1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማሌ ክልል 3.8 ሚሊዮን ሕዝብ ርዳታ ይሻል

ረቡዕ፣ የካቲት 29 2015

የሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱቃድር ረሺድ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ በሰጡት መረጃ ዳዋ ፣ አፍዴር እና ሊበን ዞኖች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል። በድርቁ ምክንያት ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ህዝብ በምግብ እጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/4OPHf
Dürre und Trockenheit am Horn von Afrika
ምስል Mulugeta Ayene/AP Photo/picture alliance

ወደ 300 ሺሕ የሚጠጉ እንስሳት ሞተዋል

በሶማሌ ክልል አብዛኞቹ አካባቢዎች ባለፉት ሶስት አመታት በቂ ዝናብ ባለመጣሉ ለምግብ እጥረት የተጋለጠዉ ሕዝብ ቁጥር 3.8 ሚሊየን  መድረሱን የክልሉ መስተዳድር አስታወቀ።የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት በድርቅ ስለተጎዳዉ ሕዝብ ብዛትና ስለሚገኝበት ሁኔታ እንዲያስረዱን ባለፈዉ ሳምንት በተደጋጋሚ ብንደዉልም ስልካቸዉን አላነሱም ነበር።አሁን እንደሚሉት ግን  ዳዋ ፣ ሊበን እና አፍዴር ዞኖች ዉስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት አልቀዋል።ሕዝቡን ለመርዳት ህብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ  ጠይቀዋልም።

የሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱቃድር ረሺድ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ በሰጡት መረጃ ዳዋ ፣ አፍዴር እና ሊበን ዞኖች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል። በድርቁ ምክንያት ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ህዝብ በምግብ እጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።እንደ አቶ አብዱቃድር ገለፃ - አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ናቸው በተባሉ ዞኖች በተለይም በዳዋ ዞን አንድ መቶ ሺህ ነዋሪ ወደ መጠለያ ገብቷል። እንዲሁም ከአፍዴር እና ሊበን ዞኖች ለእንስሳቶቻቸው ግጦሽ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሄዱ ነዋሪዎች ባሉበት ቦታ እንስሳቶቻቸው ችግር ላይ መሆናቸውን  ጠቁመዋል።

ሶማሌ ክልል እንስሳት አሁንም እየሞቱ ነዉ
ሶማሌ ክልል እንስሳት አሁንም እየሞቱ ነዉምስል Mesay Teklu/DW

 

ላለፉት ሶስት አመታት በአካባቢዎቹ ዝናብ ባለመጣሉ ምክንያት ወቅቱን ጠብቆ ዳግም የተከሰተው የዘንድሮ ድርቅ በሚሊየን የሚቆጥሩ ዜጎችን ለውሀ ችግር ዳርጓል ያሉት ኃላፊው በተለያዩ አካላት ውሀ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ቢሆንም ተደራሽ ያልሆነ ህብረተሰብ መኖሩን አስረድተዋል።በክልሉ ዳግም በተደቀነው የዘንድሮ ድርቅ በርካታ እንስሳት መሞታቸውንም አቶ አብዱቃድር ለዶይቼቬሌ ተናግረዋል።የክልሉ እና የፌደራል መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ ከጋሽ አካላት ሰብዓዊ እርዳታን ጨምሮ በውሀ እና በእንስሳት መኖ አቅርቦት ዙርያ እየሰሩ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው መላው ህብረተሰብ ከጎናችን በመቆም ርብርብ ያድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።ዉይይት፤ ኢትዮጵያ ድርቅና ረሐብ የተጣባት ሐገር

ባሳለፍነው አመት ተመሳሳይ ወቅት በክልሉ አስራ አንድ ዞኖችን ባዳረሰው አስከፊ ድርቅ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት መዘገባችን ይታወሳል።

 መሳይ መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ