቢኖር ልጃቸውን ያስከትባሉ። ራሳቸውም እድሉን ቢያገኙ ለመከተብ ፍቃደኛ ናቸው።
የኮሮና ክትባት አዲስ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገልግሎት ላይ እንደመዋሉ መጠን በተለይ መጀመሪያ ላይ ክትባቱ በተጀመረባቸው የምዕራቡ ሃገራት የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ ሳይቀር በአስተማማኝነቱ እና ሊያደርስ በሚችለው የጎንዮች ጉዳት ምክንያት ከፍተኛ ስጋት ነበር። 
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎች የ COVID-19 ክትባቶች ዘረመልን  ወይም DNA ይለውጣሉ የሚሉ ወይም  የተከተቡ ሰዎች እጃቸው ላይ ብረት ነክ ነገር ቢያስቀምጡ እንደ ማግኔት ይስባሉ የመሳሰሉ መላ ምቶች በቪዲዮ መልክ ያቀርባሉ። የክትባቱ ተቃዋሚዎች ደግሞ ይህንን አደገኝነቱን ለመግለፅ ይጠቀሙበታል። 
እስካሁን ድረስ ግን ኮቪድ 19 ን ከመከላከል አንፃር ከክትባት ውጪ አማራጭ መድኃኒት በዓለማችን የለም። ክትባት መከተብ በተህዋሲው ከመያዝ ባያድንም ሰዎች በተሐዋሲው ቢያዙ ከባድ ህመሞች እንዳይከሰቱ እንደሚከላከል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። በዚህም የተነሳ እንደ ጀርመን ያሉ ሃገራት ሰዎች እንዲከተቡ ግፊት እያደረጉ ነው። ይህንንም የሚያደርጉት ለተከተቡ ሰዎች በሽታውን ለመከላከል የተቀመጡ ግዴታዎችን በማላላት ወይም ጨርሶ በመፍቀድ ነው። 
እስካሁን በዓለም ላይ 33 በመቶው ሕዝብ መከተቡን መረጃዎች ያመለክታሉ። ቻይና፣ ህንድ እና ዩናይትድ ስቴትስ ብዙ ሰዎችን በመከተብ ቀዳሚ የሚባሉት ሃገራት ናቸው። ጀርመን ሀገር 59,5 በመቶ ያህሉ ሙሉ ክትባት አግኝተዋል። እንደዛም ሆኖ አራተኛው የወረርሽኝ ዙር ጀምሯል። ሮበርት ኮኽ የተባለው የጀርመን የምርምር ተቋም እንደሚለው ከሆነ በዚህ በአራተኛው ዙር በብዛት በበሽታው ተጠቂ እየሆኑ ያሉት ወጣቶች ናቸው። ክትባት አማራጭ ይሆን? ሁሉም ለእየራሱ አመዛዝኖ የሚመልሰው ይሆናል።

Äthiopien l Start der COVID-19-Impfung
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 2,3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ወስደዋልምስል Solomon Muchie/DW
Data visualization: COVID-19 global new case numbers trend - map calendar week 34, 2021

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ