ለወሲብ በባርነት የሚሸጡ ሴት ናይጄሪያውያን
ዓርብ፣ ሚያዝያ 15 2013ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ ከ 20 000 በላይ ሴት ናይጄሪያውያን በሜዲትራንያን በኩል አድርገው ጣሊያን ገብተዋል። አብዛኞቹ ገና 18 አመት ያልሞላቸው ናቸው። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሆነ ከነዚህ ሴቶች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ፤ የህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ሰለባ ሆነዋል ወይም አሁንም በእነዚህ ሰዎች ህይወታቸው ላይ አደጋ ተደቅኖ ይገኛል። የዶይቸ ቬለዋ ጋዜጠኛ ክርስቲን በቅድሚያ የተወያየችው ጉዳዩን በሚገባ ከሚያውቁ ሁለት ሴቶች ጋር ነው። ፕሪንሰስ ከእነዚህ አንዷ ናት። ወደ ጣሊያን የሄደችው፣ አንዲት «ማዳም» ብላ የምትጠራት ሴት አግባብታት እንደሆነ ትናገራለች። ፕሪንሰስ በወቅቱ ናይጄሪያ ውስጥ የምግብ አብሳይ ሆና ትሰራ ነበር።« ምግቧን ተመግባ እንደጨረሰች፣ ምግቡ እንደጣፈታት ገልፃልኝ ወደ ኤዶ ግዛት እንድመጣ ጋበዘችኝ። ወደ ጣሊያን መሄድ ከፈለኩም ወጪዬን እንደምትችልልኝ ነገረችኝ። እዛም በአንድ የናይጄሪያ ምግብ ቤት ውስጥ ጥሩ አብሳይ ሆኜ መስራት እንደምችል ነገረችኝ።»ፕሪንሰስ በህገ ወጥ ፓስፖርት ጣሊያን ትገባለች። እዛ ስትደርስ የጠበቃት ስራ ምግብ አብሳይነት ሳይሆን የወሲብ ሰራተኛ ሆኖ ወደ ጎዳና መውጣት ነው። « በእውነት በጣም አስፈሪ ነበር። አሁን ድረስ አስታውሳለሁ ፤ ኮርሶ ማርጋሪታ ወደሚባል ጎዳና ነበር አስገድደው የወሰዱኝ። እዛም በርካታ ግማሽ እርቃናቸውን የሆኑ ሴቶች አገኘሁ። ግራ ተጋባሁ። መፀለይ ማልቀስ ጀመርኩ።» ፕሪንሰስ የምትፈራው አሰሪዎቿን ብቻ አልነበረም። በስለት እና በሽጉጥ ያስፈራሯት ደንበኞች እንደነበርሩም በምሬት ትናገራለች። ይሁንና ወጣቷ ናይጄሪያዊት ከገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ በቀላሉ መውጣት አልቻለችም።« አንደኛው ምክንያት እኔን ወይም ወንድ ልጄን እንደሚገድሉት አስፈራሩኝ። በዛ ላይ ርዳታ የምጠብቀው ሰው አላውቅም ነበር። በተለይ ደግሞ በቋንቋ ምክንያት»በመጨረሻ ፕሪንሰስ አንዲት እንግሊዘኛ የምትናገር ሴት አግኝታ እውነታው ሴተኛ አዳሪ ሳትሆን ባሪያ መሆኗን ትነግራታለች። ወደ ፖሊስም ሄዳ ታመለክታለች።
ሌላዋ ተመሳሳይ እጣ የደረሳት ሴት ብለሲንግ ናት። እሷም ወደ ጣሊያን ሄዶ ለመስራት ባገኘችው እድል መጀመሪያ ላይ ደስተኛ ነበረች። ምንም አይነት ጥርጣሬ እንዳልነበራትም ነው የምትናገረው።« አስታውሳለሁ እሁድ ቀን ነው የደረስኩት። ከዛም ሁሉም ይዤው የመጣሁትን ነገር ፤ የእጅ ቦርሳዩን፣ ማስረጃዎቼን በሙሉ አምጪ ብለው ወሰዱብኝ። ከዛም 65000 ዩሮ እዳ እንዳለብኝ ነገሩኝ። ያኔ ነው በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እጅ እንደገባሁ የተረዳሁት» ነገር ግን እሷም ከገባችበት ችግር በቀላሉ መውጣት አልቻለችም። ያላት እድል ወደ ጎዳና ወጥቶ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የደረሳቸውን የሀገሯ ልጆች ፍዳ መቅመስ ነበር። ብለሲንግ ቃል የተገባላት ስራ በአንድ የኮምፒውተር መጠገኛ ሱቅ ውስጥ እንደምትሰራ ነበር። ሁኔታውን ፍፁም መቀበል አልቻለችም።« ለማታውቁት ወንድ ራስን አሳልፎ መስጠት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ_? ከአንድ በላይ ወንድ ጋር በየቀኑ መገናኘት ማለት? እንደዛ አይነት አልባሳትን አድርጎ ጎዳና መውጣት ማለት? በዛን ክብሬ ሲነጠቅ ነው የተሰማኝ። በጣም በሸኩ። ሞቴን ነበር የተመኘሁት። ለዚህ አልነበረም የተማርኩት። ይህ አልነበረም አላማዬ። ለዚህም ነበር ፖሊስ ጣቢያ ፈልጌ ጉዳዩን ለማመልከት የወሰንኩት። »
የፀረ ማፊያ አቃቢ ህግ የሆኑት ሊና ትሮቫኖ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ተመሳሳይ በደል ለገጠማቸው ሴቶች ቆመው ተከራክረዋል። እሳቸውም ሁሉም ሴቶች የሚነግሩን ነገር ተመሳሳይነት አለው ይላሉ።« ሁሉም ሴቶች ፤ አስተናጋጅ፤ ፀጉር አስተካካይ ወይም ነጋዴ ሆነው እንደሚሰሩ ነው የተነገራቸው። አውሮፓ ያሉ የጓደኞቻቸውን ፎቶዎች ፌስ ቡክ ላይ ገብተው ሲመለከቱም የሚያገኙት ምስል ፤ ስኬትን የሚያሳዩ ናቸው። ህገ ወጥ ደላላዎቹም ሲቀርቧቸው ፤ በጓደኝነት ስሜት፤ ሁሉን ነገር አድርግላችኋለሁ ምንም ሀሳብ አይግባችሁ እያሉ ነው። ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ነው የሚነግሯቸው።» የሚገርመው ነገር የሴቶቹ ታሪክ መመሳሰሉ ብቻ አይደለም። አብዛኞቹ ጣሊያን ውስጥ ለወሲብ ስራ የተሸጡት ሴቶች ከአንድ አካባቢ ወይም ግዛት መሆናቸው ነው። የአለም አቀፉ የስደረኞች ጉዳይ ድርጅት ሰራተኛ የሆኑት ማሪያ ሻድሮቫ ምክንያትን እያፈላለጉ ይገኛሉ። « የኤዶ ግዛት በፍልሰተኞች ይታወቃል። እንደሚመስለን በ80ያዎቹ አካባቢ ነው የጀመረው። በአካባቢው ብዙ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰሩ ጣሊያናውያን ነበሩ። እና እነዚህ ጣሊያናውያን የናይጄሪያ ሴቶችን አግብተው ይዘዋቸው ወደ ሀገራቸው ሄደዋል እና እነሱ ናቸው ንግዱን የጀመሩት ይባላል። »ሌላው ደግሞ ማሪያ እንደሚሉት በኤዶ ግዛት ጥንቆላ እና ሰዎችን ማታለል በሰፊው የተስፋፋበት ግዛት ሆኖ አግኝተውታል።
ራንሲስኮ ዴል ግሮሶ ፤ የጣሊያን ፖሊስ ናቸው። ዋናው ችግር በህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ሰለባ የሆኑት ሴቶች ለፖሊስ ደፍረው ክስ አለማቅረባቸው ነው ይላሉ። « ሰለባ የሆኑት ሰዎች ወደ እኛ መጥተው ታሪካቸውን ሊነግሩን ይገባል። በሀገራችን መንግሥት፤ በሀገራችን ህግ ማስከበር ላይ እምነት ሊኖራቸው ይገባል።»
ጣሊያን ውስጥ የሚገኝ አንድ የናይጄሪያ ማህበርን ወክለው የሚናገሩት ሳምሶን ኦሎሙ ግን ለሴቶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ክስ መመስረት ከባድ የሚያደርገውን ምክንያት ያስረዳሉ። የመጀመሪያው ችግር የቋንቋ ችግር ሲሆን ሁለተኛው ችግር ደግሞ ፍርሀት ነው።« ሴትየዋ ታስፈራራቸዋለች። ሄዳችሁ የምታመለክቱ ከሆነ ወረቀት የላችሁም። ወደ ሀገራችሁ ይመልሷችኋል። እኔን የምታጋልጡ ከሆነ እናታችሁን፤ ወንድማችሁን አስገድላለሁ። ጥንቆላው እና መተቱ ሲጨማመርበት የእያንዳንዱ ሰው አዕምሮ ልክ እንደ ርዕደ መሬት ይናጋል።ግራ ይገባል።»
ይህንን ተቋቁመው ክስ የሚመሰርቱ ሰዎች ደግሞ አፋጣኝ የፍትህ ምላሽ እንደማያገኙ ነው ለወሲብ ንግድ የተሸጡት ሴት ናይዴሪያውያን የሚገልፁት። አቃቤ ህግ ሊና ትሮቫቶ ግን ወቀሳውን ያጣጥላሉ።« በአጭር ወራት ውስጥ ብዙ ሰዎችን ፤ ከ 100 በላይ በቁጥጥር ስር አውለናል። በ 2018 ዓ ም እስከ 198 ዓመት ድረስ በእስር ሊያስወጣ የሚችል ብይን በብዙ ህገ ወጥ ሰው አዘዋሪች ላይ ተበይኗል። እኔንጃ እኛ ቢሮ ፈጣን ነን። ሰለባዎቹ ምስክርነታቸውን ሳይሰጡ ነው ምርመራውን የምንጀምረው። ሰለባዎቹ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆንም ቃላቸውን እንዲሰጡ የሚቀርቡት ህገ ወጦቹ ሰዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ነው። »
ፖሊስ ፍራንሲስኮም ቢሆኑ ተጎጂ የሆኑት ሰለባዎች ከፖሊስ ጋር ተባብረው የሚሰሩ እና አዘዋዋሪዎቹን የሚጠቁሙ ከሆነ ከለላ እንደሚሰጣቸው እና ስጋት ውስጥ እንዳይገቡ ያበረታታሉ። ስቃዩን የቀመሱት ፕሪንሰስ እና ብለሲንግ ደግሞ መፍትሄ የሚሉት ሌሎች ሴቶች የእነሱ አይነት ስቃይ ሳይደርስባቸው ገና ጋይጄሪያ ሳሉ አደጋ ውስጥ እንዳይገቡ ለወጣት ሴቶች መሰራት አለበት። ብለሲንግ «ወጣቶቻችንን ባላቸው ነገር ፀንተው እንዲኖሩ ልናሰለጥናቸው ይገባል። ይህንን ካደረግን ከፍ ሲሉ የዚህ ሰለባም ሆነ የድርጊቱ ፈፃሚ አይሆኑም። ሌላው ደግሞ ወደ ሀገራችን ተመልሰን ከመንግሥት ጋር አብረን መስራት ይኖርብናል። ወጣቶች ነፃ ትምህርት እና የስራ እድል ሊያገኙ ይገባል። ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰለባዎች ይህንን ነፃ የትምህርት እድል እና ስራ ያላገኙ ናቸው።»
ክሪስቲን ሙንድዋ
ልደት አበበ