1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ዉጊያ፣የናሚቢያ ካሳ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 10 2015

የንጉሱ ንብረት ከመሆንዋ በፊት፣ የንጉስ ንብረት ሆና፣ በ1908 የቤልጂግ ፓርላማ ከንጉሱ ቀምቶ የቤልጅ ቅኝ ተገዢ ሲያደርጋትም ሆነ በ1960 ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች በኋላ ኃይለኞች ሐብቷን የሚዘርፉባት፣ሕዝቧን የሚገድሉ፣የሚያሰቃዩባት ከመሆን ባለፍ ለሐገሬዉ ነዋሪ የፈየዱት የለም።

https://p.dw.com/p/4JlK6
DRK Symbolbild FARDC
ምስል Alain Wandimoyi/AFP

ትኩረት በአፍሪቃ፤ የኮንጎ ጦርነት፣ የናሚቢያ ካሳ

የዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን በሁለት ርዕሶች ላይ ያተኩራል።የመጀመሪያዉ ምሥራቃዊ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዉስጥ የሚደረገዉን ዉጊያ፣ከኬንያ ፖለቲካዊ-ወታደራዊ ጥረትና ተፅዕኖ ጋር ቀይጦ የሚቃኘዉ ነዉ።ሁለተኛዉ የጀርመን ቅኝ ገዢዎች ናሚቢያ ዉስጥ ለፈፀሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል ጀርመን ልትከፍል ያቀደችዉ ካሳ አከፋፈል አዲስ የገጠመዉን ዉዝግብ የሚያወሳዉ ነዉ።ሁለቱንም ዘገቦች ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሯቸዋል በየተራ ያሰማናል።
ያቺ ሰፊ፣ለም፣ በማዕድን፣ በዱር ሐብት የበለፀገች አፍሪቃዊት ሐገር አብዛኛ ታሪኳ በግጭት፣ጦርነት፣በዉጪ ኃይላት ጫናና ጭቆና የተሞላ ነዉ።ቅኝ የመገዛት ታሪኳ እንኳ ከአብዛኛ ብዜዎችዋ ለየት ብሎ የአንድ ሐገር ከመሆን ይልቅ የአንድ ንጉስ ርስት ሆና ዘመናት አስቆጥራለች።
የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች በ1885 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በርሊን ላይ በጠሩት ጉባኤ አፍሪቃን ሲቀራመቱ የቤልጂጉ ንጉስ ሊዎፖልድ ዳግማዊ ኮንጎን «ነፃ መንግስት» ብለዉ የግል ንብረታቸዉ አደረጓት።የንጉሱ ንብረት ከመሆንዋ በፊት፣ የንጉስ ንብረት ሆና፣ በ1908 የቤልጂግ ፓርላማ ከንጉሱ ቀምቶ የቤልጅ ቅኝ ተገዢ ሲያደርጋትም ሆነ በ1960 ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች በኋላ ኃይለኞች ሐብቷን የሚዘርፉባት፣ሕዝቧን የሚገድሉ፣የሚያሰቃዩባት ከመሆን ባለፍ ለሐገሬዉ ነዋሪ የፈየዱት የለም።
ለሕዝቧ ነፃነት፣ለሰላም ዕድገቱ ከቼኩቬራ እስስ የኢትዮጵያ ወታደሮች ተፋልመዉላታል።ከፓትሪስ ሉቡምባ እስከ ሎራ ካቢላ ተገድለዉበታል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ዳግ ሐመርስክዮልድ ጭምር ሕይወታቸዉን ገብረዉለታል።
የአዉሮጳ፣ የአፍሪቃ፣ የእስያ፣የደቡብ አሜሪካ ወታደር ተዋግቶባታል።ዓለም ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር ከስክሶባትል።ዛሬም ግን ጦርነት ላይ ናት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ (DRC)።የማትጥፋ-የማትለማ ትንግርተኛ ምድር።አማፂያንን እንዲወጋ በቅርቡ የተመሰረተዉ የምስራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብ አካባቢያዊ ኃይል (EARDC) አዛዥ ኬንያዊ ሜጄር ጄኔራል  ጄፍ ንያጋሕ ባለፈዉ ሮብ እንዳሉት ምስራቅ አፍሪቃዊቱን ሐገር ከ120 በላይ አማፂ ቡድናት ያተራምሷታል።
                                       
«ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዉስጥ ከ120 በላይ ታጣቂ ቡድናት አሉ።እነዚሕ ሁለት መስመሮች ከከሸፉ ወደሚቀጥለዉ መስመር እንዞራለን።እሱም ወታደራዊ እርምጃ ነዉ።ይህ በጣም ግልፅ ነዉ።ግን ዋጋ እንደሚያስከፍል መታወቅ አለበት።ፖለቲካዊ፣ትጥቅ መፍታትና ዳግም ጦሩን መቀየጥ ይሻላል።በፈቃዳቸዉ ትጥቅ የማይፈቱ ወይም የሚቃወሙ ካሉ እንምራቸዉም»
ምናልባት ጄሜራሉ ራሳቸዉ ከመወለዳቸዉ በፊት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከቤልጂግ እስከ ኢትዮጵያ፣ ከአዉሮጳ እስከ ሕንድ የሚገኙ የጦር አዛዦች በቀደም የሰማነዉን ወይም ተመሳሳዩን ብለዉት ነበር።የመጣ ሰላም የለም።
ሰሞኑን የከፋዉ ደግሞ የሐገሪቱ ጦርና በሩዋንዳ ይደገፋል የሚባለዉ M23 አማፂ ቡድን በሐገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የገጠሙት ዉጊያ ነዉ።የመንግስት ጦር ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ በከፈተዉ የአየርና የምድር ጥቃት በርካታ ትናንሽ አካባቢዎችን ካማፂዉ ቡድን ማስለቀቁ ተዘግቧል።
ይሁንና ወታደራዊ ተንታኞችና የአካባቢዉ ነዋሪዎች እንደሚሉት አማፂዉ ቡድን ትናንሽ ወይም ብዙም ወታደራዊ ጥቅም የሌላቸዉን አካባቢዎች ለጠላቱ እያስታቀፈ ስልታዊ ጠቀሜታ ያላቸዉን ከተሞች ለመያዝ እያጠቃ ነዉ።

የቀድሞዉ የኬንያ ፕሬዝደንት ጎማን ሲጎበኙ
የቀድሞዉ የኬንያ ፕሬዝደንት ጎማን ሲጎበኙምስል Benjamin Kasembe/DW

የቱትሲ ጎሳ ተወላጆች የሚበዙበት የአማፂ ቡድን ከምስራቃዊ ኮንጎ ትልቅ ከተማ ጎማ በስተሰሜን 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የንግድ ከተማን በዚሕ ዛምንት ተቆጣጥሯል።አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ከሚኖርባት ከተማ እና አካባቢዉ የሸሸዉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ከጎማ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ኪባቲ ስታዲዮም ዉስጥ ፈስሷል።
ሕፃን ካዋቂ፣ሴቱ ከወንዱ፣በግ፣ ከፍየሉ እንስሳዉ ከሰዉ በተፋፈጉበት ስታዲዮም ምግብ እና አልባሳት ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ።የ5ቶቹ እናት ልጆችዋን እሕል ለማቅመስ ለመለመን ተገድዳለች።«ለልጆቼ ምግብ መለመን አለብኝ።ገበያ ሄጄ ምፅዋት ካልጠየቅሁ ልጆቼ በረሐብ ይሞቱብኛል።እንግዲሕ እዚሕ ካንያ-ሩቺንያ ኑሮ እንዲሕ ነዉ»
ሌላዋ ቀጠለች።«አዉላላ ሜዳ ላይ ነዉ ያደርነዉ።ልጆቹ በየጊዜዉ ይታመማሉ።ሲዘንብ መሔጃ የለንም።ኑሮ በጣም አሳሳቢ ነዉ።»
ሐኪሞቹም ሕመምተኛዉን ለመርዳት አቅም የላቸዉም።ተፈናቃዮቹ ከሰፈሩበት ከተማ አንዱ የካንያ-ሩቺንያ የሕክምና ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ቴሪይ ቱራኖ እንደሚሉት በደሕናዉ ጊዜ በቀን 10 ሰዉ የሚያማክረዉ ወይም የሚመረምረዉ ሐኪም አሁን ከ400 በላይ ለማማማከር ተገድዷል።
                                        
«በፊት በቀን 10 ሰዎችን ነበር የምናማክረዉ። አሁን ከ400 በላይ ሰዎችን ወደ ለማማከር እንገደዳለን።የቤልጂግ ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን የሚረዳዉ ይሕ የካንያ-ሩቺንያ ሕክምና ማዕከል ማማከርና ህክምና መስጠት አንድ ላይ ይሰራል።ከአቅማችን በላይ ነዉ።»
ዉጊያዉ ትናንትም ቀጥሎ ነዉ የዋለዉ።የመንግስት ጦርr የአማፂያኑ ይዞታዎችን ከሰማይ በጄት፣ከምድር በታንክና መድፍ እየደበደበ ነዉ።ይሁንና ከርቀት የሚደረገዉ ድብደባ የአማፂያኑን ግስጋሴ ከማዘግየት ባለፍ ሙሉ በሙሉ ማስቆም አልቻለም።የብዙዎች ስጋት አማፂያኑ በ2012 እንዳደረጉት ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባትን የጎማ ከተማን ቢቆጣጠሩስ የሚል ነዉ።እዚያዉ ጎማ የሰፈረዉ የምስራቅ አፍሪቃ ሐገራት ጦር አዛዥ ሜጄኔር ጄኔራል ጄፍ ንያጋሕም ጦራቸዉ የሰፈረበትን አካባቢ እንጂ ሙሉ ከተማይቱን ከጥቃት ለመከላከል ስለማቀዱ ያሉት ነገር የለም።
                                        
«እንደ ኃይል አዛዥ፣ለእኔ በጣም ግልፅ የሚሆነዉ እዚሕ የሰፈርነዉ የጎማ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፊያንና  የጦሩን ዋና ዕዝ ከጥቃት ለመከላከል ነዉ።የሌላዉ አካባቢ ዘመቻም ይቀጥላል»
የኢትዮጵያና የሱዳን መዳከም፣እርስ በርስ መነታረክ፣ የዩጋንዳ፣ የብሩንዲ፣ የሩዋንዳና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ረብሊክ መጠላለፍ፣ ከየግጭት ጦርነቱ ጋር ተዳምሮ ኬንያን የምስራቅ አፍሪቃ ወታደራዊ፣ፖለቲካዊ ምጣኔ ሐብታዊ ኃያል ሐገርነቷን እያረጋገጠ ነዉ።
በ1960ዎቹ ለኬንያ ነፃነት ስትታገል የነበረችዉ የኢትዮጵያ ተፋላሚዎችዋ ዉጊያቸዉን ለማቆም የተስማሙት ናይሮቢዎች እንዲሸመግሏቸዉ ተማፅነዉ በናይሮቢዎች ፈቃደኝነትና አስተናጋጅነት ነዉ ነዉ።ለወትሮዉ ታንዛኒያ ትመራዉ የነበረዉን የምስራቅ አፍሪቃ ማሕበረሰብንም ከኬንያ በበላይነት እየመራች ነዉ።
የኮንጎ ጦርን ለመደገፍ ከዩጋንዳ፣ከቡሩንዲ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሌሎችም የአካባቢዉ ሐገራት ለዘመተና ለሚዘምተዉ ጦር ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን ወታደር ያዋጣችዉ ኬንያ ናት።የጦሩ አዛዥ የኬንያ ጄኔራል ናቸዉ።ጄኔራሉ «ፖለቲካዊ ያሉትን መፍትሔ የሚፈልጉት ወይም ተፋላሚዎችን ለማደራደር በዋና ሸምጋይነት የተሰየሙት የቀድሞዉ የኬንያ ፕሬዝደንት ዑሁሩ ኬንያታ ናቸዉ።ኬንያ በምጣኔ ሐብት፣ በዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታም ከምስራቅ አፍሪቃ የሚስተካከለት የለም።
ኮንጎ ግን ማዕድን ታቅፋ\ አረንጓዴ ለብሳ ህዝቧን ታስፈጃለች፣ቀሪዉን ታስርባለች።መቶ ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝቧ 60 በመቶዉ የሚኖረዉ ከድሕነት ጠገግ በታች ነዉ።

ተፈናቃዮች
ተፈናቃዮችምስል Benjamin Kassembe/DW
ከተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ አንዱ
ከተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ አንዱምስል GUERCHOM NDEBO AFP via Getty Images

የናሚቢያ ዘርማጥፋት የካሳ ዉዝግብ 
የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር ሔሬሮና ናማ በተባሉት የናሚቢያ ጎሳ ተወላጆች ላይ ለፈመዉ አስከፊ ግፍ ጀርመን ለመስጠት ያቀደችዉ ካሳ አዲስ ዉዝግብ ቀስቅሷል።የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር ቅኝ አገዛዝን በተቃወሙ የሁለቱ ጎሳዎች ተወላጆችን ከ1904 እስከ 1908 በጅምላ ጭፍጭፏል፣ሌሎቹን አሰቃቷል አግዟልም።
በሁለቱ ጎሳ ተወላጆች ላይ ለደረሰዉ ዘር የማጥፋት ወንጀል ጀርመን 1.1 ቢሊዮን ዩሮ ካሳ ለመክፈል እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ግንቦት 2021 ከናሚቢያ መንግስት ጋር ተስማምታ ነበር።በስምምነቱ መሰረት ካሳዉ የሚከፈለዉ በ30 ዓመት ዉስጥ ነዉ።
የሔሬሮና የናማ ጎሳ ተወካዮች ግን የክፍያዉን መጠንና አብዛኛዉ ክፍያ በናሚቢያ መንግስት በኩል ለመሰረተ ልማት አዉታሮች እንዲዉል መታቀዱን ሲቃወሙ ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ የናሚቢያ ምክትል ፕሬዝደንት ናንጎሎ ምቡምባ የክፍያዉ መጠንና የሚከፈልበት ጊዜ እንዲሻሻል ጠይቀዋል።ምክትል ፕሬዝደንቱ እንዳሉት ለካሳ የተቆረጠዉ 1.1 ቢሊዮን ዩሮ ትንሽ ነዉ።ክፍያዉ የሚሰጥበት የ30 ዓመት የጊዜም ሲበዛ ረጅም ነዉ።
የናሚቢያ መንግስት  በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ባለፈዉ ኃምሌ የጀርመን መንግስትን መጠየቁን ምክትል ፕሬዝደንቱ አስታዉቀዋልም።የስምምነት ማሻሻያዉ ጥያቄ የበርሊን መንግስትን የሚያስደት ዓልሆነም።የሐምቡርጉ የቅኝ ዘመን ታሪክ አጥኚ ዮርገን ሲመረር እንደሚሉት ግን የምክትል ፕሬዝደንት ምቡምባ መግለጫ የናሚቢያ መንስት ስምምነቱን በመፈረሙ ከዜጎቹ የሚሰነዘርበት ወቀሳና ተቃዉሞ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቋሚ ነዉ።
                                            
«ናሚቢያ ዉስጥ በሐገሪቱ መንግስት ላይ የሚደረገዉ ግፊትና ትችት በጣም በመጠናከሩ ነዉ።ትችትና ወቀሳዉ ለረጅም ጊዜ የነበረ ነዉ።በድርድሩ የሄሮሮና የናማ ጎሳዎች በተገቢዉ መንገድ አልተወከሉም የሚል ወቀሳ ድርድሩን አልተለየዉም ነበር።ባለፈዉ ዓመት ደግሞ ናሚቢያ ምክር ቤት ዉስጥ በጣም የተጋጋለ ክርክር ሲደረግ ነበር።ስምምነቱ የገጠመዉ ተቃዉሞዉ በጣም ከፍተኛ ነዉ።»
የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር በሰዉ ሕይወት፣አካል፣ሐብትና ንብረት ላይ ካደረሰዉ ግፍ በተጨማሪ የሁለቱን ጎሳዎች የመኖሪያና የመስሪያ መሬትን በመቀማቱ በሕይወት የተረፈዉን ሕዝብ አኗኗር ክፉኛ አዉኮታል።የናሚቢያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ እንዳስታወቀዉ ቅኝ ገዢዎች ያበላሹትን የሕዝቡን ሕይወት ለመለወጥ ወደ 70 ቢሊዮን ዩሮ ያስፈልጋል።
የጀርመን ፌደራዊ መንግስት በቅርቡ እንዳስታወቀዉ በሁለቱ መንግስታት መካከል የሚደረገዉ ዉይይት አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።አንድ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ  ዉይይቱ በሁለቱም ወገኖች ፈቃደኝነትና በመግባባት መንፈስ እየተደረገ ነዉ።» ብለዋል።
ይሁንና «ዉይይት» የተባለዉ ከዚሕ ቀደም የተደረገዉን ስምምነት ገቢር ለማድረግ እንጂ አዳዲስ የተነሱትን ጥያቄዎች የሚያካትት አይደለም።በቅርቡ አንድ የናሚቢያ መንግስት የመልዕክተኞች ቡድን ጀርመንን ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።ሁለቱ መንግስታት ግን አላረጋገጡም።ቡድኑ እንደተባለዉ ጀርመንን ከጎበኘ ስምምነቱ እንዲሻሻል መጠየቁ አይቀርም።ምክንያቱም የሔሬሮ ጎሳ መሪ ሙቲጂንዴ ካቲጁዋ እንደሚሉት የቪንድሆክ መንግስት ከአጣብቂኝ እንዲወጣ የበርሊኖች ድጋፍ የግድ ያስፈልገዋል።
«የናሚያቢያ መንግስት ቃርጮሽ ዉስጥ ነዉ ያለዉ።ባለስልጣናቱ መንቀሳቀስ አይችሉም።ጀርመን «እባክሽ ገንዘቡን ጨመር፣ጊዜዉን ደግሞ አጠር አድርገሽ ከዚሕ ጭንቅ አዉጪን የሚሉ ነዉ የሚመስለዉ።እንዲሕ ከሆነ ከሕዝቡ ድጋፍና ትብብር ማግኘት ይችላሉ።ጀርመን ይህንን ካላደረገች ግን አጠቃላይ ስምምነቱ ይፈርሳል።»
ከጀርመን መንግስት በኩል ክፍያዉንም ይሁን ጊዜዉን ለማሻሻል ስለመዘጋጀቱ እስካሁን በግልፅ የታየ ፍንጭ የለም።ብዙዎች እንደሚሉት ግን ግፊቱ እያየለ ስለመጣ የጀርመን መንግስት መጠነኛ ማሻሻል ለማድረግ መገደዱ አይቀርም።
የሔሬሮዉ ጎሳ መሪ ሙቲጂዴ ካቱጃም ጎሳቸዉ በክፍያዉ መጠንና ጊዜ ላይ ብቻ ሳይሆን በጎሳዉ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይም አዲስ ስምምነት እንዲደረግ ግፊት ማድረጉን እንደማያቆም አስታዉቀዋል።
ነጋሽ መሐመድ

የተጨፈጨፉት መታሰቢያ
የተጨፈጨፉት መታሰቢያ ምስል picture-alliance/dpa/Staatskanzlei Kiel/P. Kraft
የሔሬሮ ሴቶች ባሕላዊ አለባበስ
የሔሬሮ ሴቶች ባሕላዊ አለባበስምስል HILDEGARD TITUS/AFP

ታምራት ዲንሳ