ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በአማራ ክልል በሰብል ላይ ያደረሰው ጉዳት
ረቡዕ፣ ኅዳር 5 2016በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ባልተሰበሰቡና ተሰብስበው ወደ ጎተራ ባልገቡ በሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ አርሶ አደሮች ተናገሩ፣ ብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትጠዩት በበኩሉ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች እንደሚቀጥልና አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ሰብስቦ በአግባቡ እንዲያስቀምጥ አሳስቧል፡፡
በአማራ ክልል የ2016 ዓ ም የግብርና ሥራ በማዳበሪያ እጥረትፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ላይ ቢደርስም አሁንም ከፈተና እንዳልወጣ አርሶ አደሮች ይናገራሉ፣ በተለይ አሁን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በብዙ አካባቢዎች ለምርት ብክነት ምክንት እየሆነ ነው፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል ሁለቱን አነጋግረን ነበር፣ ያልተጠበቀ ዝናብ ማሳ ላይ በነበረ የጤፍ፣ አተርና ባቄላ ሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል፣ ታጭዶ የተከመረ ቦቆሎም በዝናቡ ምክንያት ባለበት መብቀል ጀምሯል ነው ያሉት፡፡ አንድ የሰሜን ጎጃም አርሶ አደርም በተመሳሳይ የተሰበሰበውን ሰብል ወቅቶ ወደ ጎተራ ለማስገባት ዝናቡ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በተለይ ለመሰብሰብ የደረሰ የዳጉሳ ሰብል ዝናቡ በፈጠረው ጫና ምክንት መሰብሰብ ባለመቻሉ ባለበት እየረገፈ፣ ቀሪውም ባለበት እየበቀለ ነው ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዳህና ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አቶ ዘነበ ማሞ መወረዳው በሚገኙ 15 ቀበሌዎች ላይ የጣለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በ5ሺህ496 ሄክታር ላይ በነበረ የጤፍ፣ የቦቆሎ፣ የማሽላ፣ የገብስ፣ የአተር፣ የባቄላ የተልባ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከ8ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮች ለጉዳት መጋለጣቸውን ገልጠዋል፡፡
በብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚትዮሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ የበጋ ወራት ዝናብ ተጠቃሚ ባልሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብሲጥል እንደነበር አስታውሰው፣ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የምስራቅና መካከለኛው የፓስፊክ ውቅያኖስና የሰሜናዊና ምዕራባዊ የህንድ ውቅያኖስ ከመደበኛው በላይ መሞቅ የሚፈጥረው ክስተት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ለቀጣዮቹ 10 ቀናትም ዝናቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የትንበያ መረጃዎችን ጠቅሰው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ አመልክተዋል፡፡ በአንፃሩ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እየቀነሰ እንደሚሄደ አብራርተዋል፡፡
በብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ስሌት በኢትዮጵያ 3 ወቅቶች ሲኖሩ አሁን ያለንበት ከጥቅምት እስከ ጥር ያለው ጊዜ የበጋ ወቅት ሲሆን፣ ለሶማሌ ደቡባዊ ክፍል፣ ለጉጂ፣ ለቦረና፣ ለሲዳማ፣ ለደቡብ ኢትዮጵያና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደ ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ተደርጎ እንደሚወሰድ ዶ/ር አሳምነው ተናግረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ