1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ፕሬዝዳንት ምርጫ

ማክሰኞ፣ የካቲት 1 2014

ሶስቱ የጀርመን ገዥ ፓርቲዎች የደገፏቸው ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በጀርመን ፕሬዝዳንት የሚመረጠው በቀጥታ በህዝቡ ሳይሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች በሚወከሉ የምክር ቤት አባላት እንዲሁም በየተሰማሩባቸው መስኮች ከበሬታ በሚሰጣቸው ሰዎች ነው።

https://p.dw.com/p/46i8I
Deutschland | Schloss Bellevue in Berlin | Amtssitz des Bundespräsidenten
ምስል Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

የጀርመን ፕሬዝደንት ምርጫ

ጀርመን መጪውን ፕሬዝዳንትዋን ለመመርጥ አምስት ቀናት ቀርተዋታል። ምርጫው የሚካሄደውም  ስልጣን ላይ ያሉት የፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የአምስት ዓመቱ የስራ ጊዜያቸው ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት ነው። ለዚህ ከፍተኛ ሃላፊነት የ66 ዓመቱን ፕሬዝዳንት ሽታይንማየርን ጨምሮ አራት እጩዎች ይወዳደራሉ። ከሽታይንማየር ሌላ ለውድድር የሚቀርቡት በግራ ክንፉ ፓርቲ የተጠቆሙት የ65 ዓመቱ ዶክተር ጌርሃርድ ራቫርት አማራጭ ለጀርመን የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ያጫቸው የቀድሞ የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ አባል የ57 ዓመቱ ዶክተር ማክስ ኦተ  እና  «ነጻ መራጮች»የተባለው ፓርቲ ያቀረባቸው የ42 ዓመትዋ ዶክተር ሽቴፋኒ ጌባወር ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ግን በጀርመን ጥምር መንግሥት ውስጥ የተካተቱት ሶስቱ ፓርቲዎች ድጋፋቸውን የሰጧቸው ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በድጋሚ ይመረጣሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የሕግ ባለሞያው ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እንደገለጹት በጀርመን ፕሬዝዳንት የሚመረጠው በቀጥታ በህዝቡ ሳይሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛቶች በሚወከሉ የምክር ቤት አባላት እንዲሁም በየተሰማሩባቸው መስኮች ከበሬታ በሚሰጣቸው ሰዎች ነው።ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ግን ህዝቡ ፕሬዝዳንቱን በቀጥታ ይመርጥ እንደነበረ ዶክተር ለማ ያስታውሳሉ። ይሁንና ናዚ ጀርመን በጦርነቱ ተሸንፎ አዲስ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ ጦርነቱ ያስከተለው የታሪክ ጠባሳ እንዳይደገም ለፕሬዝዳንቱ የሚሰጠው ስልጣን እንዲገደብ መደረጉን ዶክተር ለማ ገልጸዋል።

Max Otte CDU | Präsidentschaftskandidat der AfD
ምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

በእሁዱ ምርጫ ለመወዳደር ከቀረቡት እጩዎች መካከል አስቀድመው ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር እንደሚፈልጉ ያሳወቁት ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር ይመረጣሉ ተብሎ በሰፊው ይጠበቃል። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኅይለ ሚካኤልም ተመሳሳይ ግምት አለው።ዶክተር ለማ ይፍራሸዋም ሽታይንማየር በእርግጠኝነት ይመረጣሉ ብለዋል።በርሳቸው አስተያየት የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ልምድ ይጎድላቸዋል ያሏቸው ሌሎቹ ተወዳዳዳሪዎች የማሸነፍ እድላቸው ዝቅተኛ ነው። እንደ ጀርመን ሁሉ በኢትዮጵያም የፕሬዝዳንቱ ወይም የፕሬዝዳንቷ ስልጣን የተገደበ ቢሆንም የርዕሰ ብሄር አመራረጥ ግን ይለያል ።ሃላፊነታቸው ቢመሳሰልም ሌሎች የሚለያዩባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ነው ዶክተር ለማ ያስረዱት።ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር በድጋሚ ይመረጣሉ ወይስ ሌላ አዲስ ሰው?በመጪው እሁድ ምርጫ ውጤት ይወሰናል።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ