1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን የውጭ ዝርያ ባላቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት

ማክሰኞ፣ የካቲት 16 2013

«በጀርመን በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የመጨመራቸው ምክንያቱ መንግሥት ችግሩን ለመከላከል በቂ ጥረት አለማድረጉ ብቻ አይደለም።ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ በጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱና በምክር ቤቱም አብላጫውን የተቃዋሚዎች ድምጽ መያዙ ሌላ ለችግሩ አስተዋጽኦ ያደረገ ምክንያት ነው።»

https://p.dw.com/p/3pkPX
Deutschland Hanau | Gedenken an die Opfer des Attentat in Hanau
ምስል Michael Probst/AP/picture alliance

በጀርመን በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች

ሃናው በተባለችው የጀርመን ከተማ 9 ንጹሃን የውጭ ዜጎች  በቀኝ ጽንፈኛ የተገደሉበት አንደኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ታስቧል።የሟች ቤተሰቦች ግድያው በተፈጸመ በዓመቱ ጥቃቱን ማስቀረት አይቻልም ነበር ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መታሰቢያ የተደረገላቸው፣ ከአንድ ዓመት በፊት  በሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ውስጥ ከፍራንክፈርት ወጣ ብላ በምትገኘው በሃናው ከተማ የተገደሉት የውጭ ዜጎች ወይም መሰረታቸው የውጭ የሆነ ጀርመናውያን ናቸው። ቶቢያስ አር በሚል ስም የሚጠራው የ43 ዓመቱ ነፍሰ ገዳይ በጎርጎሮሳዊው የካቲት 9 ቀን 2020 ዓም ምሽት ተኩሶ ከገደላቸው መካከል 5ቱ የቱርክ ዜጎች  ናቸው። ጥቃቱን ካደረሰ በኋላም የ72 ዓመት እናቱን ገድሎ  የራሱንም ሕይወት አጥፍቷል።ጽንፈኛ መሆኑ የተነገረለት ታጣቂው ከግድያው በፊት በኢንተርኔት ዘረኛ ሃሳቦችን ያሰራጭ ነበርም ተብሏል።ለፖሊስም ከዚህ ቀደም መልዕክት ልኳል።የጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች አሁንም መልስ ያላገኙላቸውን የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሳሉ። አንዱ ጥያቄአቸው ግድያው በተፈጸመበት ምሽት የድንገተኛ ጥሪ መቀበያ ስልክ በአግባቡ ለምን አልሰራም የሚለው ነው።ግለሰቡ ግድያውን የፈጸመው በሁለት የተለያየ ቦታ ነው።ስልኩ ሰርቶ ፖሊስ ስለመጀመሪያው ጥቃት ሰምቶ ቢሆን ኖሮ በሁለተኛው ቦታ የተፈጸመውን ግድያ ማስቀርት በተቻለ ነበር ብለው ያምናሉ።ቶብያስ አር ሰዎቹን የገደለው በህጋዊ መንገድ በያዘው የጦር መሣሪያ መሆኑም እንዲሁ ያጠያይቃል። ቀኝ ጽንፈኞች በጀርመን በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በሚፈለገው ደረጃ መከላከል ያልተቻለበት ምክንያትም አነጋጋሪ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው።በጀርመን ዘረኝነትን መቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚሰራው ባብል ኤፋው የተባለው ድርጅት መሥራችና ሃላፊ ዶክተር መኮንን ሽፈራው መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ። ሆኖም በርሳቸው አስተያየት ጥረቱ በቂ አይደለም።ይህም ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።

Deutschland Hanau | Gedenken an die Opfer des Attentat in Hanau
ምስል Michael Probst/AP/picture alliance

ዶክተር መኮንን እንደሚሉት በጀርመን በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለመጨመራቸው እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው መንግሥት ችግሩን ለመከላከል በቂ ጥረት አለማድረጉ ብቻ አይደለም።ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ በጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱና በምክር ቤቱም አብላጫውን የተቃዋሚዎች ድምጽ መያዙ እንደ ዶክተር መኮንን ሌላው ለችግሩ አስተዋጽኦ ያደረገ ምክንያት ነው።ጀርመን ከ33 ሺህ በላይ ቀኝ ጽንፈኞች እንዳሉ ከመካከላቸው ከ13 ሺህ የሚበልጡት  ጥቃት የማድረስ ፍላጎት ያላቸው እንደሆነና ቁጥራቸው ከዚህም በላይ እያደገ መሆኑን  የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ በሃናዉ ግድያ መታሰቢያ ዋዜማ ተናግረዋል። በዶክተር መኮንን አስተያየት በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቀረት ህጎችን  ማውጣትና እነርሱንም ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።በዚህ ረገድ ርሳቸው የሚኖሩበት የበርሊን መስተዳድር የወሰደውን እርምጃ በምሳሌነት ያነሳሉ።ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የውጭ ዜጎች ጥላቻን ለማስቆም ለተቋቋሙ ድርጅቶች የሚሰጠውን ድጋፍ ቢያጠናክር ችግሩ በተጨባጭ ሊቀንስ እንደሚችል ዶክተር መኮንን የድርጅታቸውን ተሞክሮ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ