አርዓያ መምህራን እና ተጋራፊዎች
ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2011ብዙ ከማውራት ይልቅ በተግባር ማሳየት እና አዳዲስ ሀሳቦችን ማፍለቅ አንድን ጥሩ መምህር ይገልፀዋል ይላሉ የ2019 የዓለም ምርጥ መምህር ተሸላሚ ፔተር ታቢቺ። ኬንያዊው መነኩሴ እና መምህር ምርጥ መምህር የተባሉት ከ179 ሀገራት ከታጩ 10 000 መምህራን መካከል ነው።« በጣም ደስ ብሎኛል። ማመን አልቻልኩም። ከዓለም ጎበዝ መምህራን ውስጥ በመመረጤ በጣም ደስተኛ ነኝ።»
የ36 ዓመቱ ታቢቺ ኬንያ ውስጥ ድርቅ እና ረሐብ በሚያጠቃው አንድ መንደር ውስጥ የኬሪኮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሂሳብ እና ሳይንስ መምህር ናቸው። አንድ ሦስተኛ ያህሉ ተማሪዎቻቸው ወላጅ የሏቸውም ወይም አንዳቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አብዛኞቹም ተማሪዎች ከደሀ ቤተሰብ የተወለዱ ናቸው። ታቢቺ ወደዚህ ትምህርት ቤት መተው ማስተማር የጀመሩት በፊት የነበሩበትን የግል ትምህርት ቤት ትተው ነው። የወሰዱት ርምጃ ፍሬ አፍርቷል። ምንም እንኳን የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት የትምህርት መገልገያዎች ባይሟሉም ከተማሪዎቻቸው በሀገር አቀፍ ውድድሮች ተካፍለው አሸናፊ የሆኑ ይገኙበታል። ይህ ብቻ አይደለም ታቢቺ ከሚያገኙት የወር ደሞዝ 80 በመቶውን የሚያውሉት ለተቸገሩት ተማሪዎች ነው። መምህር ፔተር ታቢቺ ለመምህርነት ሞያ መስጠት ስላለበት ትኩረት እንዲህ ይገልጣሉ።« የተመኙበት ቦታ መድረስ ይቻላል። እኛ መምህራን ይህንን በማድረግ ለማገዝ እንችላለን። ለዛም ነው መምህርነት ጥሩ ሞያ የሆነው። መምህራንን ማክበር ይኖርብናል። »
መምህር ፔተር ታቢቺ ኬንያዊው የዓለም ምርጥ መምህር ብቻ ሳይሆን የተባሉት ዱባይ ላይ በተካሄደው ሥነ-ስርዓት የ1 ሚሊዮን ዩ ኤስ ዶላር ተሸላሚም ናቸው። ከሽልማታቸውም ይበልጡን ገንዘብ ለትምህርት ቤቶች አስፈላጊ ነገሮች እንዲሟሉ እንደሚለግሱ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶችስ በጣም ጥሩ ወይም አርዓያ ሆነውኛል የሚሏቸው መምህራን ምን አይነት መምህራን ናቸው?
« እጅግ በጣም ስራቸውን የሚወዱ፣ በሰዓት የሚገኙ፣ ተማሪዎች ትምህርቻቸው ላይ ትኩረት እንዲሰጡ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ቁጡ መምህራኖች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብዬ አምናለሁ።
« ሴቶች እናት የሆኑ አስተማሪዎች ነበሩ።ብዙ ነገር የሚያካፍሉን። ወደፊት ስታድጉ ስታገቡ እንደዚህ ታደርጋላችሁ የሚሉ»
« የአራተኛ ክፍል እያለሁ የሂሳብ መምህራችን ጊዜቤት እንድናቅ እና በሂሳብ ትምህርት ኃይለኛ እንድንሆን አድርጎናል።»
የሚሉ አስተያየቶች ይገኙበታል።
ተማሪዎችን ሥነ-ምግባር በማስያዝ በተለይ የብሪታንያ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ዝነኛ ናቸው። በዓመት ከ 30ሺ እስከ 35ሺ የመክፈል አቅሙ ያላቸው አንዳንድ ጀርመኖች ልጆቻቸውን የማልቨርን ኮሌጅ ይልካሉ። በዚህ ትምህርት ቤት የደንብ ልብስ መልበስ ግዴታ ነው፤ የልጃ ገረዶች ቀሚስ ከጉልበት በላይ መሆን አይፈቀድም፣ረዥም ፀጉር ተሰብስቦ መያዝ አለበት፣ ይህ ብቻ አይደለም ትምህርት የሚሰጠው ሙሉ ቀን ነው፣ ተማሪዎች ስልካቸውን እንዲጠቀሙ የሚፈቀድላቸው የተወሰነ ሰዓት አለ። ከቁርስ በፊት ቤተ ክርስትያን ይሄዳሉ። ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ መብራት ይጠፋል።
ተማሪዎችን ሥነ-ምግባር ማስያዝ ግን በተለይ ከዚህ ቀደም በነበሩ የኢትዮጵያ መምህራን ዘንድ በዱላ እንደነበር በርካቶች ገልጸውልናል። አብዲ በ1970 አካባቢ ነው ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት።« አካባቢው ለመምህራን አመቺ አልነበረም ስለሆነም ተማሪዎችን ኮትኩተው ለማስተማር ፍላጉቱ አልነበራቸውም። አንድ መምህራችን ውጡ ተበርከኩ እያሉ በዱላ እስከሚደክማቸው ይገርፉን ነበር።» ይላሉ። ከአብዲ ረዥም ዓመታት በኋላ ትምህርት ቤት የሄደችው ካሰች ደግሞ ግርፊያ ብቻ ሳይሆን ትንኮሳም ገጥሟታል።ዛሬ በሳውዲ አረቢያ ነዋሪ የሆነ አንድ የቀድሞ ተማሪ ደግሞ መምህሩን ስለሚፈራ ከትምህርት ቤት ተሸሽጎ ይቀር ነበር።
ድሮ እና ዛሬስ ምን ተቀየረ? የ 27 ዓመቱ አብዱል አዚዝ ለ10 ዓመት ትምህርቱን ካቋረጠ በኋላ መልሶ ቀጥሏል። « ድሮ የነበሩ መምህራን እንደ ወላጅ ሆነው ነው ያስተምሩን የነበረው። መቁጣ ሳይሆን በምክር አሁን ላይ ደግሞ በኃይል ነው።» ይላል። ሌላውም የ 10ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነ የነገረን ወጣት ዱላ በስም ነው የቀረው ይላል።
ወይዘሮ ኂሩት ዮሴፍ የማኅበረሰብ ባለሞያ (social Worker) ናቸው። በሚኖሩበት አዲስ አበባ መምህራን እንደድሮው ተማሪዎችን በመግረፍ እንደማይቀጡ ነው የሚያውቁት። ይሁንና የሚገረፉ ተማሪዎች ለምን አይነት የስነ ልቦና ችግር እንደሚደረጉ ያስረዳሉ። ለDW እንደገለፁት ፍራቻ፣ ከሰው ጋር አለመቀራረብ፣ ራሳቸውን በሰው ፊት መግለፅ አለመቻል እንደዚህ አይነት ችግሮች ይገጥሟቸዋል። ያ ደግሞ ወደፊት በስራም ሆነ በትዳር ህይወታቸው ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ አለው።»
ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ