1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ ኢትዮጵያ ወዴት?

እሑድ፣ ታኅሣሥ 10 2014

በጦርነቱ የተከሰተዉ ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን እና ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነዉ። በጦርነት የንብረት መዉደም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እና በሁሉም ቦታ የሚታየዉ ወቀሳ ሊነገር ለአፍ የሚከብድ ለሰሚ ግራ የሚገባ እና ለጆሮ የሚቀፍ ነዉ። እንዲህ ይሆናል ብለዉ አስበዉ ነበር? 

https://p.dw.com/p/44Uqn
Äthiopien | Verwüstungen in Lalibela
ምስል AFP via Getty Images

ያለነዉ ጦርነት ዉስጥ ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊና የሥነ-ልቦና ቀዉስ ዉስጥም ጭምር ነዉ

እንወያይ፤ ኢትዮጵያ ወዴት?

ዓመት ያለፈዉ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ጦርነት አዉዱን አስፍቶ አንዴ ጋብ አንዴ ጠንከር እያለ እንደቀጠለ ነዉ። በጦርነቱ ባይገለፅም ብዙ ሰዉ አልቋል። ከተሞችም ወድመዋል። በሁለቱም ወገኖች በኩል ጠላት ያሉትን ደምስሰዉ ጦርነቱን በድል ለማብቃት በቀር ስለሰላም ስለእርቅ እና ስለ ድርድር አያነሱም። ይልቁንም በወንድማማችንነት አብሮ በነኖረዉ ሕዝብ መካከል የጠላትነት ስሜት እየጨመረ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። የሚገደለዉ፤ የሚወድመዉ፤ የሚፈናቀለዉ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚደርስበት ሰዉ፤ ቁጥር አሁንም እየጨመረ ነዉ።  ከተማ ይያዛል። ሰዉ ይገደላል ከተማ ይወድማል ሴቶች ይደፈራሉ። ለስንት ሺህ ዘመን አብሮ የኖረ ህዝብ፤ ማኅበረሰባዊ ትስስሩና የመተሳሰብ ግንኙነቱ እየጠፋ ይመስላል። በርግጥ መንግሥት አገራዊ ውይይትን የሚመራ ተቋም መስርቶ ብሔራዊ ዉይይት ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆኑ ተሰምቶአል። ግን ኢትዮጵያ በዚህ አይነት እንዴት ነዉ የምትቀጥለዉ? ደሃዉ ኢትዮጵያዊ መኖርያዉ ከተማዉ ማብሰያዉ ብሎም አባት እናት ወንድሙ ተገድሎበት፤ እህት እናት አያቱ ተደፍሮበት ኑሮዉን እንዴት ይቀጥል? የኢትዮጵያዉያን የአብሮ መኖር የመደጋገፍ ባህል እንዴት ነዉ የሚመለሰዉ? የሃይማኖት አባቶች የታሪክ ምሁራን እና የሕግ አዋቂዎች ስለአሁንዋ ኢትዮጵያ ምን ይላሉ። እንዴት እዚህ ላይ ደረስን? እንዲህ አይነት ሁኔታ ይከሰታል ተብሎች ተገምቶ ነበር? ኢትዮጵያ ወዴት? በዚህ ዉይይት ላይ የሚሳተፉት፤

Äthiopien | Verwüstungen in Lalibela
ምስል AFP via Getty Images

መላከ መዊ ልሳነ ወርቅ ዉቤ  በጀርመን ፍራንክፈርት የምስካኤ ዙናን መድሐንያለም ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ ፤ ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ፤  ዶ/ር ግርማ መሐመድ በፖለቲካዊ ፍልስፍና ምሁርና በለንድን ሮሃምተን ዩንቨርስቲ መምህር፤ እንዲሁም አዲሱ ጌታነህ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ናቸዉ።  

ተወያዮች በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ተወያይተዋል።

Äthiopien I Kundgebung  in Addis
ምስል S. Getu/DW

በጦርነቱ የተከሰተዉ ሁኔታ እጅግ የሚያሳዝን እና ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነዉ። በጦርነት የንብረት መዉደም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እና በሁሉም ቦታ የሚታየዉ ወቀሳ ሊነገር ለአፍ የሚከብድ ለሰሚ ግራ የሚገባ እና ለጆሮ የሚቀፍ ነዉ። እንዲህ ይሆናል ተብሎ ታስቦ ነበር? 

በሃይማኖት በባህል በመተሳሰብ አብሮ የኖረ ህዝብ ይህን ያህል መጨካከኑ ከምን የመጣ ነዉ ? ቆም ብሎ ማሰብ ያልተቻለበት ምክንያቱ ምንድን ነዉ?  ወደዚህ ዉስጥስ እንዴት ገባን? 

የገባንበት ነገር ጦርነት ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ እና  የስነልቦና ቀዉስ ዉስጥም ጭምር ነዉ የሚሉ ብዙዎች ናቸዉ። የኢትዮጵያዉያ የተለያዩ ባህሎች እና ሃይማኖቶች፤  ነዉርን የተጠየፉ ናቸዉ ሲባል ለዘመናት ሲነገር ሰምተናል።  ማኅበረሰብ ነዉ ወንድም ነዉ ብለን የምናምነዉ ህዝብ እንዴት እንዲህ አይነት ስራ ሊፈፅም ቻለ? 

ይሄ እንደዉ ከህወሃት ከብልፅግና ወይም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በድርድር ወይም በእርቅ የሚፈቱት አይደለም ይባላል።  ግጭቱ ቁርሾዉ ትቶት ያለፈዉ ጠባሳ፤ በጣም ከባድ ነገር ነዉ። የነበረንን ለዘመናት የዘለቀ ማኅበራዊ ትስስር ፤ የነበረንን አንድነት ጉርብትና ፤ አብሮ መኖር እሴታችንን እጅግ ጥርጣሪ ዉስጥ ከቶታል። ይህንስ እንዴት ይገመገማል? 

Äthiopien | Verwüstungen in Lalibela
ምስል AFP via Getty Images

የህወሃት ታጣቂዎች ክልል ጥሰዉ ከተማን እያወደሙ፤ መሰረተ ልማትን እያፈረሱ ነዉ እንጂ ፤ ጦርነት እየተካሄደ አይደለም። ኢትዮጵያዉያን ለህልዉናቸዉ እየተጋደሉ ነዉ የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም። ይህስ እንዴት ይታያል። 

ጦርነቱ ብዙ አይቀጥልም ተብሎ አንድ አመትን ዘልቆአል ። ይህ ጦርነት ወይም ግጭት በአንዱ አሸናፊነት ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል? ጦርነቱ መቼ ነዉ የሚያበቃዉ? ኢትዮጵያዉያን ቆም ብለዉ የነጋቸዉን መነጋገር የሚጀምሩት መቼ ነዉ? 

በትግራይም ሆነ በሌላዉ የሃገሪቱ ክፍል ማኅህበረሰቡ የደረሰበት  የሥነ-ልቦና ስብራት ተጠግኖ እንደ ሃገር ለመቀጠል ከፖለቲካዉ ባሻገር፤ የሃይማኖት አባቶች የታሪክ አዋቂዎች፤ እናቶች አባቶች ወጣት አዛዉ ንቱ ምን መደረግ አለበት። እንዴት የአንድነት መሰረታችንን እንጠግን? በሚሉት ነጥቦች ላይ ተወያይተዋል።

ሙሉዉን ዉይይት የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።   

 

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ