1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብዙ የሚቀረው የካንሰር ህክምና

ማክሰኞ፣ ጥር 30 2015

የዘንድሮው የዓለም የካንሰር ቀን የካንሰር ህክምናን በተመለከተ የሚታየውን ልዩነት ማቀራረብ እንደሚገባ መልእክት ተላልፎበታል። ቀደም ሲል የበለጸጉት ሃገራት የጤና ችግር ተደርጎ ይታሰብ የነበረው ካንሰር አሁን የኤኮኖሚ አቅማቸው በተዳከመው የአፍሪቃ ሃገራት ዋነኛው ገዳይ በሽታ መሆኑ እየታየ ነው።

https://p.dw.com/p/4NCWV
Symbolbild: Weltkrebstag
ምስል LAURIE DIEFFEMBACQ/BELGA MAG/AFP/Getty Images

ጤና እና አካባቢ

ካንሰር የመላው ዓለም አሳሳቢ የጤና ችግር ከሆነ ሰነባበተ። እስካሁን የህመሙ መንስኤ በውል ካለመታወቁ በተጨማሪ ለህክምና የሚያስፈልገው ወጪ ህክምናው በተገቢው መልኩ ለሁሉም እንዳይዳረስ እንቅፋት እንደሆነ ነው የዓለም የጤና ድርጅት ያመለከተው።  ዓለም አቀፍ የካንሰር ቀን ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት ሲታሰብ መሪ ቃሉ ህክምናውን ለሁሉም የማዳረስን አስፈላጊነት አመላክቷል። 

በየዓመቱ አፍሪቃ ውስጥ 1,1 ሚሊየን አዳዲስ የካንሰር ታማሚዎች እንደሚመዘገቡ እና 700 ሺህዎችም በካንሰር ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ነው የአፍሪቃ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል CDC ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ ኢ ኦግዌል ኦማ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የካንሰር ቀን ሲታሰብ ባስተላለፉት መልእክት የተናገሩት። በዚሁ አጭር መልእክታቸውም አፍሪቃ ውስጥም በብዛት ሴቶች እና ወንዶችን የሚያጠቃው የካንሰር አይነትም ገልጸዋል።አዲሱ የካንሰር ህክምና ማዕከል በሀረር

«የጡት ካንሰርና የማሕጸን በር ካንሰር የአፍሪቃ ሴቶችን፤ ወንዶችን ደግሞ ፕሮስቴት ካንሰር በግንባር ቀደምትነት ያጠቃል። በጎርጎሪዮሳዊው ከ2020 እና 2040 ዓ,ም ውስጥ ባሉት ዓመታትም ከሌሎች ክፍለ ዓለማት ጋር ሲነጻጸር አፍሪቃ ውስጥ በካንሰር ምክንያት የሚከሰተው ሞት ሊጨምር እንደሚችል ከወዲሁ ትንበያዎች ያመለክታሉ።»

Äthiopien Adama University Hospital
ምስል Biruck Habtamu/Adama University Hospital

የበሽታውን አሳሳቢነት በማመልከትም ህክምናው ለሁሉም እንዲዳረስ በተጀመረው ዘመቻ አፍሪቃም የበኩሏን ጥረት እንደምታደርግ ተናግረዋል። የካንሰር ህክምና በዓለም ሲታይ በተለያየ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካን ሀገር አሪዞና ዩኒቨርሲቲ የድህረ ዶክትሬት ምርምር በመሥራት ላይ የሚገኙት በአዳማ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቢንያም ተፈራ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት የካንሰር ህክምና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ እንደነበር በማስታወስም አሁን የሚገኝበትን ደረጃ ገልጸውልናል። እሳቸው እንደሚሉትም ካንሰርን በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና መሰረተ ልማት አቅርቦቱ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤም እጅግ አነስተኛ ነው። የጡት ካንሰርን አስቀድሞ በማወቅ መታከም 

በሀገሪቱ በአንድ ወገን የካንሰር ታማሚው ቁጥር እየጨመረ መምጣት በሌላ ወገን ደግሞ ለህክምናው የሚያስፈልገው ወጪ ጥቂት የማይባሉትን አደባባይ ማውጣቱ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ ለመሆኑ በየማኅበራዊ መገናኛው ዘዴ የሚሰራጩ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዋና ከተማ አዲስ አበባ በየአደባባዩ ለህክምና የገንዘብ እርዳታ የሚለምኑም ጥቂት አይደሉም። ዶክተር ቢንያም፤

እንደ ህክምና ባለሙያው ገለጻ ከሆነ ቁጥሩን በውል ለመግለጽ ዝርዝር መረጃው በእጃቸው ባይኖርም አብዛኛው ከኢትዮጵያ ውጪ ለህክምና የሚሄደው ወገን ለካንሰር ህክምና ፍለጋ ነው። በዚህም ሀገሪቱ ቀላል የማይባል የውጪ ምንዛሪ እያወጣች እንደሆነ መገመት ይቻላልም ባይ ናቸው።

Symbolbild Brustkrebs Untersuchung
ምስል Christin Klose/Themendienst/dpa/picture alliance

እሳቸው በህክምና በሚያገለግሉበት የአዳማ ሆስፒታልም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች የካንሰር ህክምና ለማግኘት የሚመጡ ወገኖችንም በምሳሌነት ያነሳሉ። የካንሰር ህክምና ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚፈለገው መጠን ላለመስፋፋቱ እንቅፋት ከሆኑ መሰረታዊ ምክንያቶች ጥቂቶቹን አንስተዋል ዶክተር ቢንያም። የካንሰር ህክምና ባለሙያው አያይዘው እንደገለጹልን ደረጃ በደረጃ መሻሻል እንደሚኖርባቸው የዘረዘሯቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከታሰበ ትርጉም ያለው የካንሰር መመዝገቢያ ስልት ሊኖር እንደሚገባም አመላክተዋል። እስካሁን መንስኤው በውል እንደማይታወቅ የሚገለጽለት ካንሰርን ለመከላከል ሰዎች ከማጨስ እና አልክሆል መጠጥ በመታቀብ፤ አካላዊ እንቅስቃሴን ማዘውተር እንዲሁም ከታሸጉ ምግቦች ይልቅ አብስለው መመገብ ለጤና እንደሚበጅ ዶክተር ቢንያም መክረዋል። ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን። 

ሸዋዬ ለገሠ 

እሸቴ በቀለ