1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃውያን ዘንድ ያለው የመጤዎች ጥላቻ 

ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2011

ከዚህ ጋር በተያያዘ የደቡብ አፍሪቃ ስም በብዛት ይነሳል። ከሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሄዱ ጥቁር አፍሪቃውያን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከመጤ ጥላቻዎች ጋር በተያያዘ ጥቃት ይደርስባቸዋል። በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእነዚህን መሰል ጥቃቶች ተጠቂዎች መሆናቸውን ሲናገሩ ይደመጣል።

https://p.dw.com/p/3MlDk
Südafrika Xenophobie Rassismus Unruhen
ምስል Getty Images/G.Guercia

በአፍሪቃውያን ዘንድ ያለው የመጤዎች ጥላቻ

ከ 11 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ 62 የውጭ ሀገር ዜጎች በመጤ ጠሎች ጥቃት ምክንያት ተገድለዋል። ከ200 ሺ በላይ ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከጥቂት ወራት በፊትም የውጭ ዜጋ የሆኑ የንግድ ቤቶች ላይ ባነጣጠረ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገድለዋል። በደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእነዚህን መሰል ጥቃቶች ተጠቂዎች መሆናቸውን ሲናገሩ ይደመጣል። በሀገሪቱ ውስጥ በተለይ ከሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት የመጡ ስደተኞች ብዙ የጥላቻ ፈተና እንደሚገጥማቸው ራሳቸው ደቡብ አፍሪቃዊያኑ ይናገራሉ።

«ደቡብ አፍሪቃውያን ጥቁር የውጭ ዜጎችን ብቻ ነው እንደ የውጭ ሀገር ዜጋ የሚያዩት። ነጮች ወይም አውሮፓውያን ግን እንደ ውጭ ዜጋ አይታዩም። ምክንያቱም ነጮች ሁልጊዜ የተሻሉ ናቸው የሚል የአፓርታይድ አስተሳሰብ አለ። እኛ ደቡብ አፍሪቃዊ ነን። ይሁንና ቆዳቸው የጠቆረው እንደ ውጭ ዜጋ ታይተው አያያዛቸውም የተለየ ይሆናል።»  
« አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪቃውያን ማድረግ የምንወደው አንድ ነገር ቢኖር ጭፈራ ቤት ሄደን እንጠጣለን፣ እንደሰታለን ሌሎች የውጭ ዜጎች ግን ወደዚህ መጥተው ይማራሉ። ከዛም የፈለጉትን ስራ ያገኛሉ። እኛ ደቡብ አፍሪቃውያን ግን ጭፈራ ቤት እንበጠብጣለን፣ እንጠጣለን፤ ትምህርታችን ላይ እምብዛም አናተኩርም።»

The 77 Percent. Strassenbefragung zum Thema Fremdenfeindlichkeit in Südafrika
ምስል DW


ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ከሚገኙት የውጭ ሀገር ዜጎች 70 በመቶ የሚሆኑት የዚምባቡዌ፣ ሞዛምቢክ እና ማላዊ ዜጎች ናቸው። በሀገሪቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም የማይናቅ መሆኑን እዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ። መሐሙድ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት በዚችው ሀገር የሚኖረው ወጣት "በመጤ ዜጎች ላይ ያለው ጥላቻ አሁን በረድ ብሏል" ይላል። « መቼ እና እንዴት እንደሚከሰት አናውቀውም። በአሁኑ ሰዓት ግን በሰላም እየኖርን ነው።»
የመጤ ጠሎች ችግር የደቡብ አፍሪቃ ችግር ብቻ አይደለም። ጋናዊው ማይክል ኦቲ ሀገሩ ውስጥ ስላለው የመጤዎች ጥላቻ ችግር ያብራራል። « በጋናውያን እና በናይጄሪያውያን መካከል የቆየ ታሪክ አለ። ጋና ከቀኝ ግዛት ስትወጣ ሁሉም ጋናዊ ያልሆኑ ሰዎች ሀገሪቱን ለቅቀው መውጣት አለባቸው ይባል ነበር። በቅርቡም በጋናውያን እና በናይጄሪያውያን መካከል ግጭት ነበር። ጋናውያን ቢዝነሳችንን ወሰዱብን በሚል ናይጄሪያውያንን በመወንጀል በእነሱ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።»
ካሜሮናዊቷ ሚሚ ሜፎ ሀገሯ ውስጥ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ሳይሆን እርስ በእርስ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ጥላቻ ያመዝናል ትላለች። እሷ እንደምትለው ለዚህ ተጠያቂው የሀገሪቱ ፖለቲካ ነው።«መንግሥት የደቡቡ ማህበረሰብን ከሰሜኑ ጋር እንዲከፋፈል እየተጠቀመበት ያለ ይመስላል። የአንድ ሀገር ሰው ሆነው ምናልባትም አንዱ ከሌላ ብሔር ስለሆነ ብቻ ሲገፋ ይስተዋላል። በቡሉ እና ቤቲ ጎሳዎች ላይ የጥላቻ እና የዘረኝነት አገላለፆችን ሲጠቀሙ ሰምተናል። ይኼ በአሁኑ ወቅት ካሜሮን ውስጥ ትልቅ ችግር ሆኗል። መፍትሄ የማይበጅለት ከሆነ በሁለቱ የሀገሪቱ ማዕዘኖች ያለውን ችግር ይበልጥ ትልቅ ያደርገዋል።»
በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ይኖር እንደው ጠይቀን ነበር።በአዲስ አበባ የሚኖረው አዳፍር ኢትዮጵያ ውስጥ "ለውጭ ዜጎች ላይ ካለው ጥላቻ ይልቅ ከሌሎች አካባቢዎች በመጡ ማህበረሰቦች ወይም ብሔሮች ላይ ያለው ጥላቻ ያመዝናል" ይላል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ እርስ በእርስ የሚስተዋለው ጥላቻ አዳፍር እንደሚለው የተለያዩ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም ዋናው ነገር ግን ፖለቲካው እንደሆነ ይናገራል። « አሁን የሀገራችን ፖለቲካ በብሔር ላይ የተመሠረተ ነው። ፖለቲካዊ አደረጃጀቱ ፣ አወቃቀሩ በብሔር ላይ የተመሠረተ ነው። የአንዱ ብሔር የሌላውን ብሔር ጠላት አድርጎ መነሳቱ ደግሞ በጣም መጥፎ ነው።»

Sendung  The 77 Percent
ምስል DW/S. Möhl
Südafrika Xenophobie Unruhen Rassimus
ምስል Getty Images/M.Longari

አፍሪቃውያን በብሔርም ሆነ በዜግነት ደረጃ እንዳይጠላሉ ወጣቶቹ መፍትሄ ነው የሚሉት አለ። ሚሚ «እንደሚመስለኝ ወጣቱ ስለሀገሩም ሆነ ስለ አህጉሩ እጣ ፈንታ ያለው ውሳኔ ከእጁ ነው። የሚከፋፍሏቸው እና መስራት የሚገባቸውን የማያደርጉ ፖለቲከኞች እና ፕሬዚደንቶችን መስማት የለባቸውም። እኛ ወጣቶች የራሳችንን ሚና መጫወት ይኖርብናል። ለሌሎች ሀገራት ወጣቶች የመጤዎች ጥላቻ ስለሚያስከትለው ነገር በማስረዳትም ሊሆን ይችላል።» ትላለች። 
አዳፍር ደግሞ፤ « የሆነውን ወደኃላ ትተን፤ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። የኃይማኖት ተቋማትም ተከታዮቻቸውን በሚያስተምሩበት ዘርፍ ጥላቻ ለማንም እንደማይጠቅም ማስተማር አለባቸው። ህብረተሰቡም አዕምሮውን ክፍት አድርጎ ለውይይት ዝግጁ መሆን አለበት።»
አፍሪቃ ውስጥ በአፍሪቃውያን ዘንድ ስለሚታየው የመጤዎች ወይም የራሱ ማህበረሰብ ብሔሮች ጥላቻን እና ይህንን ለመቅረፍ ወጣቶች መፍትሔ ነው የሚሉትን የቃኘው የወጣቶች ዓለም ዝግጅታችንን በድምፅ መከታተልም ይችላሉ።


ልደት አበበ
ተስፋለም ወልደየስ