1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወልቂጤ ከተማ የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2014

ለጉራጌ ዞን ራስን በራስ የማስተዳደር ወይም በክልል የመዋቀር ጥያቄ መንግሥት መልስ እንዲሰጥ የሚጠይቅ አድማ በወልቂጤ እና ሌሎች የዞኑ ከተሞች መደረጉን የዐይን እማኞች ተናገሩ። ጉንችሬ ከተማ ስብሰባ እንዲሰበሰቡ የተደረጉ የመንግስት ሰራተኞች ስብሰባውን እረግጠው ወተው ሰላማዊ ሰልፍ አድርገውታል።

https://p.dw.com/p/4FKuL
Äthiopien Gurage Streik
ምስል privat

በወልቂጤ ከተማ የስራ ማቆም አድማ ተደረገ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን ያቀረበው በክልል የመዋቀር ጥያቄ መልስ አላገኘም በሚል በዛሬው ዕለት በወልቂጤ ከተማ የስራ ማቆም አድማ እንደተደረገ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬሌ ተናገሩ። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት አድማው የተደረገው ትላንት በወልቂጤ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ተበትኖ በነበረ የአድማ ጥሪ መሰረት ነው። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአይን እማኝ ከአዲስ አበባ በ158 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወልቂጤ ምንም አይነት የንግድ እንቅስቃሴ ሆነ የትራንስፖርት እንዳልነበር ተናግረዋል ።

አድማውን የጠራው ማን እንደሆነ እንደማይታወቅ ለዶቼ ቬሌ የተናገሩት የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ  የሆኑት አቶ ተስፋ ነጋ  የመንግስት መስሪያ ቤቶች ክፍት ቢሆኑም ሰራተኞች  ግን አልገቡም ሲሉ  አድማው ባለቤት እንደሌለው ነገር ግን በትላንትው እለት ወረቀት በተለያዩ ቦታዎች ተበትኖ ነበር ብለዋል ። ተቃውሞው  በተለያዩ የወረዳ ዞኖች ላይ ተመሳሳይ ተቃውሞ ሰልፎች  እንደነበሩ የተናገሩት አቶ ተስፋ ተቃውሞው « በጉብሬ፣ ቡርና፣ አክሊሉ ወረዳ ላይም  በተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል፤ ጉንችሬ ከተማ ስብሰባ እንዲሰበሰቡ የተደረጉ የመንግስት ሰራተኖች ስብሰባውን እረግጠው ወተው ሰላማዊ ሰልፍ አድርገውታል» ሲሉ አክለውም ምንም ነገር ሳይጀመር ጀምሮ ከተማዋ በኮማንድ ፖስት ስር አድርገውታል ብለዋል ሆስፒታሎች ክፍት ሲሆኑ  የመንግስት መስሪያ ቤቶች  ሰራተኛ ባይገባም ክፍት ናቸው  በተቃራኒው ግን ትራንስፖርት የንግድ ተቋማት እና መዝናኛ ቦታዎች  ሙሉ ለሙሉ ዝግ  መሆናቸውን ተናግረዋል።

Äthiopien Gurage Streik
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ክልል ለመሆን በቀረበው ጥያቄ ላይ የሚወስን ስብሰባ በመጪው ሐሙስ ስብሰባ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ምስል privat

ሌላ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የወልቂጤ  ነዋሪ የጉራጌ ዞን ከረዥም ጊዜ በፊት ያቀረበውን በክልል የመደራጀት ጥያቄ  ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገልጻሉ።

«እንደሚታወቀው የጉራጌ ዞን የክልል ጥያቄ  ከጠየቀ እረጅም ግዜ ሆኖታል። በክላስተር ይደራጃል ተብሎ ከፌደራል አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ነበር የፌደራል አካላት  ከቀበሌ ጀምረው  በወረዳው ውይይት አድርገው  ነበር ቢሆንም  ይህንን ማህበረሰቡ  አልተቀበለም ዛሬ ትራንስፖርት  ሙሉ ለሙሉ የለም የንግድ ሱቆችም እየሰሩ አይደለም። ምንም እንቅስቃሴ የለም ማለት ይቻላል። ከተማው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ላቀረብንለት ጠያቄ «እኔ በተዘዋወርኩባቸው ቦታዎች ምንም ረብሻ አላየሁም። የፀጥታ አካላትም ከተማዋ ላይ እየተዘዋወሩ ነው» ብልዋል ።የፀጥታ ኃይሎች ከ5ቀን በፊት ወደ ከተማዋ መግባታቸው በወጣቱ ማህበረሰብ ላይ ጥሩ ስሜት እንዳልፈጠረ ለዶቼ ቬሌ ተናግርዋል።

Äthiopien Gurage Streik
በወልቂጤ ከተማ ሱቆች ተዘግተው መዋላቸውን የዐይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል privat

ሌላኛዋ የወልቂጤ ከተማ ተወላጅ እና ነዋሪ  ወይዘሮ ዛይዳ ግዛቸው  የክልልነቱ ጥያቄ እንዲመለስ ከፍተኛ ተሳትፎ ከሚያደርጉ የማህበረሰብ ክፍሎች አንድዋ ናቸው።

ወይዘሮ ዛይዳ የዛሬው የስራ ማቆም እና ከቤት ያለ መውጣት አድማ ከህብረተሰቡ ብሶት የመጣ ነው ትላለች ከዚ በፊት ብዙ ግዜ ሰላማዊ ሰልፍ እና የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም የአካባቢው ሽማግሌዎች ናቸው ያስቆሙን ብላለች «ያገር ሽማግሌው ጉዳዩን  በከተራት ይዘውት ነበር   ከተራት ማለት የጉራጌ አንድ ባህላዊ ሸንጎ ስርአቱ ነው  ስለዚያ ነበር እስካሁን ዝም የተባለው» ብላለች ።

ወልቂጤ ከተማ ብቻ እንዳልሆነ አድማው የተደረገው የተናገረችው ወ/ሮ ዛይዳ   አጎራባች ወረዳዎችም አድማውን እንደተቀላቀሉ ገልፃለች ከተማዋ ኮማንድ ስር መሆንዋ የተነገረን ቅዳሜ ሽማግሌ ሲሰበሰብ ነው እንጂ በይፋ የታወጀ ወይም የተነገረን ነገር የለም ብላለች።

የዶይቼ ቬለው ጋዜጠኛ ሸዋንግዛው ወጋየሁ  ያነጋገረው ዳውድ  ከማል  አድማው የተጠራው ዘርማ በተባለው የወጣቶች አደረጃጀት እንደሆነ ተናግርዋል  ። አደረጃጀቱን በሊቀመንበርነት የሚመራው ዳውድ አድማው የጉራጌ  ህዝብ በሰላማዊ መንገድ ላቀረበው ህገ መንግሥታዊ ጥያቄ መንግሥት መልስ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ የተጠራ መሆኑን ተናግሯል።

Äthiopien Gurage Streik
የጉራጌ ዞን ክልል ለመሆን ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ግፊት ለማድረግ የተጠራው አድማ ከወልቂጤ በተጨማሪ በሌሎች የዞኑ ከተሞች እንደነበር ለመረዳት ተችሏል። ምስል privat

አስራ ስድስት የደቡብ ክልል ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሁለት ክልሎች የሚያዋቅር የውሳኔ ሐሳብ አጽድቀው ጥያቄዎቻቸውን ለኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም  አቅርበዋል። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ግን እስካሁን ተመሳሳይ ውሳኔ አላሳለፈም። በህዳር  ወር በ2011ዓምየዞኑ ምክር ቤት የጉራጌ ክልላዊ መንግሥት ለማቋቋም የሚጠይቅ ውሳኔ ያሳለፈው  ሲሆን በቀጣዩ ወር ታህሳስ ላይ  ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ምክር ቤት አቅርቦ ነበር።

የጉራጌ ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ማህሌት ፋሲል 

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ