1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ክልል የጤና ተቋማት መጎዳት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2015

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ከሰሞኑ ይፋ ባደረው ዘገባ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቷል። ድርጅቱ እንደሚለው በክልሉ ውስጥ ረዥም ጊዜያትን ያስቆጠረው ግጭት ጦርነት በምዕራብ ወለጋ ቤጊ ወረዳ ብቻ የሚገኙ 42 የጤና ማዕከላትን ከጥቅም ውጪ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/4T7vS
Mendi city
ምስል DW/N. Desalegn

ጤና እና አካባቢ

በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ እልባት ያገኛል ተብሎ የተጠበቀው በመንግሥት እና መንግሥትን በሚፋለሙ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ግጭት አለመግባባቱ እንደታሰበው መፍትሔው በአጭር የሚቋጭ አልሆነም፡፡ በግጭቱ ምክኒያት በበርካታ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች፤ በተለይም በምዕራቡ በወለጋ ዞኖች፣ በደቡብ ኦሮሚያ በኩል ደግሞ በጉጂ ዞኖች እንዲሁም በማዕከላዊ የክልሉ አካባቢ ጎልቶ የተስተዋለው የፀጥታ ችግሩ አርሶ አገር የሚቀልበውን ገበሬ ከቀዬው በማፈናቀሉ ማሳው ጦም አድሯልና ቀውሱ ቀላል አይደለም፡፡ ግጭት በሚደርስባቸው አካባቢዎች በጉልህ ጉዳት ከደረሰባቸው መሠረተ ልማቶች ደግሞ አንደኛው የጤናው ዘርፍ ነው፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው ግጭት ለሰው ልጅ ወሳኝ በሆነ የጤና መሰረተ ልማት ላይ የጎላ ጉዳት መድረሱን ጥናት አድርጎ ባወጣው ዘገባ ጠቁሟል። እንደ ዘገባው የጤና መሰረተ ልማትና የውኃ ማዳረሻዎች በዚህ ግጭት ክፉኛ ተጎድተዋል።

በምዕራብ ወለጋ የ100 ሺዎች መኖሪያ በሆነችው ቤጊ ወረዳ ብቻ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ሁሉም 42 የጤና ማዕከላት ወይ ተዘርፈዋል አሊያም ወድመዋልም ይላል የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC)፡፡ ICRC ግጭት በሚከፋባቸው አካባቢዎች ማዕከል ከፍቶ ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚጥር ለዶይቼ ቬለ ያስረዱት የድርጅቱ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የኮሚዩኒኬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ዘውዱ አያለው፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ግጭቶች መስፋታቸውን ተከትሎ ድርጅቱ በነቀምት በከፈተው ማዕከሉ ሁኔታውን በቅርበት ለመከታተል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡ በዚህም በአካባቢው ያሉ በተለይም ከጤና መሰረተ ልማት ውድመት ጋር ተያይዞ የሚደርሰውን ውድመት በመከታተል ሰብዓዊ ምላሽ ለመስጠት ተቋሙ የቻለውን ያህል ይንቀሳቀሳል ነው ያሉት፡፡

Symbolbild Afghanistan - Rotes Kreuz
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ አርማምስል picture-alliance/Ton Koene

የዓለም አቀፉ የቀይ-መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ዘገባ ሲቀጥል፤ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በጉዱሩ ወረዳ የሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፤ ከዚህ በፊት በአጎራባችም የሚገኙ ከአምስት ወረዳዎች የሚመጡትን ታካሚዎች ተቀብሎ የሚያስተናግድ ቢሆንም አሁን በጥይት ተበሳስቶ የውኃ ማጠራቀሚያዎቹም ከጥቅም ውጪ እንደሆኑም ይገልጻል። ከዚህ ሆስፒታል አልጋ፣ የህክምና ቁሳቁሶች፣ የቀዶ ህክምና መሳሪያዎች፣ መድሃኒት እና አምቡላንሶች ሳይቀር ተጠራርጎ ተዘርፏልም ነው ያለው።  በዚህም ምክንያት ከአካባቢው በግጭቱ በገፍ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ለተለያዩ ህመሞች ተዳርገው ወደ ሆስፒታሉ ቢደርሱም ለሆስፒታሉ ሠራተኞች አገልግሎቱን መስጠት አዳጋች እንዲሆንባቸው አድርጓል ነው የተባለው፡፡

ዶ/ር ዓለማየሁ ኪሪ የተባሉትን የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ያናገረው ዓለም አቀፉ የቀይ-መስቀል ኮሚቴ  በማዕከሉ አሁን የጤና አገልግሎት መስጠት እጅጉን ፈታኝ መሆኑን ተረድቷል፡፡ «የአስቸኳይ ጤና መድሃኒቶች እጥረት አሉብን፡፡ የቀዶ ህክምና ክፍላችንም እንዳማይሆን ሆኗል፡፡ አልጋ የለንም፡፡ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከርም ቢሆን በመውደሙ የውሃ ችግር አለብን፡፡ የህዝብ መድሃኒት ቤት ጭምር ተዘርፎ በመውደሙ ሥራችንን አወሳስቦብናል፡፡» ዶ/ር ዓለማየሁ የጉዱሩ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡

በኦሮሚያ አሁን ባለው አለመረጋጋት ቢያንስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለከፋ ሁኔታ መጋለጣቸው ነው የሚነገረው፡፡ አብዛኞቻቸው ደግሞ ሰብኣዊ ድጋፍን የሚሹ ቢሆኑም ባለው የፀጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅርቦቱ እየተስተጓጎለ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ በተለይም በጉጂ፣ በቦረና እና በወለጋ መሰል ችግሮች እንደሚበዙ የሚወጡ ዘገባዎች ዋቢ ናቸው፡፡

ግጭት በተራዘመባት በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የሚኖሩትና ዶይቼ ቬለ ያናገራቸው ነዋሪ፤ በዚያች ወረዳ ከአንዲት የወረዳ ከተማ ውጪ ባሉ ሁሉም ቀበሌያት እንኳን የጤና ማዕከላት ምንም አይነት ማኅበራዊ መገልገያ ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡባት ወረዳ ሆናለች ይላሉ፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ እንደጠየቁት ነዋሪ አስተያየት፤ ከዚያች ወረዳ ወጥተው ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ መታከም በራሱ መንገድ ላይ የጥይት እራት ያደርጋል፡፡ ወደ አጎራባች ወረዳ ጊዳ እንኳ ለህክምና በመሄድ ላይ ሳሉ ወጥተው የቀሩ መኖራቸውን በዋቢነትም ያቀርባሉ፡፡

Mendi city
መንዲ ከተማ ምስል DW/N. Desalegn

ዓለም አቀፉ ቀይመስቀል ኮሚቴ ዋቢ ያደረጋቸው ሙሉ ታከለ የተባሉ ተፈናቃይ እናት «ከየአቅጣጫው የሚወረወረውን ተኩስ ልንቋቋመው የምችለው አይደለም፡፡ እናም ሕይወታችንን ለማዳን ስንል ተፈናቅለናል፡፡ ነገሩ በተለይም ለሕጻናት እንደ ቅዠት ያለና በጣሙን አስቸጋሪ ጊዜ ነው፡፡ ተፈናቅለን ከቤታችን ስንወጣ በእጃችን የያዝነው አንድም ነገር የለም፡፡ ያለንን ሁሉን ትተን ነው በሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በምትገኘው ባሎ የደረስነው፡፡ እዚህም ከደረስን በኋላ ይሄ ነው ያለን አንድም አካል የለም፡፡» ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ በህክምና ሥራ የሚተዳደሩ ባለሙያ ስሜ ይቆይ ብለው ለዶይቼ ቬለ እንዳስረዱትም አሁን አሁን በአካባቢው ሰው የሚታከምበት የጤና ቁሳቁስ ፈታኝ መሆኑ ሰዎች ታክሞ ለመዳን በሚችል ቀላል በሽታ ሕይወታቸውን እያጡ ነው ይላሉ፡፡ በዚህች አገምሳ በተባለች የአሙሩ ወረዳ ሁለተኛ ከተማ ቢያንስ ከ70 ሺህ በላይ ዜጎች ከአጎራባች የገጠር ቀበሌያት ተፈናቅለው ከተማዋን እንደሚያጨናንቋት እኚህ የጤና ባለሙያ አክለው ተናግረዋል።  በመንግሥት በኩልም መልሰን እናቋቁማችኋለን ከሚል ተስፋ ባለፈ በቂ ድጋፍ እንኳ የማይቀርብበት እንደመሆኑ፤ ሰው ቢታመም መድሃኒት የለም፤ ቢኖርም መግዣው በተፈናቃዩ ማኅበረሰቡ አቅም የማይታሰብ ነው ይላሉ፡፡ እንደ ባለሙያው አሁን በዚያች ወረዳ የጤና አገልግሎት የሚሰጠው ኦቦራ በተባለች በወረዳው ከተማ እና በዚህች እሳቸውም በሚያገለግሉበት አገምሳ ከተማ ብቻ ነው፡፡

የጤና ባለሙያው በዚህ አሁን በክፍተኛ ሁኔታ የሰው ህይወት የሚያልፍበት የህክምና ችግር ከወሊድ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው የገለጹት። ኦክሲጅን እና መሰል የጤና አገልግሎት ቁሳቁሶች በዚህ ማግኘት አስቸጋሪም ነው ይላሉ፡፡ ኢላሙ፣ ዴራ፣ ወልቂጤ፣ ሉማ ዋሊ፣ ምግር እና ጆባ ዶባን በሚባሉ የወረዳው ከተሞች የነበሩ የጤና ጣቢዎች ሙሉ በሙሉ ወድመው የህክምና ቁሳቁሶቹም በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗልም ነው ያሉት፡፡ ባሉት ሁለት የጤና ተቋማትም የሚሰጠው አገልግሎት አነስተኛ ነው፡፡

Karte Äthiopien Gutin AM

ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር  ጋር ለሰብኣዊ እርዳታ የሚሠራው ዓለም አቀፉ ቀይመስቀል ኮሚቴ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ እና በጉጂ ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት እጅጉን ከፍተኛ በመሆኑ ይህንኑን መከወን ፈታኝ እንደሆነበት ያስረዳል፡፡  በኦሮሚያ ያለው የተቋማቱ አቅምም እጅግ መሟጠጡንም አመልክቷል፡፡ ይሁንና  በግጭቱ እጅጉን የተጎዳው ማኅበረሰብ የሚገኝበት በምዕራብ ወለጋ ዞን ቡልቡል፣ ቤጊ እና ቆንዳላ ፤ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ባሎ፣ ባሬዳ እና ኮምቦሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሰብዓዊ ድጋፎችን የማድረስ ሥራ ከሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በመሆኑ እተሞከረ ነው ተብሏል፡፡

የዓለም አቀፉ የቀይ-መስቀል ኮሚቴ የኮሚዩኒኬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ዘውዱ አያለው እንደገለጹልን፤ በነዚህ አከባቢዎች ያለው ችግር ከመስፋቱ የተነሳ ሁሉንም እርዳታ ፈላጊ ማኅበረሰብ ማዳረስ አስቸጋሪ ነው። ተቋሙ አሁን ያወጣው የጤና መሰረተ ልማት ውድመትን የሚያሳየው ዘገባም ተደራሽ የሆኑ ውስን ቦታዎችን ብቻ ያካተተ ነው ተብሏል። በኦሮሚያ እየተስተዋለ ባለው ግጭት አለመረጋጋቱ ክፉኛ እየተጎዳ ነው ስለተባለው የጤና መሰረተ ልማት ከክልሉ ጤና ቢሮ አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም፡፡ በተለይም ለክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንግሥቱ በቀለ እንዲሁም ለምክትላቸው ዶ/ር ተስፋዬ ክበበው በጽሑፍም ጭምር ስለጉዳዩ አስረድተናቸው ለዛሬ ምላሻቸውን አላገኘንም፡፡ ለኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርም በተለይም በህዝብ ግንኙነት ክፍል በኩል ያቀረብነው ጥያቄው ምላሽ አላገኘም፡፡

ስዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ