መፈንቅለ መንግሥት የደጋገማት ቡርኪናፋሶ
ቅዳሜ፣ መስከረም 19 2016ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረው የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ ኹንታ በዚህ ሳምንት የተቃጣበትን መፈንቅለ መንግሥት ማክሸፉን ይፋ አድርጓል። የወታደራዊ አቃቤ ሕግ እንደገለጸውም በመፈንቅለ መንግሥቱ እጃቸው እንዳለ የተጠረጠሩ መኮንኖች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ሌሎች በሽሽት ላይ መሆናቸውን ያመለከተው የአቃቤ ሕጉ መግለጫ ስለመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ መረጃዎችን አጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። የታሰሩት መኮንኖች ማንነት ይፋ ባይደረግም በሀገር ደህንነት ላይ በማሴር መጠርጠራቸው ተገልጿል። ከሳምንታት በፊት ነበር የቡርኪናፋሶ ጦር ኃይል አቃቤ ሕግ በገዢው ኹንታ ላይ ሲያሴሩ ደረስኩባቸው በሚል ሦስት ወታደሮችን ያሰረው። መርማሪዎች «ወታደሮች እና የቀድሞ በወታደራዊ ስለላ ይሰሩ የነበሩ» ትራዎሬን ጨምሮ በወታደራዊ ኹንታው ውስጥ የሚገኙ ቁልፍ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች የሚያዘወትሯቸው አካባቢዎች ሲያደርፍጡ እንደነበር ጥቆማ እንደደረሰውም አቃቤ ሕጉ አመልክቷል። ዓላማው በጊዜያዊው ወታደራዊ አስተዳደር ቃል የተገባው ምርጫ ከመድረሱ በፊት በሀገሪቱ አለመረጋጋት እና ውጥረት መፍጠር እንደሆነም ተገልጿል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ያለፈው በተደረገ በዓመቱ የተፈጸመ ሲሆን ኢብራሂም ትራዎሬን ሥልጣን ላይ ያወጣው የመንግሥት ግልበጣም ከመፈጸሙ ስምንት ወራት አስቀድሞም ሌላ ሙከራ ተደርጓል። እንደውም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎቹ መክሸፍ ያስከተለው ቁጣ የጀሃዲስቶችን ጥቃት እንዳባባሰው ነው የሚነገረው። በዚህ ሳምንት የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት መክሸፉ ይፋ ከሆነ በኋላ ትራዎሬ በማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው ብቅ ብለው፤ «ሙሉ ሉአላዊነታችንን ወደምናረጋግጥበት ምርጫ ሀገሪቱን ለማድረስ የሽግግሩን ሂደት ለመምራት ቁርጠኛ ነኝ» የሚል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ዜና ይፋ ከሆነ በኋላ ደጋፊዎቻቸው በዋና ከተማ ኦጋዱጉ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ከተሞች ጎዳናዎች ወጥተው ለእሳቸው ድጋፋቸውን በመግለጽ ሙከራውን አውግዘዋል። ስሙ ያልተገለጸው ከትራዎሬ ደጋፊዎች አንዱ፤
«የአፍሪቃ ወጣቶች ሁሉ፤ የእናንተ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ነው ችግር ውስጥ የገባው። አታንቀላፉ፤ አትተኙ፤ ድምጻችሁን አሰሙ፤ አትተኙ።»
በማለት ለአፍሪቃውያን ወጣቶች ጥሪውን አቅርቧል። በሌላ በኩል የሀገሪቱ መንግሥት በቡርኪናፋሶ ጦር ኃይል ውስጥ ውጥረት መኖሩን የሚገልጹ ሁለት ዘገባዎችን በተከታታይ ያተመውን በፈረንሳይ ቋንቋ የሚታተመውን ዠን አፍሪክ የተሰኘ ጋዜጣ ማገዱ ቅሬታም አስከትሏል። ድርጊቱን የተቃወመው የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን እርምጃው ቡርኪናዎች ስለሀገራቸው ፖለቲካዊ ሁኔታ ገለልተኛ ድምፅ እንዳይሰሙ፤ ጋዜጠኞችም በነጻነት ሥራቸውን እንዳያከናወኑ እንቅፋት ነው በማለት አውግዟል። የቡርኪናፋሶ መንግሥት የዜና ምንጩን የሀገሪቱን ጦር ኃይል ዋጋ ለማሳጣት እየሞከረ ነው በማለት ከሷል።
የኢብራሂም ትራዎሬ ያልተጨበጠ ተስፋ
ኢብራሂም ትራዎሬ ሥልጣን ላይ በወጡበት ወቅት በሁለት እና ሦስት ወራት ውስጥ የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ የማሻሻል ዕቅድ ይዘው ነበር። ሆኖም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ቡርኪናፋሶ ከጀሀዲስት ጥቃት አልተላቀቀችም። ባለፈው ዓመት መስከረም ወር መገባደጃ ላይ በጊዜያዊ ፕሬዝደንነት የተሰየሙት ትራዎሬ በጦሩ ውስጥ ያሉትን ትናንሽ ያሏቸውን በርካታ የአቅርቦት ችግሮች ማስወገድ አካባቢውን ለመቆጣጠር እንደሚያስችላቸው ተናግረው ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የአልቃይዳ እና እራሱን እስላማዊ መንግሥት በሚለው ቡድን ተጓዳኞች አማካኝነት ለሚሰነዘረው ጥቃት ጠንካራ ምላሽ መስጠት ላይ አተኩረዋል። ለጦር ኃይሉ ድጋፍ የሚሰጡ አባት ሀገርን ከጥቃት ለመከላል በሚል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የበጎ ፈቃደኞች ምልመላም አካሂደዋል። የጅሃዲስቶችን እንቅስቃሴ አመክናለሁ በሚልም የጦር ሄሊኮፕተሮች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችንም አግኝተዋል፤በሜዳው እየተገኙም ወታደሮችን ለማበረታታት ሞክረዋል። የሀገሪቱ የግል ጋዜጦች እንደሚሉት ትራዎሬን ወደ ፖለቲካው መድረክ የሳበው የቡርኪናፋሶ ችግር ገና አልተፈታም። በ34 ዓመታቸው የሀገሪቱን ግዛት አስከብረው በመጪው ሰኔ ወር ምርጫ ለማካሄድ የሽሽግር ሂደቱን ለመምራት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ትራዎሬ የዓለም ወጣቱ መሪ ነበሩ። በወቅቱ በብዙዎች ልብም የሀገሪቱ የጸጥታ ችግር መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋም አሳደሩ። አካባቢውን ለመቆጣጠር በርካታ ጥረቶች ቢያደርጉም ሁኔታዎች እንደውም እየባሰባቸው መሄዱን የሳህል አካባቢ የጸጥታ ጉዳይ አዋቂ ላሲና ዲራ ይናገራሉ።
የቀጠለው የሽብር ጥቃት
በጎርጎሪዮሳዊው 2015 በተለያዩ ጥቃቶች ቡርኪናፋሶ ውስጥ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ካለፈው ዓመት ጥር ወር ወዲህ ብቻ ባሉት ጊዜያት ደግሞ በተመሳሳይ ጥቃት የሞቱት ከስድስት ሺህ እንደሚበልጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያጠናቀሩት መረጃ ያመለክታል። ምንም እንኳን የጥቃቱ ዋና ኢላማዎች ጦር ኃይሉ እና መንግሥታዊ ተቋማት ቢሆኑም ሲቪሉ ኅብረተሰብ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መሆኑንና ከአራት ትምህርት ቤቶች አንዱም መዘጋቱንም ዘገባዎች ይገልጻሉ። የዛሬ ስምንት ዓመት ሁለት ሚሊየን ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። የትራዎሬ አስተዳደር ግን ጀሃዲስቶቹን ከአካባቢው በማባረር 190 ሺዎቹን ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ አድርጌያለሁ ይላል።
የአገዛዙ ደጋፊዎች የትራዌሬን ውሳኔ በደስታ መቀበላቸውን ነው የሚገልጹት። እንደውም በዚህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተፈጸመ ግድፈት የለም ሲሉም ይሞግታሉ። ጥቃቱ የተባባሰው የሀገሪቱ ወታደሮች በቂ ትጥቅ ስላልነበራቸው ነውም ባይ ናቸው። ቡርኪናፋሶ የፈረንሳይ ኃይሎችን በግዛቷ መገኘት እየተቃወመች ከሩሲያ ጋር ያሳየችው መቀራረብ ትችት እያስከተለባት ነው።
የፈረንሳይ ወታደሮች በሀገሪቱ መሰማራት ያመጣላቸው ለውጥ እንደሌለ የተናገሩት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባሶሎማ ባዚ የሀገራቸውን ጸጥታ እራሳቸው ለማረጋገጥ እንሠራለን በማለት ለቀረበባቸው ወቀሳ ምላሽ ሰጥተዋል።
«ደህንነታችን ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በራሳችን ይረጋገጣል ፤ በሌላ በማንም ሊሆን አይችልም። የቫግነርን ቡርኪናፋሶ ውስጥ መገኘት በተመለከተ በፈረንሳይ ቁጥጥር ሥር ባለው ፕረስ ነው የተዘገበው። ለዚህ ምላሽ አለኝ፤ የእኔ ፕሬዝደንት እኛ የቡርኪናፋሶ ቫግነሮች ነን። አዎ ይኽ ጀግና መከላከያና የጸጥታ ኃይል እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ተከላካይ ኃይላችን የቡርኪናፋሶ ቫግነሮች ናቸው።»
ቡርኪናፋሶከፈለገችው ተጓዳኝ ሀገር ጋር እንደምትተባበር በመግለጽም ከሩሲያ፣ ቱርክ፤ ኢራን እና ቬንዝዌላ ጋርም አብራ በትብብር ለመሥራት እንደምትንቀሳቀስም አመልክተዋል። በዚህ መሀልም የመንግሥት የመረጃ ተቋም በትናንትናው ዕለት በማዕከላዊ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል የመንግሥት ኃይሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን በአየር ጥቃት መምታታቸውን ገልጿል። ጥቃቱ የተፈጸመው የታጣቂዎቹ መደበቂያ ከአየር በተደረገ ክትትል ከተደረሰበት በኋላ ነው። የሀገሪቱ ወታደሮችም ታጣቂዎቹ እንደመሸጉባቸው በተገለጸው ጫካዎች ውስጥ ተሰማርተው ጥቃት ማድረሳቸውም ተነግሯል። የጥቃቱ አማባራት የትራዎሬ ጊዜያዊ መንግሥት በአንድ ዓመት ውስጥ ሀገሪቱን ከከረመችበት ችግር ማውጣት አልቻለም በሚል እያስተቸ ነው።
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር