1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ በጦርነት የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች ጥሪ

ዓርብ፣ ጥር 3 2016

ጦርነቱ ከቆመ 15 ወራት ቢቆጠሩም፥ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች አሁንም ወደቀዬአቸው አልተመለሱም። በሽረ፣ ዓብይአዲ፣ መቐለ ያሉ ተፈናቃዮች መንግስት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው እንዲሁም ዓለምአቀፍ ለጋሾችም የእርዳታ እጃቸው እንዲዘረጉላቸው ጥሪ አቀረቡ። የትግራይ ክልል ከ1 ሚልዮን በላይ ተፈናቃዮች በመጠልያዎች ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/4bAmX
Äthiopien Tigray, Mekele 2024 | Binnenvertriebene in der Tigray-Region
ምስል Million Hailesilassie/DW

በትግራይ በጦርነት የተፈናቀሉ ወደቀያቸዉ እንዲመለሱ ጥሪ አቀረቡ፤ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የምግብ እርዳታ እንዲሰጣቸዉ ጥሪ ቀርቧል

ጦርነቱ ከቆመ 15 ወራት ቢቆጠሩም፥ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች አሁንም ወደቀዬአቸው አልተመለሱም። በሽረ፣ ዓብይአዲ፣ መቐለ ያሉ ተፈናቃዮች መንግስት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው እንዲሁም ዓለምአቀፍ ለጋሾችም የእርዳታ እጃቸው እንዲዘረጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ ከ1 ሚልዮን በላይ ተፈናቃዮች በመጠልያዎች እንደሚኖሩ ይገልፃል። 

የጦርነት ተፈናቃይ የ72 ዓመቱ አዛውንት ገብረሚካኤል ወልደገብርኤል ያሉበት ሁኔታ ሲገልፁ የተናገሩት ነው። አዛውንቱ አቦይ ገብረሚካኤል ከቀዬአቸው ምዕራብ ትግራይ ዞን ፀገዴ ወረዳ የተፈናቀሉት በኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ሐይሎች መካከል፥ በ2013 ዓመተምህረት ጥቅምት ወር ጦርነት ሲቀሰቀስ ነው። ህፃናት ጨምሮ ስምንት ሆነው ቤታቸው ጥለው የወጡት እኝህ አባት ፥ ያለፉት ከሶስት በላይ ዓመታት ኑሮአቸው በሽረ ከተማ ጉና ተብሎ በሚታወቅ ግዚያዊ የተፈናቃዮች መጠልያ ነው። 

የያለፉት ዓመታት የመጠልያ ኑሮአቸው ለጠላት እንኳን የማትመኘው የሚሉት አቦይ ገብረሚካኤል፥ በሚበላ ምግብ እና የሚጠጣ ውሃ እጦት እየተሰቃዩ፣ ራሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው ለበሽታ ተዳርገው፣ ክረምት እና በጋ እየተፈራረቃቸው በአንዲት የፕላስቲክ ቤት እየኖሩ እንዳለ አጫውተውናል። መንግስት ይሁን እርዳታ ሰጪ ተቋማት ረስተውናል በማለት የሚያማርሩት አቦይ ገብረሚካኤል፥ ከጦርነቱ መቆም ዓመት በኃላ እንኳን ወደቀዬአቸው አለመመለሳቸው ተስፋ እንዲያጡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። 

በትግራይ የተለያዩ መጠልያዎች የሚገኙ በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በእርዳታ አቅርቦት እጥረት ለሞትና በሽታ እየተጋለጡ መሆኑ እና ዘላቂ መፍትሔ ማጣት በመግለፅ ቅሬታ ያቀርባሉ። እንደ ክልሉ አስተዳደር መረጃ በትግራይ አንድ ሚልዮን ገደማ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቶች፣ ግዚያዊ መጠልያ ሸራዎች እንዲሁም ቤተእምነቶች እና ሌሎች ስፍራዎች ተበትነው ይገኛሉ።በመቐለ ከሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠልያጣብያዎች መካከል በሆነው እና 13 ሺህ ተፈናቃዮች የሚገኙበት 70 ካሬ መጠልያ ጣብያ የሚኖሩት ሌላው ተፈናቃይ ግደይ ይሕደጎ፥ ለክልሉ አስተዳደር እና ለፌደራል መንግስቱ ወደቀዬአችን እንዲመልሱን በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ተግባራዊ ምላሽ የለም ይላል። አቶ ግደይ "ትላንት እንኳን ራሱ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት መጥተው ነበር። እኛም ጥያቄአችን አቅርበናል። ከእርዳታ ይልቅ ወደቦታችን መመለስ ነው የምንሻው ብለን ነገርናቸው። ጥረት እያደረግን ነው፣ በቅርቡ ትመለሳላችሁ ነው ያሉን። ግን እንዲሁ በቅርብ ትመለሳላችሁ እየተባልን አመታት አለፈ። ምንም ቁርጥ ያለ ነገር የለዉም። ዓምናም እንዲሁ ትመለሳላችሁ እየተባለ ነው ዓመቱ ሙሉ ያለፈው። አሁን የሚሉንም ከአምናው የተለየ ነገር የለውም" ይላሉ።

ሌላው ከተንቤን ዓብይዓዲ ያነጋገርናቸው ከሑመራ የተፈናቀሉአቶ ብርሃነ በበኩላቸው ፥ ፖለቲከኞቹ ከታረቁ በኃላ እኛን ረስተውናል በማለት ያማርራሉ። እንደ አቶ ብርሃነ ገለፃ የተፈናቃዩ ዋነኛ ጥያቄ ወደቦታው መመለስ እና ሰርቶ መኖር ነው። 

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የጦርነቱ ተፈናቃዮች በፕሪቶሪያው ውል መሰረት ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ እያወጣቸው በነበረ መግለጫ ሲጠይቅ ነበር። በዚህ የተፈናቃዮች ጉዳይ ዙርያ ከፌደራሉ መንግስት የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ