1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኪነ ጥበብአፍሪቃ

ጎዳናን በሥዕል ጥበብ ማስዋብ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሐምሌ 22 2014

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች፣ በትምህርት ቤቶች ፣ በምግብ ቤት እና የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የ Addis Street Art ተቋም ሥራዎች ይገኛሉ። የጎዳና የሥዕል ጥበቦችን እና ግራፊቲ የሚባሉትን የሥዕል ሥራዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት አስቤ ነው የጀመርኩት የሚለው ሰለሞን ክፍሌ የተቋሙ መስራች ነው። ሥራውን ከጀመረ 5 አመት ሆነው።

https://p.dw.com/p/4EowT
Äthiopien- Addis Street Art
ምስል ASA

Addis Street Art

ምናልባት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የእነዚህ ሠዓሊያን ሥራዎችን ጎዳናዎች ላይ አስተውላችሁ ይሆናል። ሥዕሎቻቸው በደማቅ ቀለማት ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ ትምህርት አዘል መልዕክት አሏቸው። « መንገድ ላይ ያለ የትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሰው ስዕሉን ያየዋል። » የሚለው ሰለሞን ምንም እንኳን እንደ ውጪው ዓለም ነፃነቱ ሰፊ ባይሆንም በአሁኑ ሰዓት በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እየሰሩ እንደሆነ ይናገራል።  የጎዳና ላይ ጥበብን መሳጭ የሚያደርገው ተደብቆ ሲሰራ እንደሆነ የሚያምነው ሰለሞን በአሁኑ ሰዓት ግን እየሰሩ ያሉት ፍቃድ ባገኙባቸው ቦታዎች ላይ ብቻ እንደሆነ ገልፆልናል። 

Addis Street Art በአሁን ሰዓት የተለያዩ የሥራ ድርሻ ያላቸው ከ30 በላይ አባላት አሉት። ገብረእየሱስ አስማረ እና ቤተል ጌቱ ከሠዓሊዎቹ አባላት መካከል ናቸው።
ምንም እንኳን የተቋሙ መጠሪያ ስም አዲስ አበባን ቢወክልም «አላማችን ከአዲስ አበባ ውጪም ኢትዮጵያን ቀለማማ ማድረግ ነው » ይላል ሰለሞን። አብሮት የተማረው የ 27 ዓመቱ ገብረእየሱስ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥዕል ተመራቂ ሲሆን መደበኛ ሥራው ስቱዲዮ ውስጥ ሥዕል መሳል ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ ጎዳና ላይ ለ Addis Street Art ይስላል።  አንዱ ስዕሉ በኮሮና ጊዜ የተሳለ ሲሆን « ለኮቪድ ክትባት የተገኘበት ጊዜ ነበርና ያን ጊዜ ነገሮች ወደ በጎ የተለወጡበት ጊዜ እንደሆነ ፣ ህብረተሰቡን ወደ መደበኛ ህይወት የሚመልሱ ነገሮች ላይ ነበር የሰራሁት»።  ከዚህ በተጨማሪ የስደትን አስከፊነት የሚያሳይ ርዕስ ላይ ገብረእየሱስ ስሏል። « አንድ ማንነቱ የማይታወቅ ወጣት፤ የውኃ ላይ መንሳፈፊያ ጃኬት አድርጎ ፤በፁሁፍ ደግሞ እንዲሰደድ ያስገደዱት ምክንያቶች ተቀምጠዋል። ስደት ከባድ እንደሆነ እንዲያሳይ ደግሞ በጥቁር ቀለም የውኃ ላይ መንሳፈፊያ ጃኬት አድርጓል፤ እንፋሎት ይታያል።» ይላል ሰዓሊው ገብረእየሱስ

Äthiopien- Addis Street Art
ገብረእየሱስ አስማረምስል ASA

የ3ኛ ዓመት የግራፊክ ዲዛይን የዩንቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ቤተል ጌቱም በምስል ሌሎችን ማስተማር የሚችሉ ሥዕሎችን መሳል እንደሚያስደስታት ገልፃልናለች። « እኔ የሳልኩት ዓለም ወደፊት ብትሆንልኝ ብዬ የማስበውን ነገር ነው። ከክፍለ ሀገር ነው የመጣሁት እና በምኖርበት አካባቢ ተፈጥሮዋዊ ነገሮች ቢኖሩ ደስ ይለኛል። ስለሆነም ብዙ አረንጓዴ ቀለሞችን ነው የተጠቀምኩት»

Äthiopien- Addis Street Art
ቤተል ጌቱ ምስል ASA

ቤተል ጎዳና ላይ ስትስል ፈተና ሆኖ ያገኘችው አንዱ ነገር «ብዙ ሰዎች እየመጡ ጥያቄ ስለሚጠይቁ ለእነሱ መልስ መስጠት አተኩረን እንዳንሰራ ሊያደርገን ይችላል» ትላለች። ሌላው የጎዳና ላይ ጥበብን ከባድ የሚያደርገው ነገር ቤተል እንደምትለው እንደልብ ቦታ አለመገኘቱ ነው። ቤተል እስካሁን በሁለት የጎዳና ጥበብ ላይ በመካፈል ሥራዎቿን ማሳየት ችላለች። የ 23 ዓመቷ ወጣት የተሳተፈችበት ሌላው የጎዳና ሥራ እጎአ ባለፈው ግንቦት ወር የተከበረው  የ EUROPE DAY  ወይም የአውሮፓውያን ቀንን አስመልክቶ የአውሮፓን እና የኢትዮጵያ ግንኙነትን ለማሳየት Addis Street Art ባቀረበው የሥዕል ሥራ ነው። እንደ አውሮፓ ህብረት እና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የባህል ተቋማት ጋር አብሮ የሚሰራው Addis Street Art  አላማው ሥራው ሥዕል ስሎ ገንዘብ ከማግኘት በላይ ነው ይላል ሰለሞን። የተሳተፉበት የ «ጥበብ በአደባባይ» ፕሮጀክት አንዱ ምሳሌ ነው። ይህም ፕሮጀክት የጀርመን የቋንቋ እና የባህል ተቋም (Goethe-Institut) በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ነው። ብዙ ቦታዎች ላይ ሽንት መሽናት የተከለከለ እንደሆነ በፁሁፍ እንደሚገኝ ያስተዋሉት እነዚህ ሰዓሊያን ይህንን ሁኔታ በምስል አስደግፈው ለመግለፅ እንደመረጡ ሰለሞን ይናገራል። « ለምሳሌ አንድ ሰውዬ ዱላ ይዞ ሲያስፈራራ፤ እዚህ ጋር ልትሸና ባልሆነ የሚል የሚያስቅ ምስል መጨመር፤ ብቻ እነዚህ ፁሁፎች ተፅፈው ያገኘንባቸው ቦታዎች ላይ በሚያዝናና መልኩ እነዚህን ስዕሎች ሳልን። እና ወደነው የሰራነው ፕሮጀክት ነው። » ይላል ሰለሞን።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ