እየናረ የመጣው የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ
ዓርብ፣ ጥር 5 2015የኢትዮጵያ መንግስት የነዳጅ ድጎማን በአንድ ዓመት ውስጥ በየምዕራፉ ሙሉ በሙሉ የማንሳት አካል የሆነው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በዚሁ በያዝነው ሳምንትም ይፋ ሆኗል፡፡ ባለፉት 6 ወራት ብቻ ነዳጅ በአማካይ በ28 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷልም፡፡ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሰኞ ይፋ ባደረገው የነዳጅ ዋጋ ተመን የቤንዚን ዋጋን 61 ብር ሲያደርስ ናፍጣ ደግሞ በ67 ብር ገደማ እንዲሸጥ ወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት አሁን ለሶስተኛ ጊዜ ይፋ የሆነው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መንግስት በአንድ ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማንሳት ያቀደው የነዳጅ ድጎማን በእቅዱ መሰረት ለመፈጸም የሚያስችለው ነው ይላሉ፡፡ “በዚህ ዓመት መጨረሻ ተጠቃሚው ሙሉ በሙሉ በገቢያ ዋጋ ብቻ ነዳጅ ይገዛል ማለት ነው” ያሉት ስራ አስፈጻሚው በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከተመረጡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች ውጭ ድጎማው ሙሉ በሙሉ እንደሚነሳም ተናግሯል፡፡ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ መስተዋሉን የሚያነሱት መቀመጫቸውን በታላቋ ብሪታንያ ውስጥ ያደረጉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያ አቶ አብዱልመናን መሐመድ ግን ነዳጅ የማስናር ውሳኔው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የመሰረታዊ ፍጆታ ዋጋን የሚያባብስ ነው ይላሉ፡፡
“የነዳጅ ጭማሪው ውሳኔ ድጎማን ከማንሳት ይልቅ መንግስት በጦርነቱ መዘዝ የመጣበትን የገቢ ችግር ለማቻቻል የሚያደርግ ጥረት ነው የሚመስለው” የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጭማሪው የእያንዳንዱን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ የሚነካ እና ግሽበት አባባሽ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ታደሰ ግን የነዳጅ ጭማሪው በኑሮ ውድነቱ ላይ ያሳየው ተጨባጭ አሉታዊ ውጤት እምብዛም አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ ነዳጅ በጨመረበት ወራት ላይ እና ነዳጅ ያልጨመረባቸው ወራት ላይ ያለው ወርሃዊ የግሽበት መጠን እምብዛም ልዩነት የሌለው ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ አቶ ታደሰ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በንግዱ እና በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ወርዶ ሲተረጎምም ምክኒያታዊ ባልሆነ ጭማሪ ስለሚተገበር እንጂ በጥብቅ ቁጥጥር ምክኒያታዊ የሆነ ጭማሪ ቢደረግ ተጽእኖው ቀላል እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ መንግስት በያመቱ ለነዳጅ ድጎማ የሚያወጣው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሚያሳስብና ለሌላ ልማት መዋል የነበረበት ነው ሲሉም ድጎማውን የማንሳት ግብ አስረድተዋል፡፡መንግስት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ነዳጅ የሚገዙበት ዋጋ ድጎማ ያለውና የተለየ ቅናሽ ያለው ቢሆንም ቁጥጥሩስ አዳጋች እና ለህገወጥ ስራ የሚዳረግ አይሆንም ወይ የተባሉት የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ኃላፊው፡ በተለይም ቁጥጥሩ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውጪ የላላ መሆኑንና ቅናሹ ቀጥታ ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ ማህበረሰብን መደጎም እንደመሆኑ ለታለመለት ግብ እንዲበቃ ቁጥጥሮችን ማጥበቅ ብቸኛ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ