በዩናይትድ ስቴትስ ወንጀል መስፋፋቱ
ዓርብ፣ ነሐሴ 1 2007የያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ከባተ ጀምሮ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የተገፈፀሙ ግድያዎች መበራከት አሳሳቢ ሆኗል። ባለፉት ሰባት ወራት ብቻም ቺካጎ ዉስጥ 243፤ ባልቲሞር 192 እንዱሁም ዋሽንግተን ዉስጥ 87 ግድያዎች ተፈፅመዋል። ሚልዋኬ በተሰኘችዉ ግዛት ብቻ በዚህ ጊዜ የደረሰዉ ግድያ ባለፈዉ ዓመት በዚሁ ወቅት ከተፈፀመዉ በግማሽ ከፍ ማለቱም ተመዝግቧል። የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስ አዛዥ ካቲ ላነር ባልደረቦቻቸዉ በየጎዳናዉ የሚያስተዉሉትን እንዲህ ያስረዳሉ።
«ግድያዎችን ስንመለከት በስድስትና ሰባት ሽጉጦች50 ወይም 60 ጊዜ ይተኮሳል፤ ልጆች ይገደላሉ፣ የንፁሃን ሰለባዎች ቁጥርም ይጨምራል፤ ይህም እኛን በጣም ያሳስበናል። እናም ዛሬ ከየከተማዉ የምሰማዉ ተመሳሳይ ዘገባ ነዉ።»
በአንድ ስብሰባ ላይ የተገኙት ከሴንት ሉዊስ እስከ ሂዩስተን ግዛት የሚገኙ የፖሊስ አዛዦች ባለፉት ሰባት ወራት ዉስጥ የተፈፀመዉ ወንጀሎች ብዛት የዘንድሮዉን 2015 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ከሌሎቹ የተለየ እንደሚያደርጉት ተናግረዋል። ወንጀል ተበራከተ የሚባለዉም በአንድ ከተማ ወይም ግዛት ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ ነዉ። በዩናይትድ ስቴትስ የወንጀል ድርጊት የተበራከተበት ምክንያት ምንድነዉ ለሚለዉ ፖሊስ ምንም ማብራሪያ መስጠት አልቻለም። ቶማስ ማንጀር ከፖሊስ አዛዦች አንዱ ናቸዉ።
«ይህን ስንነጋገር ለምን ይህ ሊሆን ቻለ ለሚለዉ ምላሽ ለማፈላለግ ሞክረናል፤ ለምንድ ነዉ አሁን እንዲህ የሆነዉ? የምነግራችሁም ይህ ሊሆን ለቻለበት ምክንያት ምንም ግልፅ ምላሽ እንደሌለ ነዉ።»
ኒዉዮርክ፤ ቺካጎ፤ ሂዩስተን እና ፊላደልፊያ በተፈፀሙ ወንጀሎች ምክንያት አሳዛኝ ሪከርድ አስመዝግበዋል። ቺካጎና ዋሽንግተን ዲሲ ዉስጥ የተመዘገቡ ግድያዎች በ20 በመቶ ከፍ ብለዋል። ለዚህም በርካታ የጦር መሣሪያ ዝዉዉር መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ አመልክቷል። በፋብሪካ የተመረቱ አደንዛዥ እፆችና ወሮበሎች የሚፈፅሟቸዉ የአመፅ ተግባራትም በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። በየደጃፋቸዉ የሚፈፀመዉን የሚመለከቱ በርካታ የየከተማዎቹ ነዋሪዎች በሁኔታዉ እጅግ ተደናግጠዋል።
«እጅግ የከፋ ነዉ። ከዚህ በፊት እዚህ እንዲህ አልነበረም።»
«ሰዎች ተዳክመዋል፤ ተሰላችተዋል፤ እናም ለምንም ግድ የለንም የሚሉ ይመስላል።»
ፖሊስ ጠንካራ የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን የሚመለከት ሕግ እንዲኖርና በጦር መሣሪያ ታግዞ ወንጀል በሚፈፀመዉ ላይ ቅጣቱ እንዲጠብቅም ጠይቋል።የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር በዚህ ረገድ እንዲረዳዉም ጥሪዉን አቅርቧል። በዚያም ላይ ዜጎች እንዲተባበሩ፤ ካለ ማኅበረሰቡ ትብብርም ምንም ማድረግ እንደማይቻልም ፖሊስ ይናገራል።
«ከኅብረተሰቡም ድጋፍ እንፈልጋለን፤ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በጣም ያስፈልገናል።»
እንዲያም ሆኖ ግን የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በአጋዥነት እዚጋ ለማካተት አስቸጋሪ ነዉ የሚሆነዉ። በተለይ የባልቲሞር ወይም ዋሽንግተን ዲሲ ኗሪዎች ከፖሊስ ጋር እንዲተባበሩ ማለት ነዉ። ምክንያቱም በዚነዚህ አካባቢዎች የፖሊስ ተዓማኒነት ከተሸረሸረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ