ለኢትዮጵያ ጦርነት የአሜሪካ የመፍትሔ ሐሳብ
ዓርብ፣ ጳጉሜን 4 2014የኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ባስቸኳይ ቆሞ ተፋላሚ ኃይላት የአፍሪቃ ሕብረት በሚመራዉ የሸምጋዮች ቡድን እንዲደራደሩ ዩናይትድ ስቴትስ በድጋሚ ጠየቀች።የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ምክትል ቃል አቀባይ ቬንዳት ፓቴል እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሓት ዉጊያዉን አቁመዉ እንዲደራደሩ በአፍሪቃ ቀንድ አሜሪካዉ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የሁለቱንም ወገኖች ባለስልጣናት ጠይቀዋል።ልዩ መልዕክተኛዉ በቅርቡ አዲስ አበባን ሲጎበኙ የኢትዮጵያን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርና የጠቅላይ ሚንስትሩን የፀጥታ አማካሪን ማነጋገራቸዉን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ቃል አቀባይ ቬንዳት ፓቴል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣አምባሳደር ሐመር በእስካሁኑ የኢትዮጵያ ቆይታቸው፣ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬዲዋን ሁሴን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም፣ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ በአፍሪቃ ህብረት መሪነት ወደ ሰላም ድርድር መግባት በሚያስፈልግበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።አምባሳደር ሐመር፣ለህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካሄልም፣ ተመሣሣይ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ምክትል ዋና ቃል አቀባዩ አመልክተዋል።የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ቃል አቀባይ በዚሁ መግለጫቸው ላይ፣ህወሓት ከትግራይ ውጭ ጥቃት መቀጠሉን፣የኢትዮጵያ መንግስት በአየርና በምድር የሚያደርገውን ጥቃት፣እንዲሁም ኤርትራ ዳግም ወደ ግጭቱ መግባቷን በድጋሚ አውግዘዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት ስለሚካሄደው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አስመልክተው ሲናገሩም፣"በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ እየተካሄደ ባለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ ሞሊ ፒ፣ልዩ መልዕክተኛ ሐመርና ሌሎች የአሜሪካ ዲፕሎማቶች፣ከአፍሪቃ ህብረት እንዲሁም ከቀጣናው ቁልፍ ተዋናዮች፣ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ከአውሮፓ ህብረትእና ከብሪታንያ ልዑካን ጋር ምክክር ያደርጋሉ።"የዚህ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ዓላማ፣መንግስትና ህወሓት ወታደራዊ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙና ኤርትራ ወደ ድንበሯ እንድትወጣ ግፊት ለማድረግ መሆኑን ፓቴል አስረድተዋል።
ለዚህ ግጭት ምንም ዓይነት ወታደራዊ ሐፍትሔ እንደሌለ አፅንኦት የሰጡት ምክትል ቃል አቀባዩ፣ብቸኛው መፍትሔ ተፋላሚ ኀይላቱ የሰላም ድርድር ማድረግ ብቻ ነው ብለዋል።በዚህ ግጭት የኢትዮጵያ ሕዝብ በብዙ ተጎድቷል ያሉት ፓቴል፣ ዩናይትድስቴትስ ዋነኛ ለጋሽ ሃገር እንደመሆኗ መጠን በድጋሚ በግጭት ምክንያት ለተጎዱት የነፍስ አድን ሰብዓዊ ዕርዳታ መስጠት እንደምትቀጥል አስረድተዋል።በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ግጭትና ድርቅ እያስከተሉ ያለው ተጽእኖ አሁንም እያሳሰበን መሆኑ ልብ ሊባል ይገዋል ሲሉም ምክትል ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ዩናይትድስቴትስ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ቁርጠኛ አቋም እንዳላትም አውስተዋል።"ዩናይትድስቴትስ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ያላትን እምነት እንደገና እደግመዋለሁ።የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውና የሚገባውን ብልጽግና ለማግኘት የሚያስችል ዕድል የሚኖረው ዘላቂ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው።"በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በአምባሳደር ሐመር ስለሚመራው የአሜሪካ የሰላም ጥረት፣እዚህ ዩናይትድስቴትስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የሰላምና ልማት ማዕከል የቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅን ዶይቸ ቨለ አነጋግሯቸዋል።
ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ፣አምባሳደር ሐመር ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉበኝት አስመልክቶ፣ከተለያዩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ጋር በተወያዩበት ጊዜ ድርጅታቸውን በመወከል ተገኝተው ነበር።"የዓለም ሁሉ ወዳጅነት ያስፈልገናል፤የዓለም ሁሉ መተባበር ያስፈልገናል እና በዚህ በኩል የአሜሪካ መንግስት መተባበር መቼም ለማንኛውም ሃገር ዛሬ ደግሞ አሜሪካ ትልቅ ሃገር ስለሆነ በዓለምም የታወቀ የተከበረ ስለሆነ ብዙም ዕርዳታ ስለሚሰጠን፣በብዙ ነገር ግንኙነት ስላለን እንደዚህ ያለ አማካሪ መጥቶ፣እኔ ዐሳቤ ይሄ ነው ይህን ቁልፍ ይዤ መጥቼያለሁ ቢል በቂ አይደለም።ኢትዮጵያኖቹን አዳምጦ እነሱ የሚሉትን ችግር ተረድቶ ተንትኖ ፈትፍቶ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት ይህ ነውና ችግሩ ይህ ነው በእነሱ ፍላጎት ይፈታ ብሎ መሞከር በጣም ጥሩ ነውና እንዲህ አድርጎ ማዳመጡን እኔ በጣም አመስግኜዋለኹ።"
የአሜሪካው ልዩ ልዑክ፣ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከመሄዳቸው በፊት ከኢትዮጵያን ጋር የተወያዩት፣ወደፊት የተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደርጉ ዘንድ የሚያስችላቸውን አስተያየት ለመስማት ነበር።ከዚህ አኳያም ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንዳሉት፣አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ምን እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያስችላቸውን ዐሳብ ይዘው ሄደዋል የሚል ዕምነት አላቸው።
"ቁጭ ብሎ አንድ ዐስራ አምስት ከሚሆኑ ኢትዮጵያኖች ጋር ተራ በተራ የሚናገሩትን አዳመጠ።እና መጨረሻ ላይ ትንሽ ነገር ተናገረ።በእያንዳንዱ በኩል ያለው አስተያየት፣የኢትዮጵያ ችግር ምን አንደሆነ መስማት ተዘጋጅቶ አንድ ሰዓት ተኩል እዛ ቁጭ ብሎ ማዳመጡን ግምት ሰጥቼዋል።ከዚህ በተረፈ ደግሞ እኛን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን የተናገርነውን ከምር እንደሚወስድ ተስፋ አደርጋለኹ።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ