1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሃገሬ የጥበብ ምሽት

ዓርብ፣ መጋቢት 10 2013

ኢትዮጵያዊ የሚለዉን ፍቅር ያገኘሁት ከነጋሽ ጥላሁን ገሰሰ ሙዚቃ ዉስጥ ነዉ። ከነጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን፤ ከነጋሽ ደበበ ሰይፉ ግጥም ዉስጥ ነዉ። ኢትዮጵያዊነትን የተማርኩት፤ ከነሃዲስ አለማየሁ ድርሰት ዉስጥ ነዉ። ከነአቤጎበኛ አመጽ ዉስጥ ነዉ። ኪነ-ጥበብ ከእናት አባቶቻችን እኩል የወለደን የማነታችን ቀራጭ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3qnBo
Deutschland Äthiopische Kunst Gemeinde  in Nürnberg
ምስል privat

ስደት የነፍሳቸዉን ጥሪ ቀምቶ ለእንጀራ ብቻ እያኖራቻዉ ያሉ ብዙ የጥበብ ሰዎች አሉ

«በጣም የሚደነቁ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ተዋንያን፤ ሙዚቀኞች፤ የሥነ-ፅሑፍ ሰዎች አዉሮጳ የነፍሳቸዉን ጥሪ ቀምታ ለእንጀራ ብቻ እያኖረቻቸዉ ያሉ ብዙ የጥበብ ተሰጥኦ ያላቸዉ ሰዎች እንዳሉ አይቻለሁ። ይህ በጣም ያሳዝናል»  

በጀርመን ኑረምበርግ ከተማ «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» በሚል መድረክ ላይ ተሳታፊ የሆነዉ ደራሲና ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ከተናገረዉ የተወሰደ ነዉ። ሰለሞን ሞገስ ጀርመን ሃገር መኖር ከጀመረ አንድ ሦስት ዓመት እንደሆነዉ ይናገራል። በኢትዮጵያዉያን ዘንድ በሥነ-ጽሑፎቹ በተለይ በግጥሞቹ ታዋቂ የሆነዉ ሰለሞን ሞገስ «እዉነትን ስቀሏት » ከሚለዉ የግጥም መድበሉ ጋር አራት መጽሐፍትን ለአንባብያን አብቅቶአል። ሰለሞን ሞገስ የጥበብ ፍቅሩ አዉሮጳ በመኖሩ፤ እሱ እንደሚለዉ በባህር ተዉጦ እንዳይቀር በኑረንበርግ ጀርመን ነዋሪ የሆነችዉ ሳሮን ግርማ፤ ያሰባሰበችዉ «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» መድረክ እየረዳዉ እንደሆን ሲናገር በኩራት ነዉ። በሳሮን ግርማ የተመሰረተዉ እና ሁለተኛ ዓመቱን የያዘዉ «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» መድረክ ኢትዮጵያዉያንን ብቻ ሳይሆን ጥበብ አፍቃሪ የዓለም ዜጎችን ሁሉ የሚያሰባስብ እንደሆነ እና መድረኩ ኢትዮጵያዉያን ለዉጭዉ ዓለም የሚያስተዋዉቅም እንደሆን ይነገራል። «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» መስራች ሳሮን ግርማ መድረኩ ዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓልን ለሁለተኛ ጊዜ በድምቀት እንዳከበረ ገልፃለች። መድረኩንም ለማሰባሰብ የወሰነችዉ ባህልዋን ለአዲሶቹ ትዉልዶች ልጆችዋ ለማስተዋወቅ፤ ኢትዮጵያን፤ ከኢትዮጵያዉያን ጋር ሆኖ በጥበብ ለማድመቅ ነዉ።

Deutschland Äthiopische Kunst Gemeinde  in Nürnberg
ምስል privat

«ሃገሬ የጥበብ ምሽት» የተባለዉ የኪነ-ጥበብ መድረክ ከጀመረ ሁለት ዓመት ሊሆነዉ ነዉ። በራሴ ተነሳሽነት ነዉ የጀመርኩት። ባለቤቴ ጀርመናዊ ነዉ። ስለዚህም የሃገሪን ባህል ለልጆቼም ለማስተዋወቅ ነዉ። የኢትዮጵያ በዓላትን፤ ብቻችን እንዳናከብር፤ ከኢትዮጵያዉያን ጋር አንድ ላይ ለማክበር፤ ስለኢትዮጵያ እንድናስብ እና ኢትዮጵያዉያንን ለማሰባሰብ ያደረኩት ነዉ። ከዚህም አልፎ በዚህ መድረክ ለሌላዉ ዓለም ሃገራት ሰዎች ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅም ነዉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ በዓላት እንደ ሆያሆዬ አዲስ ዓመት ሲሆን፤ ተሰባስበን፤ በአረጋዉያን መጦርያ ከሚኖሩ በሆስፒታል ከሚገኙ እንዲሁም፤ በስደተኞች መኖርያ ከሚገኙ አዛዉንት ኢትዮጵያዉያን ጋር በመሆን አክብረናል። አበባየሆሽ፤ ሆያሆዬ ጨፍረናል። እነዚህ አረጋዉያን አበባየሆሽ እና ሆያሆዬ ስለጨፈርን እንደባህላችን ገንዘብ ሰጡን። በገንዘቡን የአባይን ግድብ ማሰርያ እንዲሆን በማሰብ የአባይ ማሰርያ ኩፖንን ገዝተናል።»

በየወሩ ነዉ ማለት ነዉ የምትሰባሰቡት?

« አዎ ዝግጅታችን የምናካሄደዉ በወር አንድ ጊዜ ነዉ። ዝግጅቱ ሊቀርብ ሁለት ሳምንት ሲቀረዉ ልምምድ እናደርጋለን። ለጊዜዉ ቦታ ስለሌለን እኔ መኖርያ ቤት ዉስጥ ነዉ የምንለማመደዉ። ሁለት ሳምንት ከተለማመድን በኋላ በሦስተኛ ሳምንት ዝግጅቱን እናቀርባለን። በመድረኩ ግጥም፤ መነባንብ የሚያቀርቡ ልጆች አሉ። ዝግጅቱን ለመካፈል ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች ለምሳሌ ከሙንሽን፤ ከፍራንክፈርት የሚመጡ ልጆች አሉ። ለምሳሌ ባለፈዉ ዓመት የአድዋ ድል በዓልን ተሰባስበን ያከበርነዉ በፍራንክፈርት ከተማ ነዉ። የአድዋ ድል በዓል በታሪኩ ጉዞ ስላለዉ እኛም ይህን ለማሰብ የዓድዋ ጉዞ ብለን ከዚህ ከኑረምበርግ ተነስተን ፍራንክፈርት ነዉ ያከበርነዉ። በዚህ ዓመት በኮሮና ስጋት ምክንያት እዚሁ ጥቂት ልጆች ተሰባስበን ነዉ የአድዋ ድል በዓልን በጋራ ያከበርነዉ።»    

ሥነ- ግጥም እና መነባንብ ወይም ትያትር የሚሰሩ ሰዎች ተዘጋጅተዉ ነዉ የሚቀርቡት። በዚህ መድረክ የአንቺ ድርሻ ምንድን ነዉ።

« የኔ ድርሻ በመድረኩ የሚቀርበዉን መነባንብ ወይም ሥነ-ግጥምን አልያም ሌላ ነገር የብሄር ግጭትን የማይቀሰቅስ አንዱን ከፍ አድርጎ ሌላዉን የማያኮስስ እንዳይሆን በደንብ መቆጣጠር ነዉ። ሥነ-ግጥሙ ስለፍቅር፤ ስለሰላም፤ ስለስደት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በምንም አይነት ቅሬታን የማያስነሳ እንዳይሆን እቆጣጠራለሁ። በተረፈ እኔ ይህ ነዉ ሞያዬ ማለት አልችልም፤ በማስተባበር ሁሉም ዉስጥ እገባለሁ። በሁሉ ዝግጅት ላይ ሁለገብ ነኝ። አብሪ አዘጋጃለሁ፤ በትያትሩም በዝግጅቱም አንዱ ከቀረ ተክቼ ገብቼ እተዉናለሁ አዘጋጃለሁ እንደዚህ ነዉ።»

በጀርመን ኑረምበርግ በተቋቋመዉ  «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» መድረክ ላይ ዋና ተሳታፊ ከሆኑት ገጣምያን መካከል ሰለሞን ሞገስ ይገኝበታል። ሰለሞን ሞገስ በኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ በተለያዩ የጥበብ መድረኮች የመጽሐፍ ምርቃት ላይ ሥነ-ግጥሞችን በማቅረቡ ይታወቃል። ሰለሞን ሞገስ «እዉነትን ስቀሏት» ከተሰኘዉ የግጥም መድብሉ «እኔ አንድ አንድ ስሰጥ የተሰኘዉን ግጥም ጋብዞናል።

ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ በስደት ሳሉ የጥበብ መድረኮች አለማግኘት ማለት  ምን ማለት ነዉ? እንደነገርከን በኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ በተለያዩ የጥበብ መድረኮች የመጽሐፍት ምረቃ ሥነ-ስረዓት ላይ ተሳታፊ ነበርክ።

Deutschland Äthiopische Kunst Gemeinde  in Nürnberg
ምስል privat

« በጣም ከባድ ነዉ። እዚህ ሃገር መኖር ከጀመርኩ ሦስት ዓመት አልፎኛል። በዚህ ዓመታት ዉስጥ ምናልባት ሁለት ግጥም ጽፊ ቢሆን ነዉ። እጅግ ከባድ ነዉ። እኔ ብቻ ሳልሆን አዉሮጳን ስንዞር ብዙ ተዋንያን የጥበብ ሰዎች፤ ሙዚቀኞች፤ ገጣምያን፤ የሥነ-ጽሁፍ ሰዎች አዉሮጳ ምን ያህል እንደዋጠቻቸዉ አይተናል። አዉሮጳ የነፍሳቸዉን ጥሪ ቀምታ ለኑሮ ለእንጀራ ብቻ እያኖረቻቸዉ ያሉ ብዙ ባለሞያዎች ብዙ ተሰጦ ያላቸዉን ሰዎች አይቻለሁ። በጣም ያሳዝናል። ስደት በጣም ከባድ ነዉ። እንደዉም እዚህ ሃገር እንደመጣሁ እነዚህኑ የተለያዩ ተሰጥኦ ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያንን ለምን በሞያችሁ አትሰሩም፤ ለምን አትሳተፉም፤ ብዬ ስጠይቃቸዉ፤ ቆይ አንተም ታየዋለህ ጠብቅ፤ አገሩ እንዴት እንደሚይዝህ ታየዋልህ፤ ሲሉ ነበር መልስ የሰጡኝ። እና አሁን እኔም አይቸዋለሁ። በጣም ከባድ ነዉ። ስለዚህም ነዉ «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» መስራች ሳሮንን ማበረታት የምፈልገዉ፤ ይህን አይቼ ነዉ። ብዙ የጥበብ ተሰጥኦ ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያን እዚህ ይኖራሉ። እነሱ እንዳይዋጡ ይህ አይነት መድረክ መደገፍ ያስፈልጋል። መድረኩ ለሥነ-ጽሑፍ ለኪነ-ጥበብ የሚያበረክተዉ አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። በሌላ በኩል ኢትዮጵያዉያን የሚገናኙበት ቦታም በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል። ስደት ከባድ ነዉ። ያዉ ሆዳችን ይሞላል ነገርግን ነፍሳችን ይራባል።»  

ሥነ-ፅሑፍ ሥነ ግጥም ተሰጥኦ እስከሆነ ድረስ ለምን ይዋጣል? ከአዕምሮ ማፍለቅ አይቻልም?

«ዉጭ ሃገር ሲኖር ከነበርሽበት ኩሪ ወጥተሽ ሌላ አዲስ ባህር ዉስጥ መግባት ማለት ነዉ። አዲስ ባህር ዉስጥ መስመጥ እንደማለት ነዉ። ይህ ደሞ ሌላ ባህል፤ ሌላ ቋንቋ በመሆኑ፤ ይህን እስኪ ረዱ ይህን እስኪተዋወቁ እና እስኪማሩ ድረስ በሁለት እግር ለመቆም ጊዜ ይወስዳል። በዚህ ዉጥረት ዉስጥ ደሞ ሥነ ጽሑፍን ለመስራት፤ ለማንበብ እጅግ ከባድ ነዉ። ምክንያቱም አዕምሮአችን በሌላ ነገር ተወጥሮ በመያዙ ነዉ። አዲስ ቋንቋ መማር ይኖራል፤ ባህሉ የአኗኗር ዘይቤዉ ሁሉ የተለየ ነዉ። በዚህም ምክንያት በሁለት እግር ለመቆም ብዙ ዓመታት ይፈጃል። ከዝያ በኋላ ህይወትን ከተላመዱ በኋላ ደግሞ፤ ወደ ሥነ-ጽሑፍ መግባቱ ከባድ ነዉ።ሥነ-ጽሑፍን በየጊዜዉ እያዳበሩ ካልሄዱ የሚረሳ የሚከብድ ጉዳይ ነዉ። የቋንቋ ችሎታም እራሱ እየቀጨጨ ነዉ የሚሄደዉ። ሥነ-ጽሑፍንም የምንጽፈዉ ከማኅበረሰቡ ህይወት ተነስተን ነዉ። እዚህ ደግሞ ያለዉ ህይወት ፈጽሞ የተለየ ነዉ። ስለዚህ እንዳየሁት ከሆነ ብዙ አመቺ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ። ግን ይህን ስል ይህን ማሸነፍ አይቻልም፤ ሁሌም ጨለማ ነዉ ማለቴ ግን አይደለም።»

ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ በአገር ቤት ሳለህ የጣይቱ የጥበብ ማዕከል ተወካይ እና ታላቅዋን የመድረክ እንቁ እና ገጣሚ ዓለምፀሐይ ወዳጆን ወክለህ፤ ትሰራ እንደነበር ሰምቻለሁ። ሰሞኑን እንደሰማነዉ የጥበቧ ንግሥት የዓለምፀሐይ ወዳጆ ህልም የተሳካ ይመስላል። እና ምን ተሰማህ ይህ ስታይ?

«የዓለምፀሐይ ወዳጆ ህልም እጅግ ትልቅ ነዉ። በቅድምያ የቀደሙትን ስናከብር ነዉ፤ የሚከበርንን ሰዉ መፍጠር የሚቻለዉ። እነ ጣይቱን ስናከብር ሌላ የሚከበሩ ጣይቶችን መፍጠር እንችላለን። ጣይቱን ካላከብርን ግን ሌሎች አርአያ ሆኖዉ የሚወጡ ሰዎችን መፍጠር አንችልም። ስለዚህ ዓለምፀሐይ ወዳጆ የረጅም ጊዜ ህልምዋ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ በማየቴ እኔ እንጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ጣይቱ ብቻ ሳይትሆን ዓለምፀሐይ ራስዋ ሃዉልት የሚገባት ናት። እስዋ ራስዋ ጀግና ናት። በኪነ-ጥበቡም፤ በሰብዓዊ በጎ አድራጎቱም በተለያዩ ነገሮች የሚነገርላት ምሳሌ የሆነችን ትልቅ ፈርጣችን ነች። ኢትዮጵያ ዉስጥ ጣይቱ ማለትን ዓለምፀሐይ ማለትን መናገር በራሱ ከባድ ችግር ነበረዉ። ብዙ መሰናክሎችን አልፍ ህልሟ ወደ ተግባር በመምጣቱ ትልቅ ስኬት ነዉ። በዚህም  ደስተኛ ነኝ። ስለዚህም በቀጣይ ብዙ ወጣት ዓለምፀሐዮችን ትፈጥራለች። ሃገር ቤት እያለንም ዓለምፀሐይ የምትነግረን የነበረዉ ወጣት የሥነ-ጽሑፍ ሰዎችን ገጣምያንን እንድናበረታታ ነበር። ታዋቂዎችን ስንወስድ፤ አይ እሱ ወጥቶአል፤ አሁን አዲስ ፍጠሩ፤ ለአዲሶቹ እድል ስጡ ነበር የምትለን። በዚህም ነዉ እዚህ ጀርመን ኑረምበርግ ሳሮንን ሳይ ዓለምፀሐይን በማይበት ዓይን እያየሁ ትብብሪን ተሳትፎዬን የቀጠልኩት።

Deutschland Äthiopische Kunst Gemeinde  in Nürnberg
ምስል privat

ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ እንደዉ በመጨረሻ የምጠይቅህ ነገር፤ እንዲህ እንደ «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» አልያም ሌሎች ሌሎች የኢትዮጵያዉያን ጥበብ መድረኮች ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ጥቅም ምንድን ነዉ ትላለህ?

«ኪነ-ጥበብ ማንነታችን ነዉ። እኔ ራሴን ባይ የተቀረጽኩት በኪነ-ጥበብ ነዉ። ኢትዮጵያዊ የሚለዉን ፍቅር ያገኘሁት ከኪነ-ጥበብ ዉስጥ ነዉ። ከግጥም ዉስጥ ነዉ። ከነጋሽ ጥላሁን ገሰሰ ሙዚቃ ዉስጥ ነዉ። ከነአስቴር አወቀ ሙዚቃ ዉስጥ ነዉ። ኢትዮጵያዊነትን ያገኘሁት። ከነጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን፤ ከነጋሽ ደበበ ሰይፉ ግጥም ዉስጥ ነዉ። ኢትዮጵያዊነትን የተማርኩት፤ ኢትዮጵያዊነትን ያገኘሁት፤ ከነሃዲስ አለማየሁ ድርሰት ዉስጥ ነዉ። ኢትዮጵያዊነትን ያገኘሁት ከነአቤጎበኛ አመጽ ዉስጥ ነዉ። ኢትዮጵያዊነትን የተማርኩት እና ማንነቴን የቀረፀኝ ኪነ-ጥበብ ነዉ። ማንነታችንን የቀረፀን ኪነ-ጥበብ ነዉ። በኪነ-ጥበብ በሙዚቃ በሥነ-ጽሁፍ ያላደገ ዜጋ፤ ማንነቱ የተሟላ ይሆናል ብዬ አላስብም። ኪነ-ጥበብ ከእናት አባቶቻችን እኩል የወለደን የማነታችን ቀራጭ ነዉ። ኪነ-ጥበብ ወልዶ ስሎ ለተሻለ ስብዕና የሚያበቃን ትልቅ መሳርያም ነዉ።  

በጀርመን ኑረምበርግ የኢትዮጵያዉያኑ «ሃገሬ የጥበብ ምሽት» ይጠንክር ያብብ እንላለን። ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ