1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተጠለሉ የጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ተፈናቃዮች

ሐሙስ፣ መስከረም 19 2015

ሰሞኑን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው በሻምቡ ከተማ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች አስከፊ ያሉትን የህይወት ገጽታ እየመሩ መሆኑን አመለከቱ፡፡ እስካሁን በዩኒቨርሲቲው ደርሰው የተጠለሉት ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ያለ በቂ አልባሳትና እንክብካቤ የከፋ ህይወት ውስጥ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/4HXq5
IDPs from Horo guduru wollega
ምስል Seyoum Getu/DW

ሰሞኑን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው በሻምቡ ከተማ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች አስከፊ ያሉትን የህይወት ገጽታ እየመሩ መሆኑን አመለከቱ፡፡

እስካሁን በዩኒቨርሲቲው ደርሰው የተጠለሉት ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ያለ በቂ አልባሳትና እንክብካቤ የከፋ ህይወት ውስጥ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው፡፡  “ያለንበት ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ተፈናቅለን የመጣን ቁጥራችን ከመብዛቱ የተነሳ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ቅትር ጊቢ በአንድ ዶርም እስከ 50 ሰው ተጨናንቀን እያደርን ነው፡፡ ሁላችንም ተፈናቅለናል፡፡ ከእንግዲህ ተስፋ የምናደርገው አገርም የለን፡፡” ይህን አስተያየት የሰጡን ባለፈው ሳምንት ሓሙስ መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ታጣቂዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ በከፈቱት ጥቃት ተፈናቅለው ሻምቡ ከተማ በሚገኘው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተጠልለው የሚገኙ፤ ነገር ግን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልተናገሩ ናቸው፡፡

እኚህ አስተያየት ሰጪ እናት የአራት ልጆች እናት እና ነፍሰጡር ናቸው፡፡ በፀጥታው መደፍረሱ ምክኒያት አራት ልጆቻቸውን ይዘው ሻምቡ ከተማ ለመድረስ የሁለት ቀናት የሌትና ቀን የእግር ጉዞም ፈጅቶባቸዋል፡፡ ተፈናቃይዋ ለመፈናቀላቸው ምክኒያት የሆነውን ግጭት ሲያስረዱ፤ “የሆነው እሮብ ማታ በ11 መስከረም 2015 ሁለት የታጠቁ አካላት መሳሪያ መቀማማታቸውና ገቢያ መረበሹ ነው የሰማነው፡፡ በማግስቱ ለሓሙስ ንጋት ለ12 ሩብ ጉዳይ ላይ ቤት ስለነበርን ማንነታቸውን ያላወቅነው ታጣቂዎች በቤታችን የተኩስ እሩምታ ከፈቱብን፡፡ አስቀድሞ ግን የአማራ ታጣቂዎች ማስፈራሪያ ሲያደርሱብን ነበር፡፡ ከዚያን ሲያልፉ ቤት ከምንሞት ብለን ግማሾቻችን ወደ ጫካ፣ የበቆሎ ማሳ ውስጥ ተደብቀን አሳለፍን፡፡ በየማሳው እንደ አውረ ታድነው የተገደሉ ነበሩ፡፡ ከነ አጠገቤ እንኳ አራት ሰዎች ሲሞቱ ተመልክቻለሁ፡፡ በማግስቱ ዓርብ ስደት ጀምረን እሁድ እዚህ ሻምቡ ደረስን” ብለዋል፡፡

IDPs from Horo guduru wollega
ምስል Seyoum Getu/DW

በእለቱ በአከባቢው ከሚሊሻ ውጭ ህብረተሰቡን ከጥቃት የሚያስጥል አንድም የፌዴራልም ሆነ የክልል ኃይላት እንዳልነበሩም እኒ ተፈናቃይ ገልጸውልናል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ማህበረሰቡ ላይ ኦነግ ሸነ የተባለን ታጣቂ ቡድን ትቀልባላችሁ በሚል ከአማራ ታጣቂዎች ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ግን አመልክተዋል፡፡ ተፈናቃይዋ የራሳቸውን እና የልጆቻቸውን ህይወት ለጊዜውም ቢሆን ማዳናቸውን ቢያረጋግጡም አሁንም ግን ቀልባቸው አልረጋም፡፡ “ከእኛ የባሰ አሁን እንቅልፍ የሚነሳን መሄድ የማይችሉትን አዛውንቶች ቤት ውስጥ ዘግተንባቸው ወጥትን ይሞቱ ይኑሩ አሁን የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ከወጣን በኋላ ግን በርካቶች መሞታቸውን ነው የሰሚ ሰሚ የምንረዳው፡፡ እኛም ስንወጣ ታጣቂዎች እያንዳንዱን ቤት እንመለስባቸዋለን እያሉ ያገኙትን ሁሉ ሲዘርፉም ነበር፡፡ አሁን ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከደረስን በኋላ የአከባቢው ማህበረሰብ ምግብ ያመጡልናል፡፡ ይዘን የወጣነው ልብስ ባለመኖሩ እስከዛሬ ግን እንዲሁ የሚለበስ ነገር እንኳ አላገኘንም፡፡ እስካሁን መጥቶ ያነጋገረን የመንግስት አካልም የለም፡፡ ምንም ተስፋችን ጨልሟል” ይላሉም፡፡

ስሜ ይቆይ ያሉ አንድ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ መምህር በበኩላቸው ከጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ ከተማው የሚመጡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከእለት ተእለት መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በብዛት ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ያካተተ ነው ያሉት መምህሩ፤ አሁን በተጨናነቀ አኳኋን እንደሚኖሩ እና ከምንም በላይ ግን ጥሏቸው የመጡ የቤተሰቦቻቸው ጉዳይ እየረበሻቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ሻምቡ ከተማ የደረሱ ተፈናቃዮቹ ሙሉ በሙሉ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸውም ብለዋል፡፡

IDPs from Horo guduru wollega
ምስል Seyoum Getu/DW

ስለተፈናቃዮቹ እና የዞኑ አጠቃላይ ያልተረጋጋው የፀጥታ ሁናቴ ከዞኑ ጸጥታ እና አስተዳደር ባለስልጣናት ለማጣራት ያደረግነው ተከታታይ ጥረቶች አልተሳኩም፡፡

ስለሰሞነኛው የሆሮ ጉዱሩ ዞን አሙሩ እና ጃርደጋጃርቴ ወረዳዎች በበርካታ ቦታዮች የጥቃት ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎች “የአማራ ታጣቂዎችን” ሲወቅሱ፤ “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸነ’) በሚል የሚጠሩት ታጣቂ ቡድኖችን ለጥቃቱ ተጠያቂ የሚያደርጉም አሉ፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫው፤ ለጃርደጋ ጃርቴው ግጭት መቀስቀስ “ሸነ” ያላቸውን “የኦሮሞ ነጻነት ጦርን” ወቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ “የኦሮሞ ነጻነት ጦር እና የአመራ ኢመደበኛ ታጣቂዎች” ያሏቸው በአከባቢው ንጹሃንን እየገደሉ እያፈናቀሉም ስለሆነ መንግስት የተሻለ ትኩረት ሰጥቶ አከባቢውን እንዲያረጋጋው መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ