1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካእስያ

ቻይና ውስጥ የተቀጣጠለው ተቃውሞ

ረቡዕ፣ ኅዳር 21 2015

ቻይና እንደ አዲስ ባገረሸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የደነገገችው ደንብ ህዝቡን ለቁጣ ቀስቅሶ አደባባይ አውጥቷል። የአደባባይ ተቃውሞውን ለመግታትም ዋና ከተማ ቤጂንግን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለተቃውሞ ጎዳና በወጡት ላይ የጸጥታ ኃይሎች ጠንካራ ርምጃ እየወሰዱ ነው።

https://p.dw.com/p/4KIyy
China I Corona-Proteste in Guangzhou
ምስል REUTERS

የኮቪድ 19 እገዳ መነሻ ሆኗል

 

ቻይና እንደ አዲስ ባገረሸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የደነገገችው ደንብ ህዝቡን ለቁጣ ቀስቅሶ አደባባይ አውጥቷል። የአደባባይ ተቃውሞውን ለመግታትም ዋና ከተማ ቤጂንግን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለተቃውሞ ጎዳና በወጡት ላይ የጸጥታ ኃይሎች ጠንካራ ርምጃ እየወሰዱ ነው። የሀገሪቱ ማዕከላዊ የፖለቲካ እና ሕግ ጉዳይ ኮሚሽን ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫም እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል። በሌላ ወገን አራተኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባል ለመስጠት ዝግጅት ጀመሩ፤ ገደቡን አላልቶ ውጥረቱን ሊያረግብ እንደሚችል ተገምቷል። የሀገሪቱ ማዕከላዊ የፖለቲካ እና ሕግ ጉዳይ ኮሚሽን ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫም እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል። በሌላ ወገን አራተኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባል ለመስጠት ዝግጅት ጀመሩ፤ ገደቡን አላልቶ ውጥረቱን ሊያረግብ እንደሚችል ተገምቷል።

China I Corona-Proteste in Guangzhou
በየከተማው የተዳረሰው ተቃውሞምስል REUTERS

በቤጂንግ፣ ሻንጋይ እና በሌሎች የቻይና ከተሞች በርካታ ነዋሪዎች የሀገሪቱ መንግሥት የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ዳግም እንዳይስፋፋ ከሳምንታት በፊት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በአደባባይ ሰልፍ እየተቃወሙ ነው። የቻይና መንግሥት «ዜሮ ኮቪድ» ሲል ያወጣውን እና ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ የሚያግደውን ጠንካራ ፖሊሲ የመቃወሙ እንቅስቃሴ በዋና ከተማ ቤጂንግ የተጀመረው ባሳለፍነው እሑድ ምሽት ነው። ሰልፈኞቹ «ነጻነት እንፈልጋለን» በማለት መፈክር ከማሰማታቸው በተጨማሪ፤ የሃሳብ ነጻነታችን ተገድቧል የሚለውን ለመግለጽም ያልተጻፈበት ነጭ ወረቀት ይዘዋል።

ለምን ነጭ ወረቀት ያዛችሁ ተብለው ከተጠየቁት ሰልፈኞች አንዷ የሻንጋይ ከተማ ነዋሪ እንዲህ ይላሉ።

« ምንም መናገር አንችልም። ባዶ ወረቀት ያደረግነው የምንናገረው ሁሉ ቁጥጥር ስለሚደረግበት ነው በማለት።» ተምሳሌቱን ገልጸዋል።

China | Corona Proteste | Polizeipräsenz in Shanghai
ፖሊሶች ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋሉምስል Hector Retamal/AFP/Getty Images

ቻይና ውስጥ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ አንስቶ በቅርቡ በተሐዋሲው የተያዙት ሰዎች ቁጥር ታይቶ እንደማይታወቅ ነው የሚነገረው። ከቀናት በፊት መንግሥት ይፋ ባደረገው መሠረትም የተያዘው ሰው ከ33 ሺህ አልፏል። ኮሮናን ፈጽሞ ከቻይና ለማጥፋት በተያዘው ዕቅድ መሰረትም በተለይ በቅድሚያ ግዙፉ የአይፎን ማምረቻ ኩባንያ በሚገኝበት ማዕከላዊ ቻይና ውስጥ በርካቶች በተያዙበት አካባቢ ሰዎች ለኮሮና ምርመራ ካልሆነ በቀር ከቤታቸው እንዳይወጡ ነበር የተደረገው። ቻንግቾ በተባለችው ከተማ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ እና ረቡዕ ዕለት ነዋሪዎች እርምጃውን በመቃወም ከፖሊስ ጋር ከተጋጩ በኋላም፤ ባለሥልጣናት ስድስት ሚሊየን ህዝብ በሚኖርባት ከተማ ለስድስት ቀናት የእንቅስቃሴ ገደብ አወጁ። የከተማዋ ነዋሪዎችም በየቀኑ PCR የሚባለውን የኮሮና ተሐዋሲ ምርመራ እንዲያደርጉ አዘዙ። እርምጃው ግን በህዝቡ ተቀባይነት አላገኘም። ለተቃውሞ የወጡት ሌላዋ የሻንጋይ ነዋሪም እንዲህ ነው ያሉት፤

«PCR ምርመራ እንድናደርግ ግዳጅ የጣለብንን አምባገነን እየተቃወምን ነው፤ ሺ ዢንፒንግን ታውቃለህ።»

እጅግም የተቃውሞ እንቅስቃሴ በማይታይባት ቻይና የተቀጣጠለውን የአደባባይ ተቃውሞ የለኮሰው የኮሮና ተሐዋሲን ስርጭት ለማስቆም የተደነገገው ጥብቅ ደንብ ብቻ አይደለምም እየተባለ ነው። መቀመጫውን በታይዋን ያደረገው የግዙፉ አይፎን ኩባንያ ባለቤት ፎክስን ሠራተኞች ከአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታቸው ጋር የማይጣጣመውን ክፍያ እንዲያስተካክል ጥያቄም ሲቀርቡ እንደነበርም ተሰምቷል። በእንቅስቃሴ ገደቡ መደጋገም ቁጣው የገነፈለው ህዝብ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ሥልጣን እንዲለቅቁ፣ ገዢው የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲም እንዲወገድ የሚሉ ድምጾችን እያስተጋቡ ነው። የሆንግ ኮንግ የጸጥታ ጉዳይ ኃላፊ ክሪስ ታንግ፤ በሀገሪቱ የተፈጠረው ማኅበራዊ አለመረጋጋት ድንገተኛ ሳይሆን ታስቦበት ነው ይላሉ።

China I Corona-Proteste in Guangzhou
ተቃውሞውን ለመበተን የወጡት ፖሊሶችምስል REUTERS

«የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች እና የመገናኛ ብዙሃን አባላት፤ ያስተዋልኩት የማኅበራዊ አለመረጋጋት የመጀመሪያዎችን እንደሆነ ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ። ባለፉት ቀናት በአንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ግቢዎች እና በከተሞች ጎዳና ላይ የነበሩት ኹነቶች ሌሎችን በቻይና ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ለማነሳሳት ያለሙ ነበሩ። በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ተመሳሳይ አመጽ የቀሰቀሱ ሰዎችም ይገኙበታል። ይህ ደግሞ አጋጣሚ ሳይሆን በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ ነው።»

በዛሬው ዕለትም በየከተሞቹ ጎዳናዎች ላይም በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎች ከነተሽከርካሪዎቻቸው እንደሚታዩ ነው ተዘግቧል። በደቡባዊ ቻይና ግዛቶችም ለተቃውሞ ከወጣው ህዝብ ጋር ተጋጭተዋል። የተጠናከረውን የህዝብ ተቃውሞ ተከትሎም የቻይና መንግሥት የጣለው የእንቅስቃሴ ገደቡ እንዲላላ ይረዳል የተባለውን ለአራተኛ ጊዜ የኮቪድ 19 ክትባት ሰዎች እንዲከተቡ ሃሳብ አቅርቧል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ