1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

'ለሐቅ የመጨረሻውን ዋጋ የከፈለው' ጋዜጠኛ ኢብራሒም

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 27 2010

«ኢብራሒም አገሩን ሲለቅ ዋንኛ ምክንያቱ ለሐቅ ያለው ጥብቅና ነው። በሕይወቱ ዘመን ሲሟገትላቸው የኖረላቸው ሐሳቦች ከፖለቲካ እስከ ስፖርት አብዛኞቹ የሕዝብን ወገንተኝነት እና የሐቅ ወዳጅነቱን ያሳየባቸው» ናቸው - ጋዜጠኛ ሐብታሙ ስዩም።

https://p.dw.com/p/2qPzD
Äthiopien Ibrahim Shafi, Journalist
ምስል Ibrahim Shafi

ሐብታሙ ስዩም እና እንዳልካቸው ጥላሁን ስለጋዜጠኛ ኢብራሒም

ከትናንት በስቲያ በስደት በሚኖርባት ኬንያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ታኅሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈፅሟል። የ37 አመቱ ኢብራሒም ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ፤ ያረፈው ደግሞ ረቡዕ ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በናይሮቢ ከተማ ላንጋታ በተሰኘው ክፍለ ከተማ ነው። «እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ አብረን ነበርን» የሚለው የስራ እና የስደት አጋሩ ጋዜጠኛ ሐብታሙ ስዩም የኢብራሒም ዕረፍት ከፍተኛ ሐዘን ፈጥሮበታል። «ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በጣም በጠና የታመመ ቢሆንም እስከ መጨረሻ የሕልፈት ሰዓቱ ድረስ ሐሳቦቹን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ያጋራ ነበር። ከዛ አንፃር ነው በትልቁ ድንጋጤ የተፈጠረው። ሆኖም ሕመም ከጀመረው እና አልጋ ላይ ከዋለ ትንሽ ቆይቷል» ይላል ሐብታሙ።

ኢብራሒም ሻፊ በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ከፍተኛ 12 ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት የሥነ-ዜጋ መምህር ሆኖ አገልግሏል። በአዲስ አበባ መስተዳድር ትምሕርት ቢሮ የአስተዳደር ሠራተኛም ነበር። ከታሪካዊው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ለእስራት ተዳርጓል። ሐብታሙ ስዩም «በ97 ዓ.ም. በእስር ላይ እያለ የስቃይ ተግባራት ስለተፈጸሙበት ከዚያ በኋላ መላ ሰውነቱ ላይ ሕመሙ ተባብሶበት ነበር። ሕመሙ ወሰድ መለስ የሚያደርግ ነው። አንድ ሰሞን ይሻለዋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ይብስበታል። ለክፉ የሚሰጥም አልመሰለውም» ሲል መለስ ብሎ ያስታውሳል።  

የኢብራሒም ዕረፍት ለወዳጆቹ፣ ለአድናቂዎቹ እጅጉን አስደንጋጭ ሆኗል። «በጣም ከባድ ነው» ይላል «ኢብሮ» በሚል የቁልምጫ ስም የሚጠራው የቀድሞ የስራ አጋሩ ጋዜጠኛ እንዳልካቸው ጥላሁን። እንዳልካቸው ከኢብራሒም ጋር በመሆን በሸገር 102.1 ራዲዮ «ኳስ ሜዳ» በተባለ መሰናዶ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ለዓመታት በቀጥታ አስተላልፈዋል። በዚህ ዝግጅትም ሆነ በአዘጋጅነት ለበርካታ ዓመታት በሰራበት «ኢትዮ ስፖርት» ጋዜጣ ኢብራሒም የሚታወቀው በሚያቀርባቸው ጥልቅ ዘገባዎች እና በሳል ትንታኔዎች ነበር።

Äthiopien Ibrahim Shafi, Journalist
ምስል Ibrahim Shafi

«በአገር ውስጥ ከታዳጊዎች እስከ ብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታ ድረስ እና ስፖርት አስተዳደር፤ በእግር ኳስም ሆነ በሌሎች አስተዳደር ላይ መረጃ ያለው ነው። በስሜት የመመራት ሳይሆን ነገሮችን በጥልቀት በየትኛውም አቅጣጫ [ለማየት]፣ ለመሟገት፣ ለማሳወቅ፣ ለማስተማርም በሚያስችል ደረጃ የተሟላ ተሰጥዖ ያለው ነው» ይላል እንዳልካቸው። 

ኢብራሒም የስፖርት ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም። ወዳጆቹ በ«መዝናኛ» ጋዜጣ እና በ«አዲስ ጉዳይ» መፅሔት ያስነበባቸው መጣጥፎቹ በሳል እንደነበሩ ያስታውሳሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራቂው ኢብራሒም «በፖለቲካ በኩል፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ፣ በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ጥልቅ እውቀት እና ትንተና በእግር ኳሱ ካለው የማይተናነስ» ነበር ሲል እንዳልካቸው ይናገራል።  

ኢብራሒም አገር ጥሎ ለመሰደድ ከመገደዱ በፊት የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ረዳት አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። የያኔው የኢትዮጵያ ፍትኅ ሚኒስቴር ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. «ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳት፣ ሀሰተኛ ወሬዎችን በህትመት መልክ በማሰራጨትና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር» ከከሰሳቸው አምስት ጋዜጦች እና መፅሔቶች መካከል አንዱ «አዲስ ጉዳይ» ነበር። «የኢትዮጵያ መንግሥት ያስረናል ወይም ሌላ ጠንካራ እርምጃ ይወስድብናል» በሚል ሥጋት ወደ ኬንያ ከተሰደዱ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ኢብራሒም ነበር።

የ«አዲስ ጉዳይ» ባልደረባው የነበረው እና አብሮትም የተሰደደው ሐብታሙ ስዩም «በሕይወት ዘመኔ ከማውቃቸው ሰዎች ለሐቅ የመጨረሻውን መሥዋዕትነት ከከፈሉ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው» ሲል ይገልጸዋል። «ኢብራሒም አገሩን ሲለቅ ዋንኛ ምክንያቱ ለሐቅ ያለው ጥብቅና ነው። በሕይወቱ ዘመን ሲሟገትላቸው የኖረላቸው ሐሳቦች ከፖለቲካ እስከ ስፖርት አብዛኞቹ የሕዝብን ወገንተኝነትእና የሐቅ ወዳጅነቱን ያሳየባቸው» ናቸው ሲል ያክላል። 

ኢብራሒም በኬንያ ሳለም ለሐቅ፣ ፍትህ፣ ርትዕ እና ለተሻለች ኢትዮጵያን ጥብቅና የቆሙ ሀሳቦቹን በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲያካፍል ቆይል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ እና የጥበብ ጉዳዮች ላይ በሚሰጣቸው አስተያየቶችም ይታወቃል።  ሐብታሙ ስዩም እና እንዳልካቸው ጥላሁን ጋር በስልክ የተደረገውን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ ።  

ሐብታሙ ስዩም

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ