1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እገታ፣ግድያና ሁከት በኦሮሚያ ክልል

ሐሙስ፣ ሰኔ 15 2015

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብዶ እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት በአዳማ ሲካሄድ የነበረውን የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባን ጨርሰው አስጎሪ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የተመለሱት የሰደን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ቃጫ “ባልታወቁ” ባሏቸው የታጠቁ አካላት ከመኖሪያ ቤታቸው የተወሰዱት ቅዳሜ ሌሊት ነበር፡

https://p.dw.com/p/4SxHz
Äthiopien Addis Abeba | Oromia Regionalkonferenz
ምስል Seyoum Getu/DW

የወረዳ አስተዳዳሪዉ አጋጭና ገዳዮች አልታወቁም

 

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሰደን ሶዶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ታግተው ከሁለት ቀን በኋላ ተገድለው ተገኝተዋል፡፡አስተዳዳሪዉ ባለፈዉ ማክሰኞ ሰኔ 13 በታጠቁ ኃይላት ተገድለው የተገኙት አቶ በቀለ ቃጫ ዛሬ ሐሙስ ስርኣተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡በኦሮሚያ ክልል የሚፈፀመዉ እገታ፣ ግድያና የፀጥታ ቀዉስ እየተንሰራፋ መምጣቱ በሰፊዉ እየተነገረ ነው፡፡

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብዶ እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት በአዳማ ሲካሄድ የነበረውን የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባን ጨርሰው አስጎሪ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የተመለሱት የሰደን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ቃጫ “ባልታወቁ” ባሏቸው የታጠቁ አካላት ከመኖሪያ ቤታቸው የተወሰዱት ቅዳሜ ሌሊት ነበር፡፡ “ቅዳሜ ሌሊት ልክ ከአዳማው መድረክ እንደተመለሱ በግምት ከአመሻሹ ሶስት ሰዓት ገደማ ነበር ባልታወቁ አካላት ከቤተሰባቸው መሃከል የተወሰዱት፡፡ ከተወሰዱ በኋላ ክትትል ብደረግም ያው ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ቅዳሜ ከአስጎሪ ከታገቱ በኋላ ማክሰኞ ነው አስከሬናቸው የፀጥታ ኃይል ባደረገው ፍለጋ በቶሌ፣ ኢሉ እና ሶዶ ወረዳዎች አዋሳን አከባቢ የተገኘው፡፡ አጋቾች በራሱ ስልክ ወደ ቤተሰቦቹ እየደወሉ እስከ 10 ሚሊየን ብር ሲጠይቁ እንደነበርም በመረጃ ደረጃ ሰምተናል፡፡”

 

ከመምህርነት ጀምሮ በርዕሰ መስተዳድርነት ረጅም ጊዜ ሲያገለግሉ እንደነበር የሚነገረው አቶ በቀለ ቃጫ፤ በዚሁ ዞን የዳዎ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ እንደነበሩና ወደ ሰደን ሶዳ ወረዳ ኃላፊነት ከመጡ ሁለት ዓመታት መቆጠሩንም የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ገልጸዋል፡፡ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የታጣቂዎች እንቅስቃሴ መኖሩንና መሰል ተግባራት እየተበራከቱ መምጣታቸውን ያልሸሸጉት አቶ ኃይሉ፤ በአስጎሪ መሰል የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ግን ተሰምቶ የሚታወቅ ባለመሆኑ የግል ጥበቃ እንዳልተመደበላቸውም አመልክተዋል፡፡ በዞኑ ግን እስከ አርሶአደሮች ግለሰቦች እየታገቱ ከ200 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚጠየቁም ገልጸዋል፡፡ የሰደን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩ አቶ በቀለ ቃጫ ስርዓተ ቀብራቸው ዛሬ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት መፈጸሙንም የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አረጋግጠውልናል፡፡

በኦሮሚያ የጸጥታ ስጋቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት እየተስተዋለ እና እያሰጋም እንደሚገኝ እንዲሁ ከተለያዩ አከባቢዎች ነዋሪዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት ነዋሪ፤ ከዚህ ቀደም ሰኔ 08 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 ታጣቂዎች ስድስት ሰው ገድለው ከ100 በላይ ከብቶችን ዘርፈው ከሄዱ በኋላ “እንቅልፍ የለሽ” ያሉት አለመረጋጋት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ “አሁን የምንገኘው ኪረሙ ወረዳ አባይ በረሃ ላይ ባጅን ቀበለ ውስጥ ነው፡፡ ኔትዎርክ የለም ረጅም መንገድ እየሄድን ነው ደውለን ሰው የምናገኘው፡፡ የጸጥታ ችግሩ ውስጥ ከገባን ሶስት ዓመታት አስቆጥረናል፡፡”

እኚህ አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት ከዚህ ወረዳ በተጨማሪም እንደ ጉቲን እና አሙሩ ባሉ አጎራባች ወረዳዎችም የሚከሰተው ተደጋጋሚ የፀጥታ ችግር አሁንም ድረስ ሙሉ እልባት ያገኘ አይመስልም፡፡

ሌላው ተደጋጋሚ የፀጥታ ችግር የሚያጋጥመው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው አሊዶሮ በምትባል ስፍራ መንገደኞች እና ሾፌሮች በተደጋጋሚ በታጠቁ አካላት እየታገቱ እንደሚወሰዱ ይነገራል፡፡ ከሰሞኑም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አሽከርካሪዎች በዚህ ስፍራ በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸው ተነግሯል፡፡ ይሁንና ዶቼ ቬለ ታግተዋል የተባሉ ሰዎች ቤተሰቦችን ለማነጋገር በእጅ ስልካቸው ላይ ደውሎ ብጠይቃቸውም ለደህንነታቸው እንሰጋለን በሚል ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

በዚሁ አሊ ዶሮ በምትባል ስፍራ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም በመጓዝ ላይ ሳሉ ከዚህ ቀድም ታግተው አንድ ሚሊየን ብር ከፍለው መውጣታቸውን የገለጹልን አንድ የባህርዳር ነዋሪ እንዳሉን ግን፤ ሰሞኑን በገፍ ከታገቱት ሰዎች ቤተሰቦች 6 ገደማ የሚሆኑት ደውለውላቸው እንዴት እንደወጡ እንደጠየቁአቸዋው ነግረውናል፡፡ “ይህቺ ቦታ ወደ ባህርዳር ስንሄድ ፊቼ እና ገርባጉራቻ መካከል ነው የምትገኘው፡፡ እዚህ ቦታ እገታው ተደጋግማል፡፡ ገንዘብ ከፍሎ መውጣትም እንደ እድል እየታየ ነው፡፡ መፍትሄ መስጠት ያለበት መንግስት ነው፡፡ አጋቾች ወደ ታች አባይ በረሃ ነበር የወሰዱን፡፡ እንዚህ በ20 በ30 ቁጥር ከፍ ባለ ባይሆንም ስድስት ሰባት ሰዎች በተደጋጋሚ መታገታቸውን አውቃለሁ፡፡ አሁን ሰሞኑን ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ ዘመዶቻቸውን ለማስወጣት ብለው ወደ እኔ እደወሉ የወጣሁበትን መንገድ ሲጠይቁኝ ነበር፡፡”

ከተሰማሩበት ከመንግስት ስራ ወደ ባህርዳር በመመለስ ላይ ሳሉ እኩለ ቀን 6፡30 ገደማ በዚሁ ስፍራ ሲሄዱበት የነበረው የቢሮ መኪና በታጣቂዎች ጋይቶ እሳቸውን ጨምሮ በተሸከርካሪው ውስጥ የነበሩ ሶስት ሰዎች በታገቱ በስድስተኛ ቀን ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸውን የሚገልጹት እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ እስካሁን ይፈጸማል ያሉት የመንገደኞች እገታ እንዲቆም መንግስት በተሻለ ቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል የሚል የግል አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል፡፡

ስለ መሰል የተጓዦች ተደጋጋሚ ቅሬታ እና መፍትሄው ለመጠየቅ በሰሜን ሸዋ ዞን የኩዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ለሆኑት ለአቶ ግርማ ይልማ ዛሬ በተደጋጋሚ ደውለን ጉዳዩን ብናስረዳቸውም፤ ከ30 ደቂቃ በኋላ እንድንደውል ጠይቀውን ከዚያን ስልካቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም አያነሱም፡፡ አሁንም ከፀጥታ ስጋት ስላልተላቀቀው ኦሮሚያ ክልል እልባት ለመጠየቅ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለአቶ ኃይሉ አዱኛ እና ለክልሉ ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎችም ደውለን ማብራሪያ ለማግኘት ብንጥርም አልሰመረም፡፡ 

ስዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ